July 1, 2019
Source: https://www.zehabesha.com/amharic/archives/95843
በአማራ ክልል የባለስልጣን ግድያ መፈንቅለ መንግስት ነው ተብሎ ከብርሃን ፍጥነት በፈጠነ አቶ ንጉሱ ጥላሁን በኢትቪ ብቅ ብለው መናገራቸው እና ጠቅላይ ሚንስትር አብይ ደግሞ መከላከያ እንዲገባ ትእዛዝ መስጠታቸው ከመገረም ውጪ እውነታነትን የሌለው ጉዳይ ነው። በዚህ በከሸፈ ቅንብር መላው የኢትዮጵያን ህዝብ ያሳዘነ ብቻ ሳይሆን ያስቆጣም ጭምር ነው። አዲስ አበባ ለይ አፍንጫቸው ስር የተደረገወን የጠቅላይ ሚንስትር የግድያ ሙከራ እና የኢንጅነር ስመኘው ግድያ እስካሁን መንገር ያልቻለ ተቋም የአማራ ማስ ሚዲያ ሳይዘግብ የአማራ ባለስልጣናት ሳይናገሩ መፈንቅለ መንግስት ነው ተብሎ የታወጀው አዋጅ ለግዜው መምታት የሚፈልጉትን በመምታት ማሰር የሚፈልጉትን በማሰር የአማራውን ክልል የማዳከም ስራ የተሰራ መሆኑ እና ከአለም መንግስታቶች የሚመጣባቸውን ጫና ለመቋቋም ያሰቧት ቢሆንም የተሰራው ስህተት ግን የኢትዮጵያን ፖለቲካ በአስደንጋጭ ሁኔታ የቀየረው እና የጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ያሳጣ መሆኑ እና ከአሁን በኋላም በተረጋጋ ሁኔታ የመምራት ሞራሉ እና ተቀባይነቱን ያታጣበት የውድቀት ዋዜማ ያየሁበት ነው።
አዲስ አበባ ለይ ሁለት ትላልቅ አስደንጋጭ ክስተቶች ተከስተዋል እስከዛሬ ድረስ ማን እንዳከናወናቸ አልተነገረም ነገር ግን የግዜ እርዝመቱን ልብ ማለት ያስፈልጋል። የመጀመሪያው በዶክተር አብይ የተደረገ የግድያ ሙከራ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የኢንጅነር ስመኘው ግድያ ነው። ታድያ እስከዛሬ መንገር ያልተቻለው ወንጀሎችን እያየን በገለልተኛ አካል ሳይጣራ ፍርድ ቤት ጥፋተኛው ማን እንደሆነ ምርመራ አድርጎ ሳያሳውቅ የአማራ ማስሚዲያ ሳያሳውቅና የአዴፓ ባለስልጣን ምንም አይነት ጥያቄ ሳያቀርቡ እና ምንም ሳይናገሩ በብርሃን ፍጥነት መፈንቅለ መንግስት ነው ብለው አውጀው ክልሉን በመከላከያ ማስወረር ለግዜው ድንጋጤን ቢፈጥርም የኋላ ኋላ ከፍተኛ ዋጋ እንደሚያስከፍል ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው።
የመፈንቅለ መንግስት ዜና በመነገሯ የተሰራው ወንጀል በዚህ መልኩ ማለፍ ይቻላል ከሚል አጉል ቀቢጸ ተስፋ እና በአለም ማህበረሰብ የሚመጣውን ጫና እንወጣዋለን በሚል ግምት ነበረ። ሁለቱም ግን አልተሳኩም። አልተሳካም ብቻ ሳይሆን የጠቅላ ሚንስትሩን በኢትዮጵያ ብሎም በአለም ማህበረሰብ ላይ የነበራቸውን ተቀባይነት ከማሳጣት በተጨማሪ የውድቀት ዋዜማውን በፊሽካ እንደማስጀመር ጭምር ነው።
ጠቅላይ ሚንስትሩ መግደል መሸነፍ ነው የምትለውን ቃል ደጋግመው በመጠቀም ይታወቃሉ ፍርዱም በዚሁ ቃል መሰረት ይዳኛሉ ማለት ነው። ሰው የተናገረውን ያንኑ ፍሬ ይበላል እንደሚባል የዚህን መልስ በግዜው እንደሚመጣ እሙን ነው። ሰኔ 15 የሽንፈቶን አዋጅ እንዳወጁ እቆጥረዋለው። እኔ ከዚህ ስለሆንኩኝ የተደረገው ነገር ትክክል ነው አልልም ወይንም እኔ ከዛ ስለሆንኩኝ የተደረገው ነገር ትክክል አይደለም የሚል የተዛባ ፍርድ የለኛም ግና እውነቱ ግን እውነት ስለሆነ እናገራለው። ህውአታዊያን የአማራውንና የኦርቶዶክስን አከርካሪውን ሰብረነዋል ብለው በአደባባይ ሲናገሩ የነበሩት ዛሬ ህልም በሚመሰል መልኩ ሲነቁ አከርካሪያቸው ተሰብሮ መቀሌ እንደመሸጉ እናውቃለን። ዛሬም የአብይ መንግስት በተመሳሳይ እንደውም በአደገኛ መልኩ ስህተትን በመድገም የሽንፈት መንገዱን መቀልበስ በማይቻልበት መልኩ በአስደንጋጭ ሁኔታ መጀመራችው የኔ ብዬ የተቀበልኳቸው መሪ የሽንፈትን አዋጅ በአደባባይ ሲነግሩኝ መስማትና ማየት ለኔ ህመምም አስደንጋጭም ነው።
ደካማ አማካሪ ያለው መሪ ያለ አመት አይነግስም የሚለው አነጋገር እውነትነት ያለው ነው። የሰኔ አስራምስቷ ክስተት በቅርብ ቀን ዋጋ ወደማስከፈል ክስተት ያመራል። አብይን ለስልጣን ያበቃው የአማራው ድጋፍ ሙሉ በሙሉ በማሳጣት ህውአት በስንጥቅ ውስጥ የምታረድገው አደገኛ ሁኔታ የአብይን መንግስት ዋጋ የሚያስከፍለው መሆኑና ዋንኛው ግን የአማራ ማህበረስብ በአገር ቤትና በውጪ ያለው እንደ አማራነቱ በስሜት እና በእልህ መሰባሰቡ እና ያለውን እልህና የመከዳት ስሜት ለሚመለከት ሰው ጠቅላይ ሚንስትር አብይ ከአማራው ማህበረስብ የነበረው አመኔታ ፈርሶ በህዝቡ እየታዩ ያሉ እንቅስቃሴ ለዶክተር አብይ መጪው ግዜ ፈታኝና አደገኛ እንደሚሆን የአየር ሁኔታው በደንብ ይናገራል።
መቺው የአብይ ስጋቶች የመፈንቅለ መንግስ እንቅስቃሴዎችን እና አደጋቸውን በግልጽ ከሁለት አካሎች እንደሚመጡበት እገምታለው።
1ኛ ለአብይ መንግስት መንግስት ግልበጣ አደጋ ህውአት ስትሆን ባላት በዘረጋችው በድሮ መረብ ተጠቅማ ወደ ስልጣን የመምጣቱን ትንቅንቅ በቅርቡ ሊጀምሩ መቻላቸው።
2ኛ በጀዋር የሚመራው ቡድን አብይ እኛ እንደምንፈልገው አካሄድና ፍጥነት እየሄደ አይደለም በሚል ሰበብ በተደጋጋሚም ቅሬታ እንደሚያቀርበውም በአብይ መንግስት ላይ እምነት ያለው ባለመሆኑ ጃዋሪያን በአብይ መንግስት ላይ ከፍተኛ አደጋ በመፍጠር ስልጣኑን የመቆጣጠር አደጋ ሊከሰት መቻል።
3ኛ የሃይማኖት አባቶች የሱባኤ ግዜ ማወጅና ከዛም ከፍ ካለ ደግሞ የውግዘት ቃል ሊያስተላልፉ መዘጋጀታቸው። ውግዘት ደግሞ ለተወገዘው አካል እንኳን ሰው ምድሪቷንም እንዳትታዘዘው የሚገዝቱ ስለሆነ ሰው ብቻ ሳይሆን ምድሪቷን የምትዋጋው መሆኑ። አቡነ ጴጥሮስ የጣሊያንን ወራሪ እንደገዘቱት እንኳን ሰው ምድሪቷ አትገዛልህ እንዳሉ።
ሳጠቃልለው የሚያሳዝነውና የሚያሳስበው ነገር ጠቅላይ ሚንስት አብይ የተጣላው ኢትዮጵያን እጠብቃለውና በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ አልደራደርም ከሚለው እና አብይን ከዳር እስከዳር በመውጣት ለመንግስትነቱ እውቅናንና ቅቡልነትን ከሰጠው የአማራ ማህበረሰብ ጋር ስለሆነ መጪው ግዜ ለአብይ በጣም ፈታኝ አደገኛ እና አጣብቂኝ ውስጥ እንዳለ ይታየኛል።
ከተማ ዋቅጅራ
Email- waqjirak@yahoo.com
01.07.2019