June 26,2019 Posted by: ዘ-ሐበሻ

አንዱ ዓለም ተፈራ – ረቡዕ ሰኔ ፲፱ ፳ ፻ ፲ ፩ ዓመተ ምህረት

መረጋጋት አለብን

አሁን በባሕርዳር የተከሰተውን ድርጊት አልፈን ወደፊት ለመሄድ፤ በሁሉም ወገን ያለን፤ መነጋገር፣ መተማመንና፣ መተሳሰብ አለብን። የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሀቅ ሆኖብን፤ የውጪሰው ኢትዮጵያዊ ዐማራዎች፤ በዚህ ጉዳይ ከማንም በላይ ከፍቶን እየተከታተልን ነው። እያንዳንዳችን ከተለያዬ ምንጮች፤ የየራሳችን የሆኑ መረጃዎችን እያገኘን፤ እሁንም በየተለያዩ ስብስቦች ሆነን፤ የተለያዩ አቅጣጫዎችን የያዙ ፈለጎች እየቀየስን ነው። የዚህ በተለያየ መልክ የምናደርገው ጉዞ፤ ይሄው የት እንዳደረሰን ግልጥ ነው። የአመለካከት ልዩነት፤ ከግለሰብ ተክለ ሰውነት ጋር ተዳምሮና በሌሎች ተሹሮ፤ ለዚህ ግድያ አብቅቶናል። ዐማራ ነን ብለን ለዐማራው ኅብረተሰብ የምንቆረቆር ሁሉ፤ አሁን ማድረግ ያለብን መረጋጋት ነው።

በሀገር ቤት ያለንም ሆነ በውጪ ሀገራት የምንገኝ፤ “እንዲህ ስለሆነ ነው!” ወይንም፤ “እንዲያ ቢሆን ኖሮ!” እያልን፤ ተጨባጭ ባልሆኑ ሁኔታዎች ከመነከር ይልቅ፤ ወደፊት እየተመለከትን፤ የሁላችን የጋራ የሆኑ፤ የነበሩና የወደፊት ጉዳዮቻችን ላይ ማተኮሩ ይጠቅመናል። የሁላችን ሥጋት አንድ ነው። ሁላችን እንዲሆን በምንፈልገው ላይ የዓላማ አንድነት አለን። በነዚህ መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ አንድነት ስላለን፤ ከዚህ ያነሱ የሃሳብ ልዩነቶቻችንን በሚዛን መጠበቁ ተገቢ ይሆናል። በረባ ባልረባው መከፋፈሉና በዚያ ላይ ማተኮሩ ለዚህ አብቅቶናል።

በርግጥ በባሕርዳር የተከሰተው በቀላሉ የሚተውና የሚታለፍ አይደለም። ነገር ግን፤ ሚዛን መኖር አለበት። እኔም እንደያንዳንዳችሁ ብዙ ጥያቄዎች አሉኝ። የአካባቢ መፈንቅለ መንግሥት ማለት ምን ማለት ነው? ባሕርዳር የ “ዐማራ መንግሥት መፈንቅለ መንግሥት!” እየተካሄደ፤ የሁለት ጀኔራሎች አዲስ አበባ ላይ መገደል በምን ይያያዛል? ከግድያው ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸውን ሌሎች ባሕርዳር የተገኙ የዐማራ ባለሥልጣናትን እና የበታቾቻቸውን ማሰር ምን ማለት ነው? የዐማራው ሚሊሽያ ማቋቋም በምን መስፈርት ወንጀል ሆኖ ተገኘ? ይህ በትግራይና በኦሮሚያ እየተካሄደ አይደለም ወይ?

በሥልጣን ላይ ላሉ የመንግሥት አካላት የማስተላልፈው፤ ሕዝቡን ለማረጋጋት፤ እውነት ማዕከላዊውን ቦታ መያዝ አለበት። ሀቅ ያስተባብረናል። ሀቅ የማንም የግል ንብረት አይደለም። ሀቁን ለማወቅ ደግሞ ነገን መጠበቅ የለብንም። ተረጋግተን ወደፊት ለመሄድ፤ እውነቱ ወጥቶ ሁላችን በአንድ እንድንሰለፍ፤ በሥልጣን ላይ ያለው ክፍል ሕዝቡን ማዕከል ያደረገና ሁሉን አቀፍ ራዕይ ማራመድ አለበት። ይሄን የማጣራት ምርመራ፤ አዴፓ ወይንም የፌዴራሉ መንግሥት ብቻቸውን ካደረጉት፤ ጉዳዩ በትክክል እንዳይጣራ ይፈልጋሉ ማለት ነው። ትክክለኛ ወጥቶ መረጋጋት እንዲገኝ የባሕርዳሩም ሆነ የፌዴራሉ መንግሥት አመራር ከተቀበሉት፤ የባሕርዳሩን ጉዳይ፤ የዐማራው መንግሥት፤ ከአብን ጋር፣ በዐማራው ክልል ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲ መምህራን ጋር፣ ለሶስትዮሽ እኩል ለኩል የተውጣጣ መርማሪ ሽንጎ አቋቁሞ፤ ጉዳዩን በማጣራት፤ እውነቱን ለሕዝብ ግልጥ ማድረግ ያስፈልጋል። በዐማራው መካከል ማንም ክፍል ተገለልኩ የሚል ስሜት ካደረበት፤ መልሰን ከነበርንበት መነከር ብቻ ሳይሆን፣ የባሰ ሊከተል ይችላል። በሀገራችን በየቦታው የተቋቋሙት የነፃ አውጪ ግንባሮች ሕልውና የሚነግረን ይሄንኑ ነው። ተገለልኩ የሚል ስሜት ላለው አካል፤ ለብቻው መፍትሔ ፍለጋ መሮጥን ነው የሚያስከትለው።

ከግድያው ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የሌላቸው በየቦታው እየተለቃቀሙ የሚታሠሩት የዐማራ ልጆች፤ ይሄንን ስሜት ነው የሚይዙት። ረጋ ብሎ ሊታሰብበት ይገባል። አሁንም ደግሜ፤ እውነት የአዴፓ ወይንም የፌዴራል መንግሥቱ የግል ንብረት አይደለችም። ሕዝቡን ባጠቃላይ ማስተፉ ቢከብድም፤ የተደራጀውን የዐማራው ክፍል ማሳተፉ ለእውነት ያላችሁን ፈቃደኝነት ይገልጣል።

ለሌሎቻችን የማስተላልፈው የታወቀ ነው። ዐማራው አልፎለታል ከሚለው ጀምሮ፤ ዐማራው ሕልውናው አደጋ ላይ ነው እስከሚለው ድረስ ሊይዝ የሚችል ሰፊ የፖለቲካ መድረክ አለን። የዐማራ ሕዝብ ብዛትና ብስለት፤ ይሄን ማስተናገድ ይችላል። ይህ ደግሞ ጥንካሬ እንጂ ድክመት አይደለም። ስለዚህ፤ የፖለቲካ አመለካከታችን የተለያየ መሆኑ ሊያስጨንቀን አይገባም። የፖለቲካ አመለካከት ወቅትን መነሻ ያደረገ ነው። ሁላችን እንደምናምነው፤ የአሁኑ የዐማራ አንገብጋቢ ጉዳዮች፤ እስካሁን በትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር በዐማራነቱ የደረሰበት ግፍና በደል መዝጊያ ማግኘቱ፤ በተለይም የፖለቲካ ተሳትፎ መነፈጉ፣ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች መፈናቀሉና መባረሩ፣ አሁንም ንብረቱና መሬቱ እንደተነጠቀ መቀጠሉ፣ ባጠቃላይም ፍትኅ መጓተቱ ጎልተው ከሚታዩት ግንባር ቀደሞቹ ናቸው። ይህ ነው የዐማራው የአሁን ፖለቲካ፣ ይህ ነው የዐማራው የአሁን ጥያቄ! “የዘገዬ ፍትኅ ዘርፉ ከተጓደለ ፍትኅ ነው!” የሚል አባባል አለ። በራያ፣ በዋግ፣ በጠለምት፣ በወልቃይት፣ በጠገዴና በመተከል የተፈጸመውን የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ዐማራን የማጥፋት ክንውን አለማረም፤ አንድም ስህተት አይደለም ብሎ መቀበልን ያመለክታል፤ አለዚያም የትግሬዎቹን ነፃ አውጪ ግንባር መሪዎች ለማስደሰት አሁንም የሚጥር ክፍል እንዳለ ያሳያል። ይህ መረጋጋትን ከማስከተል አኳያ ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ ነው። ሰውን ቤትህ ግባና ተቀመጥ ማለት መረጋጋትን አያስገኝም። ደርግ እኔ ሁሉን አድርገዋለሁ እናንተ አርፋችሁ ተቀመጡ ብሎ ያደረሰውን በደል አልረሳንም።

የውጪሰው ኢትዮጵያዊ ዐማራዎች፤ በዚህ የማረጋጋት ሂደትና ከላይ ያነሳኋቸውን ጉዳዮች በትክክል ከመፍታት አኳያ ሀገር ቤት በሚደረገው ጥረት፤ እኩል ኃላፊነት አለብን። እናም፤ ዘላቂነት ያለውና ጀሮ አቅኝ የሆነ ተደማጭነት ለማግኘት፣ ደግሞም አመርቂ የሆነ የልማት ዕርዳት ለማድረግ፣ አንድ ጠንካራ ሁላችን ያቀፈ ስብስብ መፍጠር ያስፈልገናል። በየጉዳዮቻችን ብቻ ከመሰሎቻችን ጋር ተጠማጥመን መደራጀቱ ሩቅ አይወስደንም። በዐማራነታችን የዐማራውን ጉዳይ ባንድነት ልንነሳለት ይገባል። ከአምባገነንነት ነፃ የሆነ፣ ከወገንተኝነት የጸዳ፣ ከሙስና የተላቀቀና ለፍትኅና ለእኩልነት የቆመ መንግሥት ጊዜን በመጠበቅ ወይንም ሌሎች ያድርጉት በማለት አይገኝም። በሌላ በኩል ደግሞ፤ ሀገራዊ አንድነትን የሚስብክና በተግባር የሚያውል መንግሥት፤ የሕዝብን ተሳትፎ በደስታ ይቀበላል። ይህ የሚመጣው፣ እያንዳንዳችን በያለንበት፤ “እኔም ድርሻ አለኝ!” ብለን የየግል አስተዋፅዖዋችንን ስንጨምርበት ነው። እናም ለየብቻችን የምንጠራውን የስልክ ስብሰባ፤ በአንድነት በማድረግ፤ ምን ማድረግ እንደሚገባንና እንደምንችል እንነጋገር። የተወሰኑ ሰዎችን ለስልክ ስብሰባ ከጠራሁ በኋላ፤ ሌሎች ተመሳሳይ ጥሪ ሲያስተላልፉ ስለገጠመኝ፤ የኔውን ትቸዋለሁ። በዐማራው ዙሪያ የተሰባሰቡ ጥሪ ደርሶኝ አንዳንድ ቦታዎች ላይ ተሳትፌያለሁ። አሁንም የአንድነቱ ስለሚበልጥ፤ እባካችሁ በአንድነት እንስብሰብና፤ የዚህን ጉዳይ መከታተሉንና የወደፊቱንም እንነጋገር።

አክባሪያችሁ

አንዱዓለም ተፈራ

በውጪ የተቋቋመው የመላ ዐማራ ሕዝብ ድርጅት መሪ የነበረ