አረጋዊ በርሀ

በጄነራል ሰዓረ መኮንን እና ሜጀር ጄነራል ገዛኢ አበራ የቀብር ስነስርዓት ላይ ለመካፈል ወደ መቀሌ ያቀኑት የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር( ትዴት) መሪ አረጋዊ በርሀ (ዶ/ር) “የወጣቶች መንጋ” ባሏቸው ሰዎች ጥቃት እንደተሞከረባቸው ለቢቢሲ የመቀሌ ዘጋቢ አረጋግጠዋል።

ቢሆንም ግን “አካላዊ ጉዳት አልደረሰብኝም” ብለዋል።

የቀብር ስነስርዓቱ ላይ ለመገኘት የሰማእታት ሃውልት ደጃፍ ላይ ሲደርሱ ከውስጥና ከውጭ የነበሩት ወጣቶች “መግባት የለበትም” ብለው በመቃወማቸውና ጥቃት ለማድረስ በመሞከራቸው የክልሉ ፖሊስ ጣልቃ ገብቶ ሊታደጋቸው እንደቻለ ገልፀዋል።

የጄነራል ሰዓረ ቀብር አዲስ አበባ ሳይሆን መቀሌ ይፈጸማል

በሃየሎም ይምሉ የነበሩት ጄነራል ሰዓረ መኮንን ማን ናቸው?

ይህን ተከትሎም ግርግር በመፈጠሩ ወጣቶቹ በወረወሩት ድንጋይ የፖሊስ ኣባላት ላይ እንዲሁም መኪኖች ላይ ጉዳት እንደደረሰ ቦታው ላይ ተገኝቶ የነበረው የቢቢሲ ዘጋቢ አረጋግጧል።

ፖሊስ ግርግሩን ለመቆጣጠርም አስለቃሽ ጭስ ለመጠቀም ተገዶም ነበር።

ከግርግሩ በኋላ አረጋዊ በርሀ (ዶ/ር) ወደ ዞኑ የፖሊስ ጽህፈት ቤት የተወሰዱ ሲሆን፤ ማምሻውን በእንግዳ ማረፍያ ማሳለፋቸውንም ተናግረዋል።

‘ባዶ ስድስት’ የሚባል እስር ቤት ውስጥ ታስረዋል የተባለው ስህተት እንደሆነና ዛሬ ጧት ወደ አዲስ አበባ እየተመለሱ እንደሆነም ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ጉዳት የደረሰባቸው የፖሊስ አባላት በዓይደር ሆስፒታል ህክምና እያገኙ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል።