የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)

Ethiopian People’s Revolutionary Party (EPRP)

ሰኔ 20 ቀን 2011 ዓ. ም

መግደልና መገዳደል ይብቃን!!! ከሴራ ፓለቲካና ከድብብቆሽ እንውጣ!!
በባህርዳርና በአዲስ አበባ ቅዳሜ ሰኔ 15/2011 ዓ.ም. ስለደረሰው ጉዳት ከኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) የተሰጠ መግልጫ
ከትናንት ዛሬ፣ ከዛሬ ደግሞ ነገ ለኢትዮጵያና ለሕዝቧ የተሻለ ዘመን ይመጣል ተብሎ በሚታሰብበት በአሁኑ ጊዜ በባህርዳርና በአዲስ አበባ የተከሰተው ሁኔታ አስደንጋጭና አሳዛኝ ነው። እንኳንስ በአንድ የፖለቲካ ድርጅት አባላት መሀል በተለያየ የፖለቲካ መስመር ላይ በቆሙ ወገኖች መሀል እንኳ ከውይይትና ከሀሳብ የበላይነት ያለፈ ኃይልን የተከተለ የትግል ስልትን መጠቀም እንደማይገባ ወደመተማመን በተደረሰበት፣ የሰላማዊ ፖለቲካ ትግልን ባህል ለመገነባት በሚጣርበት ዘመን የተከሰተው ሁኔታ ለፖለቲካ ድርጅቶችም ሆነ ለኢትዮጵያ ሕዝብ አስደንጋጭ ነው። ኢትዮጵያና ሕዝቧ ሞልቶ የተረፈ እንግልትን አሳልፈን ከተፈጠረው የዴሞክራሲ ጭላንጭል ባሻገር ሰላማዊ ሕይወትን ለመኖር የምንናፍቅ፤ የተሻለች አገር ለልጆቻችን ለማውርስ ትልቅ ህልም ያለን ነን። እናም የተጀመረውን ለውጥ ማስቀጠል የሁላችንም ተግባር ሊሆን ይገባል። ኢትዮጵያ ከሚገባው በላይ ልጆቿ መስዋዕትነትን የከፈሉባት በደማቸውም የራሰች ሀገር ስለሆነች በምንም መልኩ ተጨማሪ የሕይወት መስዋዕትነት ሊከፈልባት አይገባም። ሀገራችን ዳግም ልጆች አባቶቻቸውንና እናቶቻቸውን ወላጆችም ልጆቻችውን በግጭትና በጦርነት እየተነጠቁባት የዋይታ ቤት ልትሆን አይገባትም። ከየአቅጣጫው የሚሰነዘረው የሰላማዊ ትግል አስፈላጊነት ንግግር በሚደመጥበትና የተፈረመው ቃልኪዳን ቀለሙ ሳይደርቅ ወደ ኃይል ተግባር የምንገባ ከሆንን ውጤታችን የብዙዎችን ተስፋ ማጨለም እንዳይሆን። በመሆኑም የተፈጠረው ክስተት ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን ሊወገዝ የሚገባው መሆኑን ኢሕአፓ ያምናል። ኢትዮጵያ ከእንዲህ ዓይነቱ አዙሪትና የሴራ ፖለቲካ መላቀቅ ይኖርባታል። ለዚህ ደግሞ፡ 1. በወገን ላይ እየተፈራረጁ ጥላቻን ማቋት፣ ጥላቻን ማስፋፋት መዛት፣ ወገንን ማስፈራራት ሊበቃ ይገባዋል፣

  1. ዜጋን መናቅ ጉልበትን፣ ሃይልንና ስልጣንን ተጠቅሞ ማፈናቀል፣ ከቀየው ማባረር፣ መበደል፣ መዝረፍ፣ ማጉላላት፣ መደብደብ፣ ማቁሰል፣ መበደል… ሊያበቃ ይገባዋል። በደል ቁርሾን ይፈጥራል፣ ቁርሾም ለበቀል ያነሳሳል፣
  2. የቆየነው በኃይማኖት፣ በዘር፣ በቋንቋ ተቧድነን እየተቋሰልን፤ እነሱና እኛ እየተባባልን ነው። ዛሬ የምንቃመሰው በብዙ አስርተ-ዓመታት ውስጥ ያቦካነውን እየጋገርን ነው። ክፉ ተግባር አንዱ ወገን ሲያደርገው ጥሩ ሌላው Phone :0251944223216 e-mail: eprp@eprp-ihapa.com

ሲያደርገው ደግሞ መጥፎ ሊባል አይገባውም። ማንም ይፈጽመው ምንጊዜም ይፈጸም ክፉ ተግባር መጥፎ ነው። ሁሌም ሊወገዝ ይገባዋል። ፍትኅና ዳኝነት ለሁሉም እኩል ሊሰጥ ይገባዋል።
አሁን የሆነው ሆኖ በአገራችን በተፈጠረው ክፉ ነገር መራራውን እውነት በመቀበል ተመሳሳይ ሁኔታ እንዳይደገም በሃቅ ላይ የተመሠረተ ምርመራ ሊደረግ ይገባዋል። የክስተቱን ትክክለኛ ምክንያት ማወቅ ሲቻል ችግሩን ከሥሩ ነቅሎ ለመጣል እንደሚቀል እሙን ስለሆነ በዚህ ረገድ ከመንግሥት ብዙ ይጠበቃል። በተጣራና በትክክልኛ መረጃ ላይ የተመሠረተ ጠንከር ያለ የሕግ የበላይነትን የማሰከበር እርምጃ መውሰድም የሂደቱ አንድ አካል መደረግ ይኖርበታል። እየተሄደበት ያለውን ሰላማዊ መንገድ ሊያጨናግፉ በሚሹለከለኩ አካላት ላይም ለኢትዮጵያና ለሕዝቧ ሲባል የማያዳግም ውሳኔ መስጠት ያስፈልጋል። በዚህ ረገድ ሕዝቡ ያልተድበሰበሰ መረጃ የመስማትና ፍትኅዊ ውሳኔ የማግኘት መብቱ ሊከበርለት ይገባል። ኢሕአፓ ለሟች ቤተሰቦችና ወዳጆች መጽናናትን ለኢትዮጵና ለሕዝቧ ሰላምና መረጋጋትን ይመኛል። እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!

Phone 0251944223216 e-mail: eprp@eprp-pa.ihapa.com