
ነገሩ ሁሉ የጀመረው ቅዳሜ አመሻሽ ገደማ ነው። ከአማራ ክልል የሚወጡ ዜናዎች በርካቶች ያልጠበቁት ነበር። በአማራ መንግሥት መስተዳድር ላይ “መፈንቅለ-መንግሥት” እንደተሞከረ ተገነረ።
በአማራ ክልል በደረሰው በዚህ ጥቃት በቅርቡ ወደ ሥልጣን የመጡት አቶ አምባቸው መኮንን [ዶ/ር] መጎዳታቸውን ተሰማ። እሳቸው ብቻ ሳይሆኑ አማካሪያቸው አቶ እዘዝ ዋሴም ጥቃት እንደደረሰባቸው ወሬዎች መሠራጨት ጀመሩ።
በአማራ ክልል አስተዳደር ላይ “የመፈንቅለ-መንግሥት” ሙከራ መደረጉን በብሔራዊ ቴሌቪዥን ቀርበው ይፋ ያደረጉት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ቃል-አቀባይ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ነበሩ።
• ስለ’መፈንቅለ መንግሥት’ ሙከራው እስካሁን የማናውቃቸው ነገሮች
• ሳፋሪኮም የተጠቃሚዎችን መረጃ በማውጣት ተከሰሰ
• በሱዳን የተቋረጠው ኢንተርኔት ለአንድ ጠበቃ ብቻ መሥራት ጀመረ
ይህ በሆነ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ደግሞ አዲስ አበባ ውስጥ ሌላ አሳዛኝ ዜና ተሰማ። ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ በገዛ ጠባቂያቸው በጥይት መመታታቸው፣ እንዲሁም አብረዋቸው የነበሩት ጄነራል ገዛዒ አበራም ጉዳት እንደደረሰባቸው ተገነረ።
ፕሬስ ሴክሬታሪው ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ ቀርበው ከሠጡት መግለጫ ውጭ ምንም ዓይነት ይፋዊ መግለጫ አልተሰማም።
ቅዳሜ አመሻሹን የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ በሰጠው መግለጫ የክልሉ ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ፅጌ “የመፈንቅለ-መንግሥ” ሙከራ ነው ከተባለለት ክስተት ጀርባ ያሉ ሰው መሆናቸውን አሳወቀ።
ማሕበራዊ ሚድያ ላይ ዜናው የተዋጠላቸውም ሆኑ ያልተዋጠላቸው ሐሳባቸውን ከመሰንዘራቸው ውጭ የክልልም ሆነ የፌዴራል ባለሥልጣን ጉዳዩን አስመልክቶ ሙሉና ግልፅ መረጃ ሊሰጥ እንዳልቻለ አስተያየት ሰጭዎች ይናገራሉ።
ምሽቱን በይነ-መረብ መቋረጡን ከወደ አዲስ አበባ ሰማን።
እኩለ ሌሊት ገደማ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አሕመድ ዥጉርጉር ወታደራዊ ሸሚዝ ለብሰው ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ ብቅ አሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው ባህር ዳር ከተማ ውስጥ “የመፈንቅለ-መንግሥት” ሙከራ የተደረገው የክልሉ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ስብሰባ በማካሔድ ላይ በነበሩበት ጊዜ ነው ሲሉ አስታወቁ።
“በመፈንቅለ መንግሥት” ሙከራው ወቅት ጥቃት ከተፈጸመባቸው መካከል “ከፊሉ መሞታቸውንና ከፊሉ መቁሰላቸውን” ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩ ሲሆን ጉዳቱ የደረሰባቸው እነማን እነደሆኑ የሰጡት ምንም ዓይነት ማብራሪያ ግን አልነበረም።
አክለውም ኤታማዦር ሹማቸው አዲስ አበባ ላይ ጉዳት እንደደረሰባቸው አሳወቁ። ‘አዲስ አበባ ውስጥ በኤታማዦር ሹሙ ላይ የተፈጸመው የመግደል ሙከራ “ከመፈንቅለ መንግሥቱ” ሙከራ ጋር ግንኙት አለው’ ሲሉም ተደመጡ።
ኤታማዦር ሹሙ ፡ከመፈንቅለ መንግሥት” ሙከራው ጋር በአማራ ክልል የተከሰተውን ችግር ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት እየመሩ እንደነበር የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምሽት ላይ “ቅጥረኞች” ጄኔራል ሰዓረንና አጋራቸው ጄኔራል ገዛዒ አበራን እንዳጠቋቸው ተናገሩ።
እሑድ
እሑድ ጠዋት ላይ በርካታ መረጃዎች ተከታትለው ወጡ። ጄኔራል ሰዓረ እና ጄኔራል ገዛዒ መሞታቸውን ለማርዳት ድምጸ ወያነን የቀደመ አልነበረም። ትንሽ ቆየት ብሎ ደግሞ በብሔራዊው የቴሌቪዥን ጣቢያ ‘የአማራ ክልል አስተዳዳሪ አቶ አምባቸው መኮንንና አማካሪያቸው አቶ እዘዝ ዋሴ ተሰዉ’ ሲል አተተ።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት መግለጫ እሰጣለሁ ሲል ለመገናኛ ብዙኃን ሰዎች መልእክት አስተላለፈ። ረፋዱ ላይ በሥፍራው የተገኙት የሚድያ ሰዎች ተንቀሳቃሽ ስልካቸውን አስቀምጠው ገቡ።
መግለጫውን የሰጡት አቶ ንጉሱ ጥላሁን [በአማርኛ] እና ቢለኔ ስዩም [በእንግሊዝኛ] ነበሩ። ከጋዜጠኞች ጥያቄ ለመቀበል ዝግጁ ያልነበሩት ቃል አቀባዮቹ በመግለጫቸው ጄኔራል ሰዓረ፣ ጀኔራል ገዛዒ፣ አቶ አምባቸውና አቶ እዘዝ መሞታቸውን አረጋገጡ።
ጄነራል ሰዓረ ላይ ጥቃት አድርሷል የተባለው ግለሰብ ቢጎዳም በቁጥጥር ሥር መዋሉን አሳወቁ። በአማራ ክልል የተደረገውን “የመፈንቅለ-መንግሥት ሙከራ” ያካሄዱት በቅርቡ በምሕረት የተለቀቁት ብርጋዴር ጄነራል አሳምነው ፅጌ እንደሆኑም ተገለጸ።
ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ላቀ አያሌው የአማራ ክልል ተጠባባቂ ፕሬዝደንት ሆነው እንደሚያገለግሉ የተሰማውም በዚሁ መግለጫው ላይ ነበር።
እሑድ ረፋዱን ከተሰሙ ትኩስ ዜናዎች አንዱ የአማራ ክልል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ አቶ ምግባሩ ከበደ በደረሠው ጥቃት ተጎድተው ሕክምና ላይ መሆናቸው ነበር።
እሑድ ከሰዓቱን ለቢቢሲ ድምፃቸውን የሰጡት የክልሉ የሰላም ግንባታና ህዝብ ደኅንነት ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ገደቤ ኃይሉ ‘የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድርን ጨምሮ ከፍተኛ አመራሮች ግምገማ እያካሄዱ ባሉበት ወቅት ብርጋዴር ጄኔራሉ በልዩ ኃይሎች ታጅበው እንደመጡና በመጀመሪያም የርዕሰ መስተዳደሩ አጃቢዎች ላይ ተኩስ እንደከፈቱ፤ ቀጥለውም የክልሉ አመራሮች ላይ የተኮሱ ሲሆን በዚህም ሦስቱ እንደተመቱ’ አስረዱ።
አክለውም አለቃቸው እና “መፈንቅለ-መንግሥት ሙከራውን” በማቀነባበር የሚጠረጠሩት ብራጋዴር ጄነራል አሳምነው የት እንዳሉ እንደማይታወቅ ገለፁ።
ሰኞ
እጅጉን የተጣረሱ መረጃዎች ብቅ ብቅ ማለት የጀመሩት በዕለተ ሰኞ ነው። መጀመሪያ የተሰማው ግን የአማራ ክልል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ አቶ ምግባሩ ከበደ መሞት ነበር።
ከሁሉ ልቆ የወጣው ዜና ግን የብርጋዴር ጄነራል አሳምነው ፀጌ መገደል ነው። ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያው ኢቲቪ ‘ብርጋዴር ጄነራል አሳምነው ፅጌ ተገደለ’ የሚል ዜና ይዞ ብቅ አለ።
ብርጋዴር ጄነራል አሳምነው ከባህርዳር ወጣ ብሎ ባለች ዘንለዘልማ ተብላ በምትታወቅ ሥፍራ በተደረገ የተኩስ ልውውጥ እንደተገደሉ ተሰማ።
ሌላኛው ዜና ደግሞ ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የተሰማ ነበር። ዜናው ደግሞ የጄነራል ሰዓረ ገዳይ መሞቱን የሚያትት ነበር። ይህ ዜና ነበር ብዙዎችን ግራ ያጋባው።
ቢቆስልም በቁጥጥር ሥር ውሏል የተባለው ግለሠብ ራሱን አጥፍቷል መባሉ ግርታን ፈጠረ። እንዴት በቁጥጥር ሥር ያለ ሰው ራሱን ያጠፋል? የብዙዎች ጥያቄ ነበር። የፖሊስ መግለጫ እና የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀተታ መጣረስ ጉዳዩን ከድጡ ወደማጡ አደረገው።
ነገር ግን ዘግይቶ ደግሞ ብሐራዊው የቴሌቪዥን ጣቢያ ግለሰቡ አልሞተም፤ በሕይወት አለ ሲል አተተ።
ሥርዐተ ቀብር
ቅዳሜ ምሽት አዲስ አበባ ውስጥ የተገደሉት የሃገር መከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም የጄኔራል ሰዓረ መኮንን አዲስ አበባ ውስጥ በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቀብራቸው እንደሚፈጸም ተናግሮ ነበር።
የጠቅላይ ሚንስትሩ ፕሬስ ሴክሬታሪ ቢልለኔ ስዩም ቀደም ብሎ እንደተናገሩት የጄነራል ሰዓረ የቀብር ሥነ ሥርዓት ማክሰኞ ዕለት እንደሚፈጸምና በዚህም የጄነራሉ አስከሬን ከቤታቸው ተነስቶ በወታደራዊ ሥርዓት ታጅቦ ወደ ሚሊኒየም አዳራሽ ተወስዶ ከጠዋት እስከ ስድስት ሰዓት ድረስ በሚሊኒየም አዳራሽ ቤተሰቦቻቸው፣ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት፣ ታዋቂ ግለሰቦች እንዲሁም ወዳጅ ዘመዶቻቸው በሚገኙበት የሽኝት ሥነ ሥርዓት ይደረጋል ተብሎ ነበር።
የዛኑ ዕለት የትግራይ ቴሌቪዠን ላይ ከቤተሰቦቻቸውና ከትግራይ ክልል ባለስልጣናት እንደተነገረው የቀብር ሥነ ሥርዓታቸው መቀሌ ውስጥ ይፈፀማል ተብሏል።
በርካታ መረጃ፤ ሥፍር ጥያቄ. . .
በክልል ደረጃ “መፈንቅለ-መንግሥት” አለ ወይ ከሚለው አብይ ጥያቄ አንስቶ የቅዳሜው ክስተት እና መዘዙ ብዙ ጥያቄዎች እያስተናገደ ነው።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ [አብን] ጉዳዩ ጥቃት እንጂ ‘የመፈንቅለ-መንግሥት’ ሙከራ አይደለም ሲል ተቃወመ፤ በተፈጠረው ነገር ማዘኑን ሳይሸሽግ።
አቶ ገደቤ ጉዳዩን ሲተንትኑልን እንዲህ ብለው ነበር፤ “11፡00 ሰዓት አካባቢ የተወሰኑ የፀጥታ አመራሮች ከድርጊቱ በፊት ለስብሰባ እንደተፈለጉና ወደ ስብሰባው ቦታው እንደሄዱ፤ ከዚያም ወዲያውኑ እነርሱ መግባታቸው ከተረጋገጠ በኋላ ተከታትሎ የተደራጀ ኃይል ገብቶ ከፍተኛ ተኩስ በመክፈት ግለሰቦች እንዲታፈኑና እንዳይንቀሳቀሱ መደረጉን አውቃለሁ።”
አቶ ገደቤ አክለው “በወቅቱ እኔ በስብሰባው ላይ አልነበርኩም፤ አልተጠራሁም። ቅዳሜ እስከ 7፡00 ሰዓት ድረስ ብርጋዴር አሳምነው ቢሮ ነበርኩ። 9 ሰዓት አካባቢ ሌላ ሥራ ስለነበረኝ እስከ 11፡00 ሰዓት ሥራ ላይ ነበርኩ፤ ከዚያም ከፍተኛ ተኩስ ሰማሁ” ሲሉ ክስተቱን ያወሳሉ።
አቶ ገደቤ ጥቃቱ ከፕሬዝደንቱ ጽሕፈት ቤት በተጨማሪም የፀጥታ ቢሮ፣ ፖሊስ ኮሚሽን፣ የርዕሰ መስተዳድሩ ቢሮና የአዴፓ ጽሕፈት ቤት ላይም ጥቃት መፈፀሙን ተናግረዋል። በርካታ የፀጥታ ኃይሎች መገደላቸውን አቶ ገደቤ ይናገራሉ፤ ምንም እንኳ ቁጥሩን ይፋ ባያደርጉም።
በባሕርዳር የርዕሰ መስተዳድሩ ጽሕፈት ቤት ስብሰባ ላይ የነበሩት ሰባት ሰዎች እንደነበሩ ተነግሯል። ከሞቱት አራት ባለሥልጣናት በተጨማሪ አቶ ዮሃንስ ቧያለው፣ አቶ ላቀ አያሌው፣ አቶ መላኩ አለበል እና አብርሃም አለኸኝ በሕይወት የተረፉ ናቸው።
ብርጋዴር ጀኔራል አሳምነው ፅጌ ከሰሞኑ ልዩ ኃይል ሲያስመርቁ የተለየ ወታደራዊ ልብስ መልበስቸውና ያስተላለፉት መልዕክትስ ከግርግሩ ጋር ምን ግንኙነት አለው? አሁንም ምላሽ ያላገኙና ጊዜ የሚጠብቁ ናቸው።
የባሕርዳሩ ግርግር እና የጄኔራል ሰዓረ ግድያ ምን አገናኛቸው? ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉዳዩን ሲከታተሉ ነው ቢሉም፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ ዝርዝር መረጃ እስኪገኝ ድረስ አጥጋቢ ሆኖ የተገኘ አይመስልም።