- 1 ጁላይ 2019

የኢትዮጵያ ህልውናና አንድነትን በሚመለከት መንግሥት ከሰላማዊው መንገድ ባሻገር አስፈላጊ ከሆነ የጦር መሳሪያን በማንሳት የሚፈጸሙ አፍራሽ ድርጊቶችን ለመከላከል አስፈላጊውን ሁሉ ከማድረግ ወደኋላ እንደማይል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚንስትሩ ይህን ያሉት የመንግሥትን የ2011 በጀት ዓመት እቅድ አፈፃፀም ሪፖርትን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡበት ወቅት ሲሆን በዚሁ ጊዜ “ለኢትዮጵያ አንድነት ግንባራችንን እንሰጣለን” ካሉ በኋላ “በኢትዮጵያ ህልውና የሚመጣ ካለ በእስክሪብቶ ሳይሆን ክላሽ ተሸክመን ለመዋጋት ዝግጁ መሆናችንን የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲገነዘብ እፈልጋለሁ” ብለዋል።
• “ሌሎችንም ከፍተኛ ባለስልጣናት የመግደል ዕቅድ ነበረ”
• “መደናገጥ ባለበት ወቅት ስህተቶች ሊያጋጥሙ ይችላሉ” አቶ ንጉሱ ጥላሁን
አክለውም “ለሕዝብ ማስተላለፍ የምፈልገው፤ ይህ ለውጥ እውነተኛ ለውጥ ነው። ይህ ለውጥ ኢትዮጵያዊያንን ወደ ብልጽግና የሚያወጣ ለውጥ ነው። በልበ ሙሉነት ልነግራችሁ የምፈልገው፤ እውነት ከእኛ ጋር ስለሆነ ማንም አያቆመንም። እውነትን ይዘን ስለምንሰራ የኢትዮጵያ አምላክ ያግዘናል” ሲሉ ተናግረዋል።
የተለያዩ ጉዳዮችን አንስተው ለምክር ቤቱ አባላት ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ፤ ከኢትዮጵያ ውጪ የሆነው ሐሰተኛና ግጭት ቀስቃሽ መረጃዎችን በማህበራዊ ሚዲያ በሚያስተላልፉ ሰዎች ላይ ምሬታቸውን ሲገልጹ ”እኔ እናንተን ለመቆጣጠር የምችልበት መንገድ ስለሌለኝ፤ የእውነት አምላክ እግዚአብሔር በእናንተ ላይ ይፍረድባችሁ ብቻ ነው የምለው” ሲሉ ገልጸዋል።
መፈንቅለ መንግሥት
ሰሞኑን መንግሥት በብርጋዴር ጄነራል አሳምነው ጽጌ የተሞከረው መፈንቅለ መንግሥት ነው ማለቱን ተከትሎ በርካቶች እንዴት መፈንቅለ መንግሥት በክልል ደረጃ ይደረጋል፤ ይህን ተግባር መፈንቅለ መንግሥት ብሎ መጥራቱ ትክክል አይደለም ሲሉ የሞገቱት ጥቂት አይደሉም።
ጠቅላይ ሚንስትሩም በዛሬው የፓርላማ ውሏቸው የተፈጸመው ጥቃት ”በኢፌዴሪ መንግሥት ላይ የተፈጸመ መፈንቅለ መንግሥት ነው” ብለዋል።
“በየትኛውም የፌደራል ሥርዓቱ ላይ የሚቃጣ ጥቃት የኢፌዴሪ ጥቃት ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ ”አመራር ገድሎ እና አግቶ ሲያበቃ፤ የመንግሥት ተቋማትን ከተቆጣጠረ በኋላ፤ ‘ለምን መፈንቅለ መንግሥት ትሉታላችሁ’ መባሉ ትክክል አይደለም” ብለዋል።
የሰሞኑ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ አድራጊዎች ከባህር ዳርና ከአዲስ አበባ ውጪ በቤኒሻንጉል ጉሙዝም ኃይል አሰማርተው እንደነበረ እና ከኦሮሚያ የተመለመሉ ”ገዳዮችን” ያካተት እንደነበረ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ተናግረዋል።

• “በዚህ መንገድ መገደላቸው ከፍተኛ የፀጥታ ችግር መኖሩን ያሳያል” ጄነራል ፃድቃን
• “ከፍተኛ ችግር ውስጥ ገብተናል. . . ግን እናሸንፋለን”
በተጨማሪም በመፈንቅለ መንግሥቱ ሙከራ ላይ ከወራት በፊት የጥቅማ ጥቅም ጥያቄ አለን ብለው የመጡ የሠራዊቱ አባላት መኖራቸውንም ተናግረዋል። ”መከላከያ አስሮ ገምግሞ ‘እነዚህ ወጣቶች ናቸው ይማራሉ’ ብሎ የለቀቃቸው በርካታ ወጣቶች ተሳታፊ ሆነውበታል” ብለዋል።
”እንዴት ሰው አምባቸው መኮንን ይገድላል?” በማለት የጠየቁት ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ ”አምባቸው እንኳን ልትገድለው፤ ልትቆጣው እንኳን የሚያሳሳ ሰው ነው” ሲሉ ገልጸዋቸዋል።
”ሰዓረ እንደ ሃበሻ ዳቦ ከላይ እና ከታች እሳት እየነደደበት፤ ጓዶቼን ቀብሬ የመጣሁባትን ኢትዮጵያን አላፈርስም ያለ ጀግናን እንዴት ሰው ይገድላል?” ሲሉ ጠይቀዋል።
የመንግሥት ፈተናዎች
ጠቅላይ ሚንስትሩ ባለፉት ወራት በመንግሥታቸውና አስተዳደራቸው ላይ ሆን ተብሎ በሌሎች አካላት የተከናወኑ ጥቃቶችንና ፈተናዎችን ዘርዝረዋል። ጠቅላይ ሚንስትሩ የጥቃቶቹን ዝርዝር በሰኔ 16 የቦንብ ፍንዳታ በማስታወስ ነበር የጀመሩት።
”ገና ሁለት ወራት እንኳ ሳይሆነን የጀመርነውን ለውጥ ለማጨናገፍ በአደባባይ የምታቁት ሙከራ ተደረገ” ያሉ ሲሆን፤ ከዚህ ሁለት ወር በኋላ ”በሶማሌ ክልል የኢትዮጵያን አንድነት የሚፈታተን ገንዘብ እና ትጥቅ ያለው የተደራጀ በሺህዎች የሚቆጠር አባላት ያለው ኃይል ችግር ፈጠረ። . . . እሱን ተሻግረን ሳንጨርስ የተደራጀ ወታደር ቤተ መንግሥት መጣ። በምትውቁት ሁኔታ እነሱን ከመለስን በኋላ በምዕራብ ኦሮሚያ በሦስት ወር መንግሥት እሆናለሁ ብሎ ምዕራብ ኦሮሚያን የሚያተራምስ ኃይል ተፈጠረ” ብለዋል።
• “ከጄ/ል አሳምነው ጋ በምንም ጉዳይ ያወራሁበት አጋጣሚ የለም” እስክንድር ነጋ
”ከቦታ ቦታ ዜጎቻችንን የሚያፈናቅሉ ኃይሎች ተፈጠሩ . . . አፈናቃዮች ብለው ዘፈኑብን። ተፈናቃዮችን ስንመልስ ደግሞ በኃይል መለሳችሁ አሉን” በማለት ከተፈናቃዮች ጋር የነበረውን የመንግሥትን ፈተና አስረድተዋል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ መንግሥት ያጋጠመውን ፈተና መዘርዘር ሲቀጥሉ፤ ”ጥቂቶች አውቀው፤ አብዛኛዎቹ ደግሞ ሳይገባቸው በሁለት እግር እንኳን መቆም ያልቻለችን ሃገር የደሞዝ ጭማሪ በሚል አንዴ መምህር አንዴ ደግሞ ሃኪም እያሉ ተደራጁብን” ብለዋል።
”ይህ ፖለቲካ ነው። ኢትዮጵያ የደሞዝ ጭማሪ የምትጠየቅበት ጊዜ አልነበረም” በማለት የደሞዝ ጥያቄው አግባብ አለመሆኑንና ፖለቲካዊ አንድምታ እንዳለው ጠቅሰው አልፈዋል።
ቁልፍ ቦታዎች በኦሮሞ ተይዟል
ቁልፍ የሚባሉ የመንግሥት የሥልጣን ቦታዎች በኦሮሞ ነው የተያዙት የሚለው አስተያየት ”ውሸት” ነው ሲሉ አጣጥለውታል ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ።
”የተከበረው ምክር ቤት፤ በእያንዳንዱ ተቋም ኦሮሞ ያልተገባ ሥልጣን ይዞ ከሆነ አጣርቶ ከእኔ ጀምሮ እርምጃ መውሰድ ይችላል” ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ “ኦሮሞ በአንድም ቦታ ያልተገባ ሥልጣን አልያዘም” ብለዋል።
የክልል እንሁን ጥያቄዎች
ጠቅላይ ሚንስትሩ የክልል እንሁን ጥያቄ በሕጋዊ መንገድ ምላሽ እስኪሰጥ ድረስ ህዝቡ በትዕግስት እንዲጠብቅ ጠይቀዋል። ”በደቦ እና በጩኽት የሚመለስ ነገር ለማስተናገድ ከእንግዲህ ትዕግስታችን አልቋል። ሁሉም ሥርዓት ጠብቆ ይሄዳል፤ በሥርዓት እንመልሳልን። ያን የማይጠብቅ ከሆነ በተለመደው መንገድ እናስተናግደዋለን።” ሲሉ ተደምጠዋል።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ የክልል እንሁን ጥያቄን ለመመለስ ሕገ-መንግሥቱም መሻሻል ይኖርበታል ብለዋል። ምዕራፍ አራት የመንግሥትን አወቃቀር በተመለከተ የሰፈረው መቀየር እንደሚኖርበት ጠቁመዋል።
የተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ስለመዋል
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለያዩ የወንጀል ተግባራት ላይ ተሳትፈዋል ተብለው የተጠረጠሩ ግለሰቦችና ቡድኖች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አመልክተው፤ በዚህም መሰረት ከሽብር ቡድን ጋር በተያያዘ 48፣ በተለያዩ ስፍራዎች ከተፈጸሙ ብሔርን መሰረት ባደረጉ ጥቃቶች የተጠረጠሩ 799 አመራሮችና የፀጥታ ኃይል አባላት እንዲሁም በኢኮኖሚያዊ ወንጀሎች የተጠረጠሩ 34 ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ለምክር ቤቱ ገልጸዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ በሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ውስጥ ተሳታፊ ሆነዋል የተባሉ 64 ተጠርጣሪዎችና በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ደግሞ 51 ሰዎች በሕግ አስከባሪዎች መያዛቸውን ጠቁመዋል።
የሐገር ውስጥ ተፈናቃዮች
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምክር ቤቱ በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች ስላጋጠሙት መፈናቀሎች አንስተው ማብራሪያ ሰጥተዋል። በዚህም ባለፉት ዓመታት ሁለት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ዜጎች እንደተፈናቀሉ አመልክተው ከዚህ ውስጥም ከመጋቢት 2010 ዓ.ም ጀምሮ አንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ሰዎች መፈናቀላቸውን ገልጸዋል።
ከተፈናቀሉት መካከል አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን የሚሆኑት የተፈናቀሉት በሚኖሩበት ክልል ውስጥ ሲሆን 800 ሺህ የሚሆኑት ደግሞ ይኖሩበት ከነበረው ክልል ተፈናቅለው በሌላ ክልል ውስጥ የሚገኙ ናቸው። ከአጠቃላዩ ተፈናቃዮች ውስጥ 400 ሺህዎቹ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ባጋጠሙ ችግሮች ከቀያቸው የተፈናቀሉ ናቸው።
ጠቅላይ ሚኒስተር ዐብይ ተፈናቃዮችን በተመለከተ መንግሥት ያከናወናቸውን ሥራዎች ጨምረው ሲገልጹ ከአጠቃላዩ ተፈናቃዮች ውስጥ ከሁለት ነጥብ አንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ወደ ነበሩባቸው ቦታዎች እንዲመለሱና እንዲቋቋሙ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሪፖርታቸው አክለውም ለእንዲህ አይነቱ መፈናቀል ምክንያት እንደሆኑ የሚጠቀሱትን በተለያዩ ቦታዎች የሚያጋጥሙ ግጭቶችን ለማስቆምና ዘላቂ ሰላምን ለመፍጠር መንግሥታቸው ትኩረት ተሰጥቶ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
የሐገሪቱ ኢኮኖሚ
የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በተመለከተም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለተወካዮች ምክር ቤት ያቀረቡት ሪፖርት ላይ እንዳመለከቱት ከ2008 እስከ 2009 ባለው ጊዜ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ 8 ነጥብ 8 በመቶ ማደጉን እንዲሁም ባለፈው ዓመት 7 ነጥብ 7 በመቶ እድገት ማሳየቱን ተናግረዋል።
አክለውም በዚህ ዓመት ያለፉትን አስራ አንድ ወራት አፈፃፀም መሰረት በማድረግ በ2011 ዓመተ ምህረት ኢኮኖሚው 9 ነጥብ 2 በመቶ ያድጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።