July 1, 2019 መጋቢት 20, 2011
የዚህ ጽሁፍ ዓላማ የሀገሬ ልጆች ኢትዮጵያውያን የአባቶቻችንን የግዕዝ ፊደላትን የመፍጠር መሰል የቀደምትነት ተመክሮ እንደ አርዓያ በመከተል ሀገር-በቀል የኢትዮጵያ ርዕዮተ-ዓለም ይነድፉ ዘንድ ለማበረታታት ነው። ይህ ማዘዣ አይደለም፤ ለውይይት መነሻ የሚሆን ጥቆማ እንጂ።

አባተ ካሣ
የበለፀጉ እና በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት በዓለም ላይ ይገኛሉ። አብዛኛዎቹ በአፍሪካ የሚገኙት በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ነፃነታቸውን የተቀዳጁት ገና በ1953ዎቹ የመጀመሪያ ዓመታት ነበር። ይሁንና ኢትዮጵያ፣ በሺህ ዓመታቶች የተመዘገበ ታሪኳ የምትኮራና ከአምሰት-ዓመት የጣሊያን ወረራ በቀር በዚያ ሁላ ዘመን ሁሌም ነፃነቷን የተጎናጸፈች ሀገር የነበረች ግን በማደግ ላይ ካሉት ሀገራት ጎራ ናት። 1966 በኢትዮጵያ የዘውዳዊ ሥርዓት (monarchy) ፍፃሜን እና የጥቂቶች ሥርዓት (oligarchy) ጅማሬን ያሳየ ዓመት ነበር። ሆኖም ከፖለቲካ ባህሏ አኳያ ዛሬ ላይ ለኢትዮጵያ ይበልጥ ተስማሚ የሚሆነው የፖለቲካ ሥርዓት፣ በተፎካካሪ ወይም ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዘንድ ሥልጣን የሚከፋፈልበት የብዙሃን ሥርዓት (polyarchy) ሊሆን ይችላል።
ለአንድ ሀገር ተስማሚ የልማት ሞዴል የማመንጨቱ ኃላፊነት በራሱ በሕብረተሰቡ ላይ ይውላል፤ ከራሱ ታሪክ እና ባህል እንዴት መማር እንደሚችል በመመርመርና በውስጥ እና በውጭ አካባቢ ሁናቴዎች ያሉትን እንቅፋቶች እና እድሎች ሙሉ በሙሉ በመረዳት ይሆናል። ስለሆነም የራሳችን ለሆነ ጉልብትና ስለሚበጅ አዲስ ዓይነት ሞዴል የተወሰኑ ቁልፍ እሳቤዎችን እስቲ እንገምግም።
ብዙዎቹ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ብሔራዊ ኢኮኖሚያቸውን ለማጎልበት የወሰዱት ሞዴል የበለፀጉ ኅብረተሰቦች የተከተሉትን ካፒታሊስት አልያም ሶሻሊስት ሞዴል ነው። ነገር ግን አብዛኛዎቹ አሁንም ድረስ በአስከፊ ድህነት እና በአሽቆልቋይ ኢኮኖሚ እየተሰቃዩ ይገኛሉ፤ ኢትዮጵያም ከእነርሱ የተለየች አይደለችም።
ይሁንና፣ ካፒታሊዝምም ሆነ ሶሻሊዝም አያሌ ያልተፈቱ ችግሮች አሉባቸው። እውቁ ጣሊያናዊ ጋዜጠኛ አሪጎ ሌቪ፣ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር ጥቅምት 30/1980 ታይምስ ኦፍ ሎንደን ላይ “Failure Cannot Shatter the Socialist Dream” በተሰኘ ጽሁፉ፣ ጉዳዩን እንደሚከተለው በግልፅ አስቀምጦታል፡-
ሶሻሊስቶች ገነት ስለሆናች አገር ያልማሉ፤ ሁልአቀፍ ብልፅግና ያለውና በዚያ ላይ ደግሞ ለግለሰቦች ፍፁም ነፃነትን የሚያጎናፅፍ መደብ-አልባ የእኩሎች ኅብረተሰብ ይመኛሉ። ይህቺ ገነት የሆነች አገር መቼም እውን ሆና አታውቅም።
የሶሻሊስት ህልም የጠንካራነቱ ኃያልነት እጅግ ምሁር የሆኑ ግን ደግሞ ለሶሻሊዝም የማርክሲስት ኃልዮት አሰቃቂ ውድቀት ፍፁም ጭፍንነትን ያዳበሩ ብዙ ሰዎች መኖራቸው ነው።
የማርክሲስት ሶሻሊዝም መትረፍረፍንም ሆነ እኩልነትን አልያም ነፃነትን ማቅረብ እንደማይችል አረጋግጧል። ስልተ-ምርት ሙሉ በሙሉ በመንግስት ቁጥጥር ስር መሆን ለሶሻሊስት ዩቶፕያ መሠረት ሊሆን ይችላል የሚለው ሀሳብ፣ ዛሬ ላይ ታሪካዊ የቁም-ቅዠት ብቻ ስለመሆኑ ገሀድ ወጥቷል።
የታሪክ ተሞክሮ እንዳስተማረን፣ የሶሻሊስት አወቃቀር መሠረት ማበጀት የሚችለው ለየተማከለ፣ አምባገነን ሥርዓት እና የሕዝብን ድምፅ የማያከብር የፖለቲካ ኃይል ብቻ መሆኑን ነው።
ሰርቶ-አደሩን በማኅበር የመደራጀት ነፃነቱን፣ ሸማቹን ደግሞ አማራጭ የማግኘት መብቱን ይነፍጋል። እጅግ አስከፊ የሆነ የአላቂ ሀብቶች ክፍፍል ሥርዓትን ያቀርባል። ፈጠራን አዝጋሚ ያደርጋል። ተቀዛቅዞ እስኪቆም ድረስ ኢኮኖሚውን ይጫነዋል።
እንደዚህ በግልፅ ስህተት በሆኑ እሳቤዎች ላይ ይህን ዓይነት የከረረ አቋም ሊኖር የቻለው ሌሎች እሳቤዎች በተመሳሳይ አጥጋቢ ሳይሆኑ በመገኘታቸው እውነታ ብቻ ነው።
በርግጥ በምዕራቡ ዓለም በአብላጫነት የሚተገበረው “ቅይጥ ኢኮኖሚ (mixed economy) ፣ የማኅበራዊ ዋስትና መንግስት (welfare state)” ሞዴል፣ ታላላቅ የታሪክ ስኬቶቹ እንዳሉ ሆኖ፣ ታላላቅ ስንክሳሮችን ባለማቋረጥ ያስከስታል፡- ግሽበት እና ሥራ-አጥነት፤ እንዲሁም ቅጥ-ያጣ ኢፍትሃዊነት እና የእኩልነት እጦት፣ ትርፍ አግበስባሽነት፣ እና ስግብግብነት ይገኙበታል።
ስለሆነም፣ ሁለቱም ሶሻሊስቶች እና ካፒታሊስቶች ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የተሻለ ቀመር በመፈለግ ላይ ይገኛሉ።
ሪቻርድ ኤል. ስክላር “Beyond Capitalism and Socialism in Africa” በተሰኘ ርዕስ በሞደርን አፍሪካን ስተዲስ ጆርናል (Journal of Modern African Studies, 26 (1988), pp. 14-15, 18) በካፒታሊዝም እና በሶሻሊዝም መካከል ባለው ‹ታላቅ ፉክክር› አስመልክቶ ባቀረበው እይታ ላይ፣ ንፅፅሮሹን እንደሚከተለው ያብራራዋል፡-
ዛሬ ላይ ጥቂት ታዋቂ ሶሻሊስቶች የሶሻሊዝምን “የልማታዊነት ብቃቶች” ከካፒታሊዝም ብቃቶች በላይ አድርገው ይመዝኗቸዋል፤ ጥቂቶቹ ደግሞ በኢንዱስትሪ ጉልብትና የመጀመሪያ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ማኅበረሰቦች የካፒታሊዝምን የአጭር-ጊዜ ጠቀሜታ ይሞግታሉ። በምትኩም ሶሻሊዝም እንደ ካፒታሊዝም ባለ የሠራተኛው ሕዝብ ልዩ መብት በተሰጠው መደብ በመጨቆን እና በመበዝበዝ ላይ በሚመረኮዝ የኢኮኖሚ ሥርዓት ላይ የሞራል የበላይነት አለው ብለው ይከራከራሉ። ሶሻሊዝም ክሽፈቶች ቢኖሩትም የርዕዮት እና የፖለቲካ ንቅናቄ እንደሆነ ቀጥሏል፤ ምክንያቱም ካፒታሊዝም በተናጠል ከማኅበራዊ ኢፍትሃዊነት ጋር ተዛምዶ ታይቷል። የግለሰብ የደህንነት ስጋት፣ የማኅበራዊ አደረጃጀት እጦት፣ እንዲሁም የከተማ ሥራ-አጥነት በአፍሪካ ውስጥ ያለው ካፒታሊዝም ህያው አጋላጮች ናቸው።
ለሦስት አስርት ዓመታት በአፍሪካም ሆነ በሌላ ቦታ በሚገኝ የሦስተኛው ዓለም በቆየው የሙከራ ጊዜ የማኅበራዊ ተሟጋቾች የሶሻሊዝም እክሎች ገጥመዋቸዋል። ለሶሻሊስቶች ሊማሩት ዘንድ የከበዳቸው ከባዱ ትምህርት ካርል ማርክስ ከማንም በተሻለ ያስተማረው ነው። በግልፅ ሲቀመጥ፣ ሀብትን (capital) ምንም አይተካውም፤ የኢኮኖሚያዊ ጉልብትና አቀሳቃሽ ኃይል እርሱ ነው። ለሶሻሊስቶች ሁለተኛው ትምህርት፣ ይህም ከማርክስ መማር የማይቻለው ትምህርት፣ ሶሻሊዝም ብቁ የሆነ የማበረታቻ ኃልዮት (theory of incentives) የሌለው ስለመሆኑ ነው።
ሲጠቃለል፣ ሶሻሊዝም ሀብት (capital) ያስፈልገዋል፣ እንዲሁም የማበራቻ ኃልዮት (theory of incentives) ይጎድለዋል፤ በሌላ በኩል ካፒታሊዝም መንግስት ያስፈልገዋል፣ እንዲሁም የማኅበራዊ ኃላፊነት ኃልዮት ይጎድለዋል። የአፍሪካ ሀገራት የኢኮኖሚ ሥርዓቶች ለአጠቃላይ ሚዛናዊ የኑሮ ሁኔታ የግል ሀብት፣ አግባብነት ያለው የመንግስት ተሳትፎ፣ ጠንካራ ማበራቻዎች፣ እንዲሁም ሕዝባዊ ኃላፊነት ያስፈልጓቸዋል። እነዚህ የማኅበራዊ እድገት መደበኛ መመዘኛዎች ሊሟሉ የሚችሉት በካፒታሊዝም እና በሶሻሊዝም ጥንቃቄ የተሞላበት ቅይጥ ብቻ ነው።
ጉዳዩ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ወይ የካፒታሊስት አልያም የሶሻሊስት ሞዴልን በፍፁምነት እንዲቀበሉ የሚወስናቸውን ገዳቢ የፖለቲካ አስተሳሰብ ትክክለኛነቱን መፈተን ነው። እኔ ኢትዮክራሲ (Ethiocracy) በሚል መጠሪያ የማቀርበው ሀሳበ-ዘ-መፍትሔ (proposal) ከሁለቱ ሞዴሎች ጥንካሬዎቻቸውን ጥቅም ላይ የሚያውል፣ ግን ደግሞ ድክመቶቻቸውን የሚያስወግድ ንፅረታዊ (relativistic) እና ተግባራዊ (pragmatic) አቀራረብን በማስተዋወቅ ያንን አስተሳሰብ ለመተካት ይሞክራል።
ደርግ እውነቱ ሶሻሊዝም ነው አለ። ህወሓት/ኢሕአዴግ ደግሞ የጐሣ ፌደራሊዝምን እንደ እውነት ይመለከታል። ሁለቱም ከግለሰብ ይልቅ ቡድን የሚያስቀድሙ ስርአቶች የተሳሳተ ፍፁምነትን ይከተላሉ። ስቴፈን ሃውኪንግ እንደነገረን ግን፣ “ከህዋ (universe) መሠረታዊ ሕጎች አንደኛው ምንም ፍፁም የሆነ ነገር የለም የሚለው ነው። ፍፁምነት (perfection) ከነጭራሹ የለም። ያለ ፍፁም-አልባነት ደግሞ አንተም ሆንክ እኔ አንኖርም ነበር።” ጽንፋዊ የሆነ የሶሻሊስት ኢኮኖሚ ፖሊሲ እንደ ኢትዮጵያ ላለ ለቅድመ-ኢንዱስትሪያዊ የግብርና ኢኮኖሚ አግባብነት እንዳልነበረው ታዝበናል። ገደብ-አልባ ካፒታሊዝምም ቢሆን አዋጪ አማራጭ ተደርጎ ሊወሰድ አይችልም።
የሶሻሊዝምን ከልማት ኃልዮት ረገድ መውደቅ እና የካፒታሊዝምን ከማኅበራዊ ኃላፊነት አኳያ ውድቀት ከግንዛቤ በማስገባት፣ ጥንካሬዎቹን ውጤታማ የሚያደርግና ድክመቶቹን አላስፈላጊ የሚያደርግ አንድ ተግባራዊነት ያለው የኢኮኖሚ ሥርዓት መምረጥ ይገባናል። የ‘ስልት/ግብ’ (means/end) አመክንዮአዊ መነሻ ንጽጽሮሹን ለማብራራት ይረዳን ይሆናል፡- ካፒታሊስት እንደ ስልት እና ሶሻሊስት እንደ ግብ። ሶሻሊዝም እንደፍልስፍና ‘እዝአዊ/directive’ ነው፤ ድልድዮችን አይገነባም ወይም እንጀራ አይጋግርም። ካፒታሊዝም እንደ ሳይንስ ‘ምርታማ/productive’ ነው፤ የልማት ኃልዮት ነው። የሶሻሊስት ስልተ-ምርት በከፍተኛ መጠን የእዝ ኢኮኖሚን ሲከተል፣ የካፒታሊስት ሞዴል ደግሞ የገበያ ፍላጎቶች ላይ ያተኩራል። የሶሻሊስት መንገድ የቡድናዊነትን (collectivism) ቅርፅ ሲወስድ፣ ካፒታሊስት ግላዊነት (individualism) ላይ አፅዕኖት ያደርጋል። የሶሻሊስት ሥርዓት የስልተ-ምርቱ ሕዝባዊ ባለቤትነትን ለማስፋት ቁርጠኝነት ሲያሳይ፣ ካፒታሊስቱ ሰፊ የግሉ ዘርፍ ባለቤትነትን ይመርጣል።
ኢትዮክራሲ በበኩሉ፣ ሀሳቦች እና ድርጊቶች በቀኖናዊ የርዕዮት ዓለም መስመሮች ሳይሆን፣ በጠቃሚ ውጤቶቻቸው የሚመዘኑበት ተጨባጭነትን (pragmatism) ይከተላል። የነፃ ገበያ ገፅታዎችን ከመንግስት ጣልቃ-ገብነት ጋር እንደወረደ ከሚያጣምረው ከቅይጥ ኢኮኖሚ ሞዴል በተለየ መልኩ፣ ኢትዮክራሲ የሁለቱንም የካፒታሊስት እና ሶሻሊስት እሳቤዎች ያካትታል፤ ነገር ግን እሳቤዎቹ እየተመረጡ የሚካተቱት በሥርዓቱ ክህሎት፣ መሠረተ-ልማትና ቴክኖሎጂ ላይ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ፣ የቡድን ሥራን በመደገፍ፣ ፉክክር እና ፈጠራን በማበረታታት፣ ዓለማቀፋዊ ትስስሮችን በማሳደግ፣ እንዲሁም የሀገር ውስጥ ቁጠባን እና የሀብት ምስረታን በማስተባበር ምርታማነትን የሚጨምር እድገት-ወዳድ የጋራ አስተሳሰብን (pro-growth mindset) የማስረፅ አቅም ላይ መሠረት በማድረግ ሲሆን፣ በሀቀኛ ዴሞክራሲ፣ በሕግ የበላይነትና ከሞራል አንፃር ትክክል በሆኑ እርምጃዎች ላይ በሚያተኩር በጠቃሚያዊነት (utilitarian) አሰራር የሚታገዝ ነው። ኢትዮክራሲ የዜጎችን ምሉዕ ተሳስትፎ ውጤታማ ለማድረግ የኢትዮጵያን ባሕላዊ እሴቶች ያቅፋል፤ ምክንያቱም “ባሕል ስትራቴጂን ቁርስ ስለሚያደርገው።” የፖለቲካ ሥርዓት ባሕልን ሳይሆን በተቃራኒው ባሕል የፖለቲካ ሥርዓትን መወሰን ስላለበትና የፖለቲካ ባሕል በአንድ የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ ለሚከናወን ሁሉም ነገር የመሠረት ድንጋይ በመሆኑ ምክንያት፣ ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ባሕል ይኸውም የፖለቲካ እርምጃዎች የሚወሰዱባቸውን ሁናቴዎች ከሚወስኑ መሠረታዊ የእምነቶች ሥርዓት፣ አመለካከቶች፣ እሴቶች እና ገላጭ ምልክቶች ጋር ተዛማጅነት ያለው ሥርዓት መንደፍ የግድ አስፈላጊ ይሆናል። እዚህ ላይ ኢትዮጵያ የፖለቲካ ባሕሏን በማጎልበት ረገድ ሺህ ዓመታቶችን የከፈለች ስለመሆኗ አፅንዖት መስጠት እፈልጋለሁ፣ እናም መሬት ላይ ያሉት እውነታዎች ፍፁም የተለዩ በሆኑባት ሀገር ላይ ፀጉረ-ልውጥ ተመክሮ መጫን አግባብ አይሆንም።
ፒዬሮ ጌሄዶ “Why is the Third World Poor” በተሰኘ መፅሐፉ ላይ እንደሚያስቀምጠው መከራከሪያ፣ መንፈሳዊው የልማት ፅንሰ-ሀሳብ ልማትን እንደ የሰው ልጅ እውነታ፣ ስለሆነም ቴክኒካዊ ወይም ኢኮኖሚያዊ ከመሆኑ በፊት በቀዳሚነት ባሕላዊ እንደሆነ አድርጎ ይመለከተዋል። የሚያድገው እና የሚጎለብተው ሰው በመሆኑም፣ ኢትዮጵያዊው ፈላስፋ ዘርዓ ያዕቆብ (1599-1692) እንዳለው፣ “ሰው የእራሱ ልማት ቀዳሚው አስፈፃሚ ነው።” እናም ልማት እውነተኛ እንዲሆን ከተፈለገ፣ ሕዝቦች መለወጥ እንዲቻላቸውና የተለያዩ የህይወት ሁናቴዎችን ይላመዱ ዘንድ ለሁሉም ሕዝብ ተስማሚ የሆኑ የባሕል እሴቶችን ሊያከብር ይገባዋል። የአንድ ሀገር ቁሳዊ እድገት ማንነቷን የሚወክለውን የቆየ ባሕሏን ለማጣቷ ክፍያ ሊሆን እንደማይችል ጌሄዶ በአፅዕኖት ያስቀምጣል።
የካፒታሊዝም እና የሶሻሊዝም፣ እንዲሁም የሊበራል ዲሞክራሲ እና የሶሻል ዲሞክራሲ መልካም ጎኖችን በማዋሃድ እኔ ኢትዮክራሲ በማለት የጠራሁትን አዲሱን የኢትዮጵያ የማኅበራዊ፣ የኢኮኖሚ፣ እና የፖለቲካ ፖሊሲ ታገኛለህ። ኢትዮክራሲ ማኅበራዊ ኃላፊነትን ያነገበ የገበያ ኢኮኖሚ፤ ሀገር-በቀል አዲሱ የኢትዮጵያ ርዕዮተ-ዓለም ነው። ኢትዮ የሚለው ኢትዮጵያን የሚወክል ሲሆን፣ -ክራሲ አንድ የመንግሥት ወይም የአገዛዝ ዓይነትን ይጠቁማል። ስለዚህም ኢትዮክራሲ ኢትዮጵያዊ የመንግስት ስርዓት መንገድ ነው፣ ምክንያቱም ሀገራችን የራሷን መቀየስ ይኖርባታልና! ኢትዮክራሲ የኢትዮጵያ እውነተኛ ዲሞክራሲ መገለጫና የሁሉንም ዜጎች እኩልነት፣ የግለሰብ ሰብዓዊ መብቶችን፣ እንዲሁም የሕግን የበላይነት ያገናዘበ በእውቀት ላይ የተመሠረተ ኢኮኖሚ ነው። ኢትዮክራሲ ዲሞክራሲያዊ ላልሆነውና ጐሣን መሠረት ላደረገው የፖለቲካ ኢኮኖሚ፣ለኢትዮዽያ ተስማሚ ላልሆነው የህወሓት/ኢሕአዴግ አብዮታዊ ዲሞክራሲ እና ልማታዊ መንግስት ፖሊሲ በአማራጭነት የቀረበ ነው። ልማታዊ መንግስት ሞዴል ለቻይና እና ለሌሎች የምስራቅ እስያ ሀገራት ሰርቷል፤ ምክንያቱም እነርሱ የጐሣ ፌዴሬሽን ፖሊሲ እራስ ምታት የለባቸውምና። ህወሓት/ኢሕአዴግ የተከተለው የጆሴፍ ስታሊን ጐሠኝነት ሞዴልን እንደመሳሪያ በመጠቀም የእከክልኝ-ልከክልህ ዜሮ-ድምር ፓለቲካ ነው። ጐሠኝነትን የመንግሥት ስልጣንን ለመቆናጠጥና የግል ሀብትን ለማካበት (ዝምደኝነት/cronyism እና ኪራይ-ሰብሳቢነት/rent-seeking) እንደ ስልት ተጠቅሞበታል።
ኢትዮክራሲ የኢኮኖሚ ዘርፉን በአራት ክለስተሮች ይመድባቸዋል፤ በተጠቃሽም በመንግስት ባለቤትነት ስር ያሉ፣ በግሉ ዘርፍ የተያዙ፣ በኅብረት ሥራ ማኅበራት የተያዙ፣ እና ሌሎች ድርጅቶች/ተቋማት።
(ሀ) የመንግሥቱ ዘርፍ እንደ መንገድ፣ ማረሚያ ቤት፣ የአየር ትንበያ፣ ፖሊስ፣ ፓስፖርት፣ ፖስታ ቤት፣ እና የመሳሰሉትን ሕዝባዊ መሠረተ-ልማቶችን ያቀርባል።
(ለ) የግሉ ዘርፍ በቅርበት በተያዘም ሆነ ይፋዊ ገበያ ላይ በሚቀርቡ አክሲዮኖች አማካኝነት በገበያ ኃይላት ቁጥጥር የሚደረግባቸው ምርት እና አገልግሎቶችን ያደርሳል።
(ሐ) በኅብረት ሥራ ማኅበራት የተያዘው የኢኮኖሚ ዘርፍ እንደ የግብርና ኅብረት ሥራ ማኅበራት ባሉ አቅራቢዎች ቁጥጥር ስር የሆኑ ተቋማትን ይመለከታል፤ ወይም በጋራ ባለቤትነት ስር እንዳሉ ኩባንያዎች ሌሎችም በደንበኞች ቁጥጥ ስር የሆኑ ኩባንያዎች፤ እንዲሁም ሌሎች በሠራተኞች ባለቤትነት እና ቁጥጥር ስር የሆኑ ተቋማት።
(መ) በባለቤትነት ያልተያዙት ሌሎች ደግሞ እንደ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች (NGOs)፣ ለንግድ ያልተቋቋሙ ድርጅቶች (NBOs)፣ እንዲሁም በማኅበራት ያልተያዙ ድርጅቶች (NCOs) ዓይነት የሆኑ ለትርፍ ያልተቋቋሙ ተቋማትን ያካትታል። የሙያ ማኅበራት፣ የንግድ ማኅበራት፣ በጎ አድራጎት ድርጅቶች፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ሆስፒታሎች፣ እንዲሁም ቀይ መስቀል የመሳሰሉት በዚህ ዘርፍ ውስጥ ይገኛሉ።
ለሶቭየት ሕብረት መፈራረስ መሠረታዊ ምክንያቶች ከነበሩት አንደኛው ሁሉም ነገር በመንግሥት ባለቤትነት መያዙ ነበር። ስኬታማ ለመሆን አራቱንም የባለቤትነት ቅርፆች በስፋት ጥቅም ላይ የማዋል አመዛዛኝ እርምጃ መውሰድን ይጠይቃል። ገበያን ለመተካት ከሚጥሩ መንግሥታት ይልቅ ገበያ የሚፈጥሩ መንግሥታት እድገትን በማፋጠን ረገድ ይበልጥ ስኬታማ ናቸው። በነገራችን ላይ፣ የመንግሥት ተሳትፎ ፈጠራን ያቀጭጫል የሚለው ከፍተኛ ተቀባይነት ያለው የካፒታሊስት ምልከታ ይኑር እንጂ፣ በቻይና የሚታየው ይህ አይደለም።
ማኅበራዊ ኃላፊነትን ባነገበው የኢትዮክራሲ የገበያ ኢኮኖሚ፣ የፍቅር እና እንክብካቤ ፍልስፍናዎች በፉክክራዊ ገበያ ላይ ከተጣበቁት የስግብግብነት እና ራስ-ወዳድነት ፍልስፍናዎች ጋር ይማዘናሉ። አክራሪ የነፃ-ገበያ አቀንቃኞች (Market fundamentalists) የጋራ ጥቅም በተሻለ ሁኔታ እውን የሚሆነው ያለ ምንም ገደብ የራስን ጥቅም በማስጠበቅ ነው የሚል የተሳሳተ እምነት አላቸው። ገበያዎች ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍልን (distributive justice) ለማምጣት የተነደፉ አይደሉም። ለምሳሌ፣ የግል ኮርፖሬሽኖች የሥራ ዕድል መፍጠርን ዓላማ አያደርጉም፤ ትርፍ ለማምጣት (በተቻለ መጠን ጥቂት እና በርካሽ ዋጋ) ሰዎችን ይቀጥራሉ። የንግድ ተቋማት የሚፎካከሩት ለማትረፍ ነው፣ ፉክክሩን ለማስቀጠል አይደለም፤ እንዲያውም ቢቻላቸው ሁሉንም ተፎካካሪዎች ከነጭራሹ ያስወግዱ ነበር። ኢትዮክራሲ ከጂዲፒ (GDP) ይበልጥ ስለአዕምሮ ጤና እና ስለሕጻናት ድህነት ይጨነቃል።
ከቀኖናዊ ግትርነት ይልቅ፣ ኢትዮክራሲ ተጨባጭነት ያለው ተለዋዋጭነትን (flexibility) ይከተላል። ኢትዮክራሲ ፍፁማዊውን የመንግሥት ዓይነት እሳቤ ይቃወማል። ፍፁም (perfect) ባልሆነ ዓለም ውስጥ ፍፁም መንግሥት ሊኖር አይችልም፤ ውዳቂውንም (mediocrity) ዝም ብለን መቀበል የለብንም። ኢትዮክራሲ የንግድ ዓይነት ተጨባጭ የኢኮኖሚ አመራር ስልትን ይከተላል። ለዜጎቹ ጥበቃ፣ ፍትሕ እና ምርጥ መንግሥታዊ አገልግሎቶችን በተቻለ መጠን በጣም በዝቅተኛ የሀብት ወጪ ለማቅረብ የሚተጋ እየላቀ የሚሄድ መንግሥት መመዘኛዎችን ነድፎ ያቀርባል። ለለውጥ የተቃኘ ስለሆነና በርዕዮት-ዓለም ስንክሳሮች እንዳይደናቀፍ ዕድል ስለማይሰጥ፣ ኢትዮክራሲ መንግሥታዊ ልህቀትን እውን በማድረግ ጉዞው የተሻሉ መመዘኛዎች በማሳካት ሕዝባዊ አገልግሎት እያሻሻለ ይቀጥላል። ከሃይማኖት በተለየ መልኩ፣ በኢትዮክራሲ የፖለቲካ ኢኮኖሚ እሳቤዎች ምንጊዜም በለውጥ ሂደት ላይ ሲሆኑ፣ ለግትር ርዕዮት ቦታ የለውም። ኢትዮክራሲ ለትግበራ እና ውጤት፣ ለባለሙያ እውቀት፣ እንዲሁም በሁሉም ወገን አሸናፊነት (win-win) ትብብር አማካኝነት እውን ለሚሆን የጋራ ጥቅም አስፈላጊነት ትልቅ ዋጋ ይሰጣል።
ኢትዮክራሲ ከሁለቱም ከካፒታሊዝም እና ከሶሻሊዝም ነቅሰን ብናስቀራቸው ጠቃሚ የሆኑትን ንጥረ-ነገሮች የሚያቅፍ አማራጭ (flexible)፣ ፈጠራዊ፣ እና ኢ-ቀኖናዊ አካሄድን በመከተል የአንዲት ደሃ ሀገርን ‘መሠረታዊ ፍላጎቶች’ ለማሟላት ይጥራል። በዚህም ጥግ-ደረስ የሆነ የካፒታሊዝምም ሆነ የሶሻሊዝም ፖለቲካን ውድቅ ያደርጋል። በሌላ አገላለፅ፣ኢትዮክራሲ አንዱን ከሌላው የመምረጥ ቀኖናዊ እና ግትር አካሄድ ለታዳጊ ኅብረተሰብ የማይገባ ወይም ገዳቢ እንደሆነ አድርጎ ይመለከተዋል። በኢትዮክራሲ ፋይዳ ላለው ሥራ ቅድሚያ የሚሰጥ መንግሥት፣ ለልማት የተነሳሳ አስተሳሰብ፣ አሳታፊ ዲሞክራሲ፣ ሕገ-መንግሥታዊ አወቃቀር፣ መልካም አስተዳደር፣ እንዲሁም በምርጫ መሳተፍ የዜጋዊ ኃላፊነት ሆኖ ምርጫዎችም በሳምንቱ መጨራሻ የእረፍት ቀናት የሚካሄዱባቸው ቢሆኑ የሚመርጥ እና እነዚህ ስርዓቶች በኢትዮጵያ ውስጥ የመንግሥት መሠረታዊ ደንቦች ሆነው እንዲያገለግሉ ያሳስባል።
በድሮው የፍፁም ዘውዳዊ አገዛዝ፣ እንዲሁም በዛሬው የአንድ-ፓርቲ የበላይነት ሥርዓት ላይ በፖለቲካ እና በአስተዳደራዊ ተቋማት መካከል የአስተዳደር ጉልብትና አለመመጣጠን ይታያል፤ የአለመመጣጠኑ ሚዛን ለኋለኛው ባደላ መልኩ። ስለሆነም እንደ ሕግ አውጪ እና የፖለቲካ ፓርቲዎች የመሳሰሉትን የመንግሥታዊ አስተዳደር ሥርዓትን ግንባታ ዋና ዋና አካላት ለማጠናከር በአግባቡ የተነደፉ የተቋማት አቅም ግንባታ ፕሮግራሞችን የመጀመሩ አስፈላጊነት ከፍተኛ ነው።
የፋሺስት አምባገነን (የጣሊያኑ)፣ ንጉሣዊ አምባገነን፣ ወታደራዊ አምባገነን፣ የሠርቶ-አደር አምባገነን፣ እንዲሁም የአንድ-ፓርቲ አምባገነን ሥርዓቶች በተከታተል ለኢትዮጵያ ድህነትን እና ስቃይን አትርፈዋል። ኢትዮክራሲ በመባል በቀረበው ማኅበራዊ ኃላፊነትን ባነገበው የገበያ ኢኮኖሚ መንግሥት ሥልጣኑን የሚያገኘው ነፃ በሆነ እና በተደጋጋሚነት በሚካሄዱ ምርጫዎች አማካኝነት ከሕዝቡ በተገኘ ፈቃድ ነው። የመንግሥት ሥልጣን መቆጣጠሪያዎቹ የሦስቱ መንግስት አካላት መዛኙ ቁጥጥር (check-and-balance system) ፣ በነፃ ፕሬስ ልጓም ቁጥጥር፤ እንዲሁም የፖለቲካ አመራር አባላቱ ከተፎካካሪ/ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ሲመረጡ ነው። በተጨማሪም አዲሱን ሕገ-መንግሥት የምናውጀውና የምናቋቁመው አንድ አውራ-ፓርት ሳይሆን እኛ ዜጎቹ ስንሆን ብቻ ነው። ከ86 ብሔሮች የተውጣጡትና በግምት 123 የሚሆኑትን ቋንቋዎች የሚናገሩ ግን አንድ የጋራ አማርኛ የሥራ ቋንቋ ያላቸው የዛሬይቱ ኢትዮጵያ 110 ሚሊዮን ሕዝቦች ለረዥም ጊዜ በሕብር ኖረዋል፤ ማለትም እኛ ኢትዮጵያውያን ለዘመናት የመደመር ታሪክ ያለን ሕዝብ ነን። የህወሓት/ኢሕአዴግን የፖለቲካ አጀንዳ ለማስፈፀም የተነደፈው አሁን የሚገኘው ጐሣ-ተኮር ፌደራሊዝም ሕገ-መንግሥት፣ የሰላማዊ አብሮነት የባሕል እሴቶችን ከማበረታታት ይልቅ ‘የእርስ-በርስ ግጭቶችን’ የሚያቀጣጥል መለያየትን እያስፋፋ በመሆኑ፣ ሊሻሻል ወይም በሌላ ሊተካ ይገባል።
የፖለቲካ ለውጥ ያለ የኢኮኖሚ ለውጥ ለሕዝቦች ምንም ማድረግ በማይችሉት ጉዳይ ላይ ቅሬታ የማቅረብ ነፃነት ብቻ ነው የሚሰጠው። ስለዚህም የቀመሩን የኢኮኖሚ ክፍል ይበልጥ እናብራራ። አዲሱ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ፖሊሲ የምግብ አመራረትን በማሳደግና ርሃብን በማስወገድ ላይ ማነጣጠር ይኖርበታል። ይህን ለማድረግም ማኅበራዊው በጀት ከወታደራዊው በጀት በጉልህ መጠን የበለጠ መሆን አለበት፤ ሆኖም ይህ የሚሆነው የሀገሪቱን ደህንነት አደጋ ላይ በማይጠል መልኩ እንደሆነ ሲረጋገጥ ነው። ይህ ፖሊሲ ግብርናን፣ የጥሬ-እቃ ምርትን፣ እና ቀላል ኢንዱስትሪን በመደገፍ የሚጀምር የተመጣጠነ ልማት (balanced development) ላይ ያተኩራል። አዲስ ትኩረት ሊሰጠው የሚያስፈልገው ወደ ውጭ የመላክ አቅምን አሳድጎ የውጭ ንግድ ገቢን ለማረጋገጥና የውጭ ቴክኖሎጂዎችን ለመግዛት እንዲቻል እንደ ስኳር፣ ጥጥ፣ ቆዳ እና ቡና ኢንዱስትሪዎች ባሉ ፋይዳ ጨማሪና (value-added) ግዙፍ የሰው ኃይል የሚጠቀሙ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ልማት ነው።
የብድር ዕዳ የጂዲፒ 59% መሆን ልማትን ከባድ ያደርገዋል። አዲሱ መንግሥት በውርስ ለሚረከበው ተንጠልጣይ ዕዳ፣ የብድር ማቅለያ ዐቅድ (debt relief scheme) መንደፍ አስፈላጊ ነው። አዲሱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ሁለተኛው የዓለም ጦርነትን ተከትሎ ከተተገበረው ማርሻል ፕላን ወይም የአውሮፓን ማገገሚያ ፕሮግራም ጋር ተመሳሳይ የሆነ የካፒታል ፍሰትን የሚያመጣ የገንዘብ አቅርቦትን ከወዲሁ ያስብበታል። እንዲህ ያለው የመልሶ-ግንባታ ስትራቴጂ ዛሬ ላይ ለኢትዮጵያ አስፈላጊ ሊሆን ይችላል፤ ምክንያቱም ለዚህ የሚያስፈልጉት አብዛኛዎቹ መዋቅሮች እና ተቋማት እንዳሉ አሉ ወይም ሊጠገኑ/ሊዘጋጁ ይችላሉ።የገበያ ፍላጎትን (demand) እንዲያንሰራራ ለማድረግና በዚህም የኢኮኖሚ ማገገምን ለማሳካት የመንግሥት የግዢ ወጪዎችን መደገፍ እንዲያስችል የገበያ ፍላጎት-ተኮር የሥራ አመራር ስትራቴጂን መንደፍ ያስፈልጋል። እንዲህ ዓይነቱ ስትራቴጂ የተፈለገውን ውጤት እንዲያመጡ የታለሙ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችን ይበልጥ በማጥራት ከማስተካከያ እና ከማስቀጠያ ምልከታዎች መካከል እያማረጠ በሚጓዝ የበጀት ዓመት ፖሊሲ መደገፍ ይኖርበታል። ከዚህ አኳያ ሊተገበሩ የሚገባቸው የአጠቃላዩ የኢኮኖሚ ፖሊሲ መመሪያዎች እነዚህን ያካትታሉ፡- የምርታማነት መጨመርን ለመደገፍ እና የመግዛት አቅምን እውን ለማድረግ በሥራ ቅጥር አልያም ደግሞ ያለሥራ ቁጭ ብሎ የነበረውን የሰው ኃይል በሕዝባዊ የሥራ ፕሮግራሞች ላይ በማሳተፍ የሰው ሀብትን ስምሪት፤ ዘላቂ የቱሪዝም እድገት መገንባት፣ የዘላቂ ውጤት መዋዕለ-ነዋይ ፍሰት (impact investing – ይህም ለሕዝብ መልካም ሁኔታን ለሚያበረክቱ ለማኅበራዊ እና ለአካባቢያዊ ተፅዕኖዎች መጨነቅን የመሳሰሉ ለማኅበረሰቡ በጎ የማድረግ ሥራዎችን በተጓዳኝ እያከናወኑ ዘላቂ የገንዘብ ትርፍን ማሳካት)፤ እና ለጂዲፒ እድገት ወሳኝ የሆነውን ቁጠባን ማበረታታት።
መፃኢ ጊዜያችንን ለመተንበይ የተሻለው መንገድ መፃኢ ጊዜያችንን እራሳችን መፍጠር ነው። አዲሱ በእውቀት ላይ የተመሠረተው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ፖሊሲ በተግባር ለሚገኙ መሠረታዊ ፍላጎቶች እና ለሕዝቦች ተስፋ ምላሽ መስጠት የሚኖርበት ሲሆን፣ ሀገሪቱ በስፋት የተንሰራፋውን ርሃብ፣ በሽታን፣ እንዲሁም መሃይምነትን በ2031 ዓ.ም. እንደምትቆጣጠር ያቅዳል።
የመሬት ስሪት ማሻሻያ፡ አለምነህ ደጀኔ እንደሚለው፣ በኢትዮጵያ ውስጥ መሬት በአንፃራዊነት በብዛት ይገኛል፤ ከ75 እስከ 85 ሚሊዮን ሄክታር የእርሻ መሬት ኢትዮጵያ አላት። ከአርሲ የተገኙ ጥናቶች ለአብዛኛው ገበሬ ውጤታማ ግብርና ለማካሄድ በነፍስ-ወከፍ 5 ሄክታር መሬት አግባብነት ሊኖረው ይችላል የሚለውን የደሳለኝ ራህማቶን ጥናት ይደግፋሉ። በኢትዮጵያ ለረዥም ዘመን የቆየውን መሬትን በግል ባለቤትነት የመያዝ ባህል ከግምት በማስገባት፣ እንዲሁም የግብርና ዘርፉን ዳግም እንዲያንሰራራ ለማድረግ፣ በግብርና የሚተዳደሩ ቤተሰቦች የእርሻ መሬት የግል ባለቤትነት ሊፈቀድላቸውና ምርታቸውንም በነፃ ገበያ መሸጥ እንዲችሉ ሊደረግ ይገባል። አዲሱ የግብርና ፖሊሲ አዲስ የሆነ የ‘መሬት ለአራሹ’ መርሀ-ግብር እውን በማድረግና በሁሉም ከአጭር-ጊዜ የዝቅተኛ ብድር አቅርቦት ጋር በተያያዙ ዋጋዎች ላይ ቁጥጥርን በማንሳት ላይ ሊያነጣጥር ይገባል። እድገቱ እየጨመረ ያለውን የኢትዮጵያን ሕዝብ ለመመገብ፣ የግብርና ምርታማነት መሻሻልን ይጠይቃል። ስለሆነም ድህነትን ወደሚቀጥለው ትውልድ ላለማስተላለፍ፣ በበሬ ከማረስ ዘመናዊ የግብርና ተስማሚ ቴክኖሎጂን ተቀብሎ ወደመተግበር የሚደረግ ሽግግር ቅድሚያ የሚሰጠው ብሔራዊ እንቅስቃሴ ሊሆን ይገባል።
መንግሥት በሕግ የሚቆጣጠረው ነገር ግን ግለሰቦች በባለቤትነት ይዘውት የሚያንቀሳቅሱት የገበያ ሥርዓት፣ ከሁለቱም ዓለማት ምርጦቹን ተመክሮዎች ያጣመረ ስለመሆኑ እውቅና ሲሰጠው ቆይቷል። ከማትረፍ ዓላማ እና ከፉክክር/ከውድድር አነቃቂነት ጋር በተያያዘ የግሉ ዘርፍ ባለቤትነት ምርታማነትን ሲያበረክት፣ የመንግሥት የገበያ ሕጋዊ ክትትል መኖር ደግሞ ከትርፍ ጎን-ለጎን ለሕዝቡ አገልግሎት እና ደህንነት ተደራሽ ስለመሆናቸው ያረጋግጣል። አንድ ንግድ በኪሣራ መንቀሳቀስ ወይም ትርፍ ባለማስገኘት ቢቀጥል ከነጭራሹ መኖሩን እንደሚያቆም ሁሉ፣ ትርፍ እንደ ወሳኝ መስፈርት ተደርጎ እውቅና ሊሰጠው ይገባል፤ ምክንያቱም የንግድ ብልፅግና ለአንድ ሀገር ህልውና መሠረታዊ ነው። በተጨማሪም የመንግሥትና-የግል ትብብር/ሽርክና (public-private partnership – PPP) ፅንሰ-ሀሳብ በመሠረተ-ልማት ፕሮጀክቶች ይጠቅም እንደሆን የፋይዳ ትንታኔ (value-for-money – VfM) ልዩ ጥናት ማድረግ ተገቢ ይሆናል።
ኢትዮክራሲ የሕዝቡን መሠረታዊ ፍላጎቶች ከመንግሥት በላይ ገበያው በተሻለ መመዘን ይችላል የሚለውን የኢኮኖሚ ንቡር ኃልዮት (classic economic theory) የሚቀበል ሲሆን፣ በተጨማሪም አንዳንድ ነገሮች በጣም ወሳኝ ከመሆናቸው የተነሳ ለማያስተማምነው ለገበያውውሳኔ መተው መልካም እንዳልሆነም ያምናል። ገበያም ሕግ ከሌለ ሌብነትን ይጋብዛል። ስለሆነም የሕዝቡን መሠረታዊ ፍላጎቶች እና የግሉን ዘርፍ የሚያገናኝ አካል ለማቅረብ ከመንግሥት የሆነ ዓይነት ማኅበራዊ ቁጥጥር ይጠበቃል። የግሉ ኢንዱስትሪ ተመጣጣኝ ትርፍ የማግኘት መብት አለው፤ ሆኖም ሠራተኞቹም ጤንነታቸው እና ደህንነታቸው የመጠበቅ መብት አላቸው፤ ሸማቹ አደገኛ ያልሆነ እና በአግባቡ የተመረተ የምርት ዕቃ የማግኘት መብት አለው፤ እንዲሁም ሕዝቡ አየር፣ ውሃ እና ደረጃውን የጠበቀ ሕይወት የመኖር መብቱ የተጠበቀ መሆን አለበት። የማይታየው እጅ የሚባለው የገበያ ኡደት ለሁሉም ነገር መፍትሔ ሊያቀርብ አይችልም፤ መንግሥት ጥያቄ ወይም ክስተት የማይጠብቅ (proactive) እንዲሆን እና ለከተሞች፣ ለአየር ንብረት ለውጥና ለከባቢ ሁናቴ ኃላፊነትን መቀበል ይኖርበታል። ኢትዮጵያ አሁን የምትገኝበትን ሁኔታዎች ከግምት በማስገባት፣ በግራ ከሶሻሊዝም ግድፈቶች እና በስተቀኝ ከልቅ ካፒታሊዝም መሀከል በመሆን የኢትዮክራሲ ተጨባጭ አማራጭ ይበልጥ ተስማሚ ሊሆን ይችላል።
ኢትዮክራሲ የግል ኢንዱስትሪው በተሻለ ሊከውነው የሚችለውን መንግሥት ሊሠራው አይገባም በሚል መርሆ መሠረት የግል እና የመንግሥት ባለቤትነቶች ጎን-ለጎን በሚኖሩባቸው ፖሊሲዎች ላይ የተግባር ሙከራ ማድረግን ይፈቅዳል። የግል ባለሀበቶች መተማመኑ እንዲኖራቸው መንግሥት ቁጥጥር እና የሕግ ማዕከፎችን (frameworks) የማቋቋም ኃላፊነት ሊጣልበት ይገባል። የሚፈለገው የሁለቱም ጤናማ የመንግሥት ዘርፍ እና ጤናማ የግሉ ዘርፍ መኖር ነው። ስለሆነም ኢትዮክራሲ የመንግሥት ባለቤትነትን በሚከተሉት ሁኔታዎች ላይ ይፈቅዳል፡- (ሀ) ለሁሉም አስፈላጊ በሆኑ እንደ ትራንስፖርት እና ውሃ ዓይነት አገልግሎቶች፤ (ለ) ለሌሎች በአግባቡ መንቀሳቀስ አስፈላጊና መሠረታዊ በሆኑ እንደ ኢነርጂ እና ኤሌክትሪክ ያሉ ቁልፍ ኢንዱስትሪዎች፤ (ሐ) አዲስ ኢንዱስትሪ ለማቋቋምም ሆነ የድሮውን ለማዘመን ከፍተኛ ካፒታል የሚጠይቁና መንግሥት በራሱ ካፒታሉን ሊያመነጭ በሚችልባቸው አንዳንድ ትግበራዎች፤ እንዲሁም (መ) ሞኖፖል አግባብ በሚሆንበት ጊዜ፣ ለምሳሌ ኃይል ማመንጨት፤ ምክንያቱም ሕዝቡ በመንግሥት በኩል ባለቤት በመሆን ከፍተኛውን ቁጥጥር ሊይዝ የሚችልበት ዓይነት ዘርፍ በመሆኑ።
ዛሬ በኢትዮጵያ ያለው ገዢ ፓርቲ ፖለቲካውን ከመምራት ባሻገር፣ በቴክኒካዊ እና በኢኮኖሚያዊ የማምረት ሥራ አመራር ላይም በቀጥታ ተጠምዶ ይገኛል። የፖለቲካ ፓርቲ ቢሮክራሲው ቅጥ-ያጣ ጣልቃ-ገብነት በመንግሥት ኤንተርፕራይዞች ከዳይሬክተሮች ቦርድ ጋር እስከሚስተካከል ሚና ድረስ የተለጠጠ ነው። የፓርቲ የበላይነት መተማመንን (confidence) ያከስማል፣ እንዲሁም የመንግሥት ኃላፊዎችን እና የኤንተርፕራይዝ መሪዎችን ተነሳሽነት ይገድባል። ስለዚህም ከሁሉም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እና የማምረቻ ተቋማት የፓርቲ ተወካዮች ሊወገዱ ይገባል።
ድህነት የግድ የግል ውድቀት ማሳያ ላይሆን ይችላል። ዝቅተኛ ተከፋይ፣ ሥራ-አጥ፣ ወይም የአካል ጉዳት ያለባቸው ሠራተኞች ከእነርሱ ባልመነጨ ጥፋት የተረጂነት እድል ሊገጥማቸው ይችላል። እንዲህ ላለ ጊዜ ነው መንግሥት ለሠራተኞች ገቢ ድጋፍ የማድረግ ኃላፊነት ያለበት፤ ይህም እንደ ችሮታ ሳይሆን እንደ ማኅበራዊ ፍትሕ መቆጠር ያለበት። ከኢኮኖሚው ደረጃ ጋር ተመጣጣኝ የሆነ ሁል-አቀፍ የማኅበራዊ ዋስትና ሥርዓት ሊዘረጋ ይገባዋል። ኢትዮክራሲ በጠንካራ የሥራ ሥነ-ምግባር እና በኢትዮጵያዊያን የይቻላል መንፈስ ላይ መሠረት ያደረጉ የራስ-አገዝ የገጠር ማኅበረሰብ ልማት ፕሮግራሞችን ያበረታታል።
ከተቋማዊ አቅም ግንባታ ረገድና በተቋማዊ አፈፃፀም ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ለማሳደር፣ እውቀት እና ክህሎት ለመንግሥትም ሆነ ለኤንተርፕራይዝ ከምንም በላይ ዋጋ ያለቸው እና አስተማማኝ ሀብቶች ናቸው። የአመራር ጉልብትና ለኢትዮጵያ መፃኢ ጊዜ የሚፈስ መዋዕለ-ነዋይ ይሆናል፤ እንዲህ ያለው የሥልጠና ወጪ ለኢትዮጵያ ከፍተኛውን የገንዛብ-ፋይዳ (value-for-money) ትርፍ ማረጋገጥ የሚችል ቀላል የመሠረተ-ልማት መዋዕለ-ነዋይ ፍሰት ነው። ስለዚህ የኢትዮክራሲ አዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ፍልስፍና ሰብዓዊ ካፒታልን የማፍራት አቅም ያለው ሰውን ማዕከል ያደረገ ይሆናል። የማይቋረጥ ማሻሻያ ትግበራ ባህልን (continuous improvement culture) በንግድ ተቋምም ሆነ በመንግሥት ሥራ ላይ አጣጥሞ ተፈፃሚ በማድረግ፣ በኢትዮጵያ በአመራር ቦታ ላይ የሚገኙ ሰዎች ሥራን የተሻለ፣ ፈጣን እና ፋይዳዊ (better, faster, and leaner) በማድረግ ሀብትን በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል ይቻላቸዋል። እውቀት የኢኮኖሚ እድገትን የሚያሽከረክር ሞተር ሲሆን፣ መንግሥት የጥገኛነት ስሜት አመለካከትን (dependency syndrome mindset) እንዲቀርፍ ያስችለዋል። ኢትዮጵያ በቅድሚያ የእውቀት ሀብቷን ሳታሳድግ እና ሳታበለፅግ ድህነትን ማስወገድ አይቻላትም። ለምሳሌ፣ የሀገራችን ሀብት የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ መፃኢ እጣ-ፈንታው በሠራተኞቹ እውቀት እና በማሰብ ችሎታቸው ላይ እንጂ በአውሮፕላኖቹ እና በጉዞ ስምሪቱ ላይ የተመረኮዘ አይደለም።
መንግሥታዊ ማሻሻያ፧ ከኢኮኖሚው ሥራ አመራር ጋር በተያያዘ አበክሮ ሊታወቅ የሚያስፈልገው ዋናው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት የገንዘብ ሚኒስቴር ነው። ይህ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት በብሔራዊ ኢኮኖሚው ላይ ከሚጫወተው ወሳኝ ሚና አኳያ፣ ከፍተኛ የሙያተኝነት ደረጃ ባላቸው ሰዎች የተሞላ ስለመሆኑ መንግሥት ማረጋገጥ ይገባዋል። እንዲሁም (ሀ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የመንግሥት (የአስፈፃሚው) ተፅዕኖ የሌለበትና ተጠሪነቱንም ለፓርላማው (ለሕግ አውጪው) ማድረግ፣ እና (ለ) የፋይናንስ ሥርዓቱን ነፃ (liberalize) ማድረግ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገባቸው ናቸው።
ኢትዮጵያ እንደሚገባት አላደገችም፣ ምክንያቱም እንደሚገባት ስላልተመራች፤ ይህም ድህነትን ከአመራር ግድፈት የመነጨ ችግር ያደርገዋል፣ ምክንያቱም የአመራር ብቃት ዋጋ አለውና። ኢትዮጵያ (አሁንም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሕዝቦቿ እየተራቡ የሚገኙባት) የኢኮኖሚ ስንኩል (economic basket case) ሀገር የሆነችው በሕዝቦቿ ድክመት ሳይሆን በመሪዎቿ ውድቀት ነው። ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት የሕዝቦቿን ታልቅነት የሚመጥኑ መሪዎች ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድን እንደ ሀገራዊ መንፈስ አነቃቂና ተስፋ-ሰጪ የኢትዮጵያ መሪ ተቀብዬአቸዋለሁ። አሁን ኢትዮጵያ ከምትገኝበት ወቅታዊ ሁኔታ (Current State) በሽግግር ሂደት አማካኝነት (Transition State) ኢትዮጵያ መድረስ ወዳለባት ወደሚፈለገው መፃኢ ሁኔታ (Desired Future State) የሚደረገውን የለውጥ ሂደት መስመር ማስያዝ እና ማፋጠን የሚችሉ መሪ እንደሆኑ ይሰማኛል። የህወሓት/ኢሕአዴግ ፍፁም አምባገነንነት ተቀባይነት የለውም፤ ምክንያቱም አገዛዙ የጋራ ጠላቶቻችን የሆኑት አምባገነንነት ፣ድህነት፣ በሽታ፣ ሙስና፣ እንዲሁም የውስጥ መፈናቀል ክትትል ማዕከል (Internal Displacement Monitoring Centre) እንዳስቀመጠው በ2011ዓ.ም. ለ1.4 ሚሊዮን ዜጎች በሀገር ውስጥ መፈናቀል ምክንያት የሆነው የጐሣ ግጭት መገለጫ ነውና። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ኢትዮጵያን ከህወሓት/ኢሕአዴግ የማፊያ ኢኮኖሚ እና የጐሣ አፓርታይድ ሥርዓት ሁሉም ዜጎች በሕግ ፊት እኩል ወደሚሆኑበትና የግለሰብ ሰብዓዊ መብቶች ሙሉ በሙሉ ወደሚከበሩበት እውነተኛ ዲሞክራሲ ለማሸጋገር ተፅዕኖ የመፍጠር አቅማቸውን (soft power) መጠቀም ይችላሉ የሚል ተስፋ አለኝ። ኤኤንሲ(African National Congress) ጉዳዩን ነጮች ላይ ሳይሆን ‘አፓርታይድ’ ላይ በማነጣጠር ለሁሉም ደቡብ አፍሪካውያን መብት ባደረገው ትግል ስኬታማ ሆኗል። እኛም የጐሣ አፓርታይድን ለመፈረካከስ ተመሳሳዩን እርምጃ መውሰድ እና ለሁሉም የኢትዮጵያ ዜጎች እኩልነትን የሚሰጥ ዜጋ-ተኮር ስርዓትን ማወጅ፣ በአሳብ ብቻ መወዳደር እንጅ በጐሣ ማንነት ላይ ተመርኩዞ የፖለቲካ ፓርቲዎች መቋቋምን መከልከል ይጠበቅብናል።
“ሁሉም ለአንድ ኢትዮጵያ፣ አንድ ኢትዮጵያ ለሁሉም” በሚለው መንፈስ ተነሳስተው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ የሽግግር ሂደቱን የሚያስተናብሩበት ትክክለኛ መንገድ በቀዳሚነት ትልቁ እና ደፋሩ እርምጃ ‘የብሔራዊ አንድነት የሽግግር መንግሥት’ ማቋቋም ሊሆን ይገባል። ይህ ካልሆነ ግን የራሳቸውን የ‘መደመር’ መርሆ ተከትለው በአሳታፊ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያን ዜጎች ተዋናይ በማድረግ ድልድያችን ሆነው መገኘት ነው። ከዚህ አኳያም (ከሚቀጥለው ምርጫ አስቀድሞ) አሁን በሚገኘው ሕገ-መንግሥት ላይ ከ4 እስከ 5 ወራት በሚደርስ ጊዜ ውስጥ ውይይት ለማድረግና በዜጎች ሕዝበ-ውሳኔ በሌላ ለመተካት ወይም ለማሻሻል የሚሰባሰቡ ከየወረዳው በአብላጫ ድምፅ የተመረጡ ተወካዮችን አስፈላጊው እውቀት ያላቸውን ባለሙያዎች የሚያካትት የብሔራዊ ሕገ-መንግሥት ጉባኤ (National Constitutional Convention) ማዘጋጀት አለባቸው። ጥናታቸውን ለማፋጠን እና ለመነሻነት ዓላማ፣ ቡድኑ ሁሉም የዓለም ሕገ-መንግሥቶች ታትመው የሚገኙበትን ይህንን ድረ-ገጽ ሊጠቀሙ ይችላሉ፡-https://www.constituteproject.org/
በነገራችን ላይ፣ ስለ አዲስ ወይም ስለሚሻሻል ሕገ-መንግሥት ከተነሳ አይቀር፣ “Constitution” ለሚለው ቃል የተሰጠው “ሕገ-መንግሥት” ከሚለው አማርኛ ቃል ጋር ቅራኔ አለኝ፤ ምክንያቱም “የዘውድ ሕገ-መንግሥት”፣ “የደርግ ሕገ-መንግሥት”፣ እና “የኢሕአዴግ ሕገ-መንግሥት” የሚል መጠሪያ ያስታውሰኛልና። “ርዕሰ-ብሔር” እና “ርዕሰ-መስተዳድር” እንደምንለው ሁሉ ለኢትዮጵያ “Constitution”ንም የመንግሥት ሳይሆን የሀገሪቱ ላዕላይ ሕግ እንደመሆኑ“የኢትዮጵያ ርዕሰ-ሕግ” ተብሎ ቢጠራ ይሻል ይመስለኛል። ኢሕአዴግ ሕገ-መንግሥቱን የራሱ የድርጅታዊ ሰነድ ያደረገ፣ ጐሣ-ተኮር መንግሥት የደነገገ ከፋፋይ አምባገነን ነው። ስለመሆኑ ትግላችን ግን ኢትዮዽያዊነትን አስቀድሞ የግለሰብ ዜግነትን ያቀፈ፣ከሥዩመ-እግዚአብሔር ወደ ሥዩመ-ፓርቲ የተሸጋገረውን አሁን ወደ ሥዩመ-ሕዝብ ለማሳደግ፣ከሕዝብ ለሕዝብና በሕዝብ ድምፅ የተመረጠና በሕግ የበላይነት የሚዳኝ ሕገ-ሕዝብ አስተዳደር ለመፍጠር ነው። መንግሥት እና አገርን አንድ አድርጎ የማየት ልማድም ማብቃት አለበት። ሀገር ሉዓላዊነቱን በመንግሥት አማካኝነት የሚያስተገብር ሉዓላዊነት ያለው አካል ነው። ሀገር ኑዋሪ ሲሆን መንግሥት ግን ጊዜያዊ ነው።
ከመንግሥት (ወይም ከሲቪል ማኅበር) አስቀድሞ የተፈጥሮ ሕግ ነበር። ሁሉም ሰው ከመነሻው ራስ-ተኮር በመሆኑም እራሳችንን አንዳችን ከሌላችን ለመጠበቅ መንግሥታትን መሠረትን። ሰዎች እራስን የማቆየት ወይም የማኖር (ተፈጥሯዊ) መብታቸውን ተፈፃሚ ለማድረግ መንግሥታት ላይ ያምፃሉ። ሕግ ሰብዓዊ ተፈጥሮን ያከበረ ሊሆን ይገባል። ስለዚህም የሕግ መነሻ ወይም ምንጭ ሰዎች መሆን ይኖርባቸዋል። ዜጎች ኢ-ፍትሃዊ የሆነን መንግሥት የማውረድ መብት ብቻ ሳይሆን ግዴታም ሊኖርባቸው ይገባል። ቶማስ አክዌነስ እንዳለው፣ “አምባገነናዊ መንግሥትን መቃወም ለፈጣሪ ሕግጋቶች መገዛት ነው።”
በሟቹ በመለስ ዜናዊ ሲቀለድበትና ሲወገዝ የቆየው የኢትዮጵያ ዳያስፖራ፣ አሁን ተሰውሮ እንደቆየ ሐብት (hidden treasure) ተቆጥሮ በሀገር-ግንባታ ሂደቱ እንዲሳተፍ በጋበዙን በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ተቀባይነት አግኝቷል። በነገራችን ላይ፣ ለሁለቱም ለመንግሥት እና ለኢትዮጵያ ዳያስፖራ የጋራ ጥቅም ሲባል፣ ብሎም የጠቅላይ ሚኒስትር አብይን ድልድይ የመገንባት ጥረት ለማጠናከር፣ የጥምር ዜግነት (dual citizenship) ሕግ የማውጣቱ ሥራ ጉልህ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። ራዕይ ለማመላከት፣ወደ አሜሪካ በስደት የመጡት እና ትውልደ-አሜሪካ-ቻይናውያን ለየራሳቸው ሀገራት ያሳኩትን ኢትዮጵያም እንዲሁ እንድታሳካ ለዲያስፖራ ኢትዮዽያውያንም ትክክለኛውን ዓይነት ምቹ ሁኔታ በመፍጠር የሰብዓዊ ካፒታልን ፋይዳ ሊጨምር የሚችል ሰውን ማዕከል ያደረገና እውቀት-መር የሆነ መርህ የኢትዮክራሲን ራዕይ ያንጸባርቃል።
ኢትዮጵያ የመደብ ፖለቲካን በደርግ ዘመን፣ እንዲሁም የጐሣ ፖለቲካን በህወሓት/ኢሕአዴግ ዘመን ሞክራለች። አሁን ደግሞ ጊዜው ከፓርቲ በፊት የሀገር ፍቅርን የምናስቀድምበት የብሔራዊ ፖለቲካ ጊዜ ነው። የፖለቲካ ፓርቲዎችም ቢሆኑ ፓርቲያቸውን በተሻለ የሚያገለግሉት በቅድሚያ ሀገራቸውን ሲያገለግሉ ነው። የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የሲቪል ማኅበራት፣ እንዲሁም ሀገር-ወዳድ ግለሰቦች ለ“ዛሬ ትብብር፣ ነገ ውድድር” ዝማሬ ሙሉ ምላሽ ይሰጡ ዘንድ ከክፍፍል ፖለቲካ (factional politics) መፋታት ይኖርባቸዋል። ቅድሚያ ኢትዮጵያን ከውስጥ እና ከውጭ ጠላቶችዋ ለመታደግ የመተባበሪያ ጊዜው አሁን ነው። ስለሆነም፣ ለቀጣዩ ነፃ እና ፍትሐዊ ምርጫ በሚደረገው ዝግጅት ተፎካካሪ/ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሸናፊ በሚሆኑበት ትብብር ላይ በመሳተፍና አስተማማኝ እና ኗሪ የህወሓት/ኢሕአዴግ ምትክ አማራጭን ለዜጎች የሚያቀርብ የፓርቲ መርሃ-ግብር ወይም ማኒፌስቶ በማዘጋጀት በትክክለኛው የታሪክ መስመር ላይ እንዲቆሙና ለውጥ እንዲያመጡ ጥሪዬን አቀርባለሁ።
ህወሓት/ኢሕአዴግ ጐሣን መሠረት ባደረገ የጥላቻ ፖለቲካ ይመራል። እኛን የሚመራን ኃይላችን ለሀገራችን ያለን ፍቅር ነው። ፍቅር በጥላቻ ላይ ይነግሣል። ኢትዮክራሲ መርዛማውን የጐሣ-መር ትርክት አይታገስም። መላው ኢትዮጵያዊያን ኃላፊነት በጎደላቸው፣ ቅቡልነት በሌላቸውና ብቃት በተሳናቸው መሪዎች ስር ሲሰቃይ ቆይቷል። ኢትዮክራሲ በአዲስ ዜጋ-ተኮር ርዕሰ-ሕግ (constitution) እና በላቁ የነፃነት (liberty)፣ የእኩልነት (equality)፣ እና የወንድማማችነት (fraternity) ልዕለ-ሀሳቦች ጥላ ስር አዲሲቷን ኢትዮጵያ ለመገንባት አርቆ ይመለከታል።
ከ123 ዓመታት በፊት በአድዋ ጦርነት፣ ከሁሉም የጐሦች ቡድኖች እና ከሁሉም ሃይማኖቶች የተውጣጡ ሐገር-ወዳድ ኢትዮጵያዊያን፣ ኢትዮጵያ ከክፍሎቿ ድምር በላይ የላቀች ስለመሆኗ አረጋግጠዋል። የብዙሃን-ጐሣ ብሔራዊ ሀገር በመሆናችን፣ የራሳችን የግዕዝ ፊደል ያለን፣ የአድዋ ድል እና የሰው ዘር መገኛነታችን ሁሉም ኢትዮጵያን የተለየንነት (Ethiopian Exceptionalism) ስለመወከላቸው እውቅና የተሰጠን የአኩሪ ታሪክ ባለቤቶች በመሆናችን እድለኞች ነን። ዛሬ ግን የኛ ተግዳሮት የራሳችንን ድል መቀዳጀት ነው። የኢትዮጵያ ስብጥራዊ ውበት በይበልጥ የሚመሰለው ለጋራ መልካምነት በቆመ የብዙሃን አንድነት ነው። አንድ ላይ ስንሆን ጠንካራ ነን። የማንከፋፈል ስንሆን የማንበገር እንሆናለን። ብዙ ሆነን አንድ የሚያደርገን ኢትዮጵያዊነታችን ነው። ለኢትዮጵያውያን ልዩነታችን ጌጣችን እና የፈጠራ ምንጫችን፣ አንድነታችን ኃይላችን ነው።
ለማጠቃለል፣ ኢትዮክራሲ አደገኛ ለሆኑት የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ሀገር-በቀል መፍትሔ ነው። በማያቋርጥ ድህነትና በጐሣ ፖለቲካ ካንሰር አባባሽነት ላለፉት 28 ዓመታት ስንደናቀፍ ቆይተናል። አምባሻውን እንዴት ማተለቅ እንችላለን በሚለው ላይ ከፍተኛ ትኩረት ማድረግ ሲገባን፣ የጐሠኝነት ለያዪው አስተሳሰብ ግን አምባሻውን ይከፋፍለዋል። ኢትዮጵያውነት የልዩነቶች ውኅደት የፈጠረው የወል ማንነት መገለጫ የሆነ እኛነት ነው።ኢትዮጵያ የብዙሀን-ጐሣ ሀገርነቷን ስብጥራዊ ውበት ጎን-ለጎን እያበለፀገች የጐሣ ክፍፍሎሹን (silo syndrome) በመቅረፍ የሀገራዊ አንድነት ስሜት ዳግም እንዲያንሰራራ የመጠቀ ስትራቴጂ ያስፈልጋታል።
ኢትዮክራሲ የፈጠራ ችሎታና ትግበራ የተጎዳኙበትን፣ እንዲሁም ኢትዮጵያ በ2031 ዓ.ም. ሰብዓዊ ካፒታሏን ከታሰረበት ማነቆ አልላቃ የተንሰራፋውን ርሃብ፣ በሽታና መሃይምነት ድል መንሳት የሚያስችላትን ሕዝብን ማዕከል ያደረገና በእውቀት ላይ የተመረኮዘ የኢኮኖሚ ሥርዓት (knowledge based economy) ሥራ ላይ በማዋል የዲሞክራሲ እና የልማት ፍኖተ-ካርታ አስቀምጦ ኢትዮጵያን ከጥገኝነት ስሜት አመለካከት (dependency syndrome mindset) ነፃ ያደርጋታል። ስለ እውቀት ገንቢነት ስናስብ ማንበብ እና መፃፍ የሰብዓዊ ልማት የመጀመሪያ እርምጃዎች መሆናቸውን እያስታውስን፣ የኢትዮጵያን ቋንቋዎች የበለጠ ለማበልፀግና የሁሉንም ሥነ-ጽሑፍ ለማጎልበት የግዕዝን ፊደል ለሁሉም የኢትዮጵያ ቋንቋዎች በትጋት እንድንጠቀም ሀሳብ አቀርባለሁ።
ኢትዮጵያዊያን የበሬ እርሻ እና የሣር ጎጆ ባሕልን በመለወጥ ውድ አገራቸውን ኢትዮጵያን ለማዘመን ይመኛሉ። የሥራ-አጡን ወጣት ስሜት ከከተማ መንገድ ወደ ገጠሩ ልማት ለመለወጥ፣ የሀገሪቱን ከእጅ-ወደ-አፍ አኗኗር ወደ ተደራጀ ንግድ-ተኮር እርሻ (commercial farming) ለማሸጋገር ከግብርናው ዘርፍ በመጀመር በንቃት መሣተፍና በሁል-አቀፍ የሀገር-ግንባታው ጥረትም መርካት ይጠበቅባቸዋል። ሀገሪቱን ከድህነት ውስጥ ጎትቶ ለማውጣት የሥራ-ወዳድነት ሥነ-ምግባር፣ የራስ-አገዝ ባህል፣ እንዲሁም የኅብረት ሥራ የማኅበረሰብ ልማት መርሆዎች በወጣቱ ዓዕምሮ ውስጥ ሊሰርፁ ይገባል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የህወሓት/ኢሕአዴግ አያሌ ስህተቶችን በማረሙ ላይ መጠመዳቸውን አያለሁ አደንቃለሁም፤ ነገር ግን አያሌ የኢትዮጵያ ማኅበረሰቦችን ላዳረሰ እጅግ የሚያስጨንቅ የሞት እና የንብረት ውድመት ጉዳይ ቸል ማለታቸውያሳስበኛል። ምክንያቱም የኢትዮጵያን መሠረታዊ ችግር ይህም ማለት በህወሓት/ኢሕአዴግ ሕገ-መንግሥት የታወጀውን አውዳሚ የጐሣ ፌዴራሊዝም (ዜናዊዝም) መፍትሔ ለመስጠት የፖለቲካ ፈቃድም ሆነ ወኔ ያጠረቸው ይመስላል።
ኢትዮጵያ አንድ ወይስ ሁለት የሕግ አውጪ ምክር ቤቶች ሊኖራት ይገባል? ወይም ለኢትዮጵያ የሚስማማው አሃዳዊ ወይስ ፌዴራላዊ ሥርዓት ይሆን? ወይም ለኢትዮጵያ የሚሻለው ፓርላሜንታዊ ወይስ ፕሬዝዴንታዊ ሥርዓት ነው የሚሉት ጉዳዮች በሁሉም የሚመለከታቸው ወገኖች ጤናማ ክርክር እና ሕዝባዊ ውይይት ከተደረገ በኋላ ህገ-መንግሥት መተካት ወይም ማሻሻል እና ከዛ በኋላ ምርጫ ማካሄድ ይቻላል።
ሁላችንንም ሊያኮራ የሚችል የመንግሥት ዓይነት ከሁለት ክፍለ-ዘመናት በፊት በቶማስ ፔይን እንዲህ ተገልፅዋል፡- “በማንኛውም አንድ የዓለም ሀገር እንደዚህ ብሎ መናገር የተቻለ እንደሆን፣ ደሃው ሕዝቤ ደስተኛ ነው፣ አላዋቂም ሆነ ሀዘንተኛ ሰው በመካከላቸው አይገኝም፤ እስር ቤቶቼም እስረኛ ጎዳናዎቼም የኔቢጤ አይታዩባቸውም፤ አረጋዊያን የሰው ፊት አያዩም፤ የሚጣለው ግብር ጨቋኝ አይደለም፤ ይህ እሳቢው ዓለም ባልንጀራዬ ነው፣ ምክንያቱም ደስታው ደስታዬ ነውና። እነዚህ ነገሮች መነገር ከቻሉ፣ እነሆ ያ ሀገር በሕገ-መንግሥቱ እና በመንግሥቱ ሊኮራ ይችላል።”
ኢትዮጵያን ከኢሕአዴግ የአምባገነን አገዛዝ ነፃ ለማውጣት ኢትዮዽያውያን በሀገርቤት በገፍ ሲታሰሩና ብዙዎች ደግሞ በፖለቲካ ትግሉ ህይወታቸውን መስዋዕት ሲከፍሉ ቆይተዋል። በበኩሌ ኢትዮዽያን ከኤስኖክራሲ (ሥልጣን ለጐሠኞች) ወደ ኢትዮክራሲ (ሥልጣን ለኢትዮዽያ ሕዝብ) የሚያሸጋግር መፍትሄ ሀሳብ አቅርቤአለሁ። ለረዥም ጊዜ ሙሉ ለሙሉ ከሽፎ በሥልጣን የቆየ መንግሥት አንድም የለም። ኢትዮጵያ ነፃ ትወጣለች፤ አምባገነንነትም በዲሞክራሲ ይተካል፤ ምክንያቱም እንደ የአፍሪካውያን አባባል “ዝናብን ማንም ሊያቆመው አይችልም!”
አቶ አባተ ካሣ “Value Analysis and Engineering Reengineered” እና “የፋይዳ ትንታኔ እና ህንደሳ” መፅሐፎች ደራሲ ነው።
ኢትዮክራሲ ላይ የሚኖራችሁን ምልከታ በደስታ ለመቀበል ዝግጁ ነኝ። አመሰግናለሁ።kassa.abate@gmail.com Sponsored by Revcontent