
አቶ ዮሐንስ ቧያለው የአማራ ክልል ርእስ መስተዳደር ሆነው ሊመረጡ እንደሚችሉ አንዳንድ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ምን አልባት ከአዴፓዎችና፣ ከአዴፓ ውስጥ አዋቂዎችና የቀድሞ ብአዴኖች ከነበሩት ውጭ፣ ስለ አቶ ዮሐንስ ብዙ ሰው በቂ መረጃ ይኖረዋል ብዬ አላስብም።
አቶ ዮሐንስም ሆነ ሌላ አመራር፣ በሰኔ 15 የባህር ዳሩ ግድያ ሕይወታቸው ያለፈውን ዶ/ር አምባቸው መኮንን ተክተው በአማራ ክልል ርእስ መስተዳደር ሲሆኑ፣ ከፊታቸው ትልቅ ፈተናዎች ይጠብቃቸል። ከነዚህ ፈተናዎች በቀዳሚነት የሚጠቀሰው አንዱ ፈተና የሚያጠነጥነው አዴፓ ከኦዴፓ ጋር የሚኖረውን ግንኙነት በተመለከተ ነው። አዲሱ ርእስ መስተዳደር ከኦዴፓ ጋር የሕዝቡን ፍላጎት በማዳመጥ፣ በመርህና በእኩልነት ላይ ተመርኩዞ ይሰራሉ ወይ? በተለይም በኦዴፓ ያሉ አፍራሽ ጽንፈኞችን የመጋፈጥ ድፍረት ይኖራቸዋል ወይ? የሚሉት ጥያቄዎች ብዙዎች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች ናቸው።
ኦዴፓ በፌዴራል መንግስት ስልጣን የያዘው በአዴፓ ድጋፍ ነው። አዴፓዎች ባይኖሩ ኖሮ፣ ኦዴፓዎችን የሕወሃት ሃይል ሊጨፈልቃቸው እንደሚችል የሚታወቅ ነው ። አዴፓዎች ከኦዴፓዎች ጋር አብረው መስራት የፈለጉት በቅንነትና አምነዋቸው ስለነበረ ነው ። አማራ፣ ኦሮሞ .. ሳይባል እንደ ኢትዮጵያዊያን በጋራ አብረን አገራችንን እናሳድጋለን በሚል። ኦዴፓዎች ግን ስልጣን ሲይዙ ተስገበገቡ። ቁልፍ ቁልፍ የሚባሉ ቦታዎችን ያዙ ። የጽንፈኛ ኦሮሞዎችን ፍላጎት ላማሳካት ሲስተማቲክ በሆነ መንገድ መንቀሳቀስ ጀመሩ። እኩል አብረን እንደግ ሳይሆን ኦሮሞ ይቅደም፣ የኦሮሞ ልዩ ጥቅም ይጠበቅ አሉ። በአዲስ አበባማ ሆነ በፊዴራል ደረጃ ወሳኝ የሚባሉ ቦታዎችን ለመቀመጥ ዘር መለኪያ ሆነ። በአጭሩ አነጋገር የኦዴፓ አመራሮች የተደረገላቸውን ዉለታና ድጋፍ ረስተው፣ እንዴት ወደ ስልጣን እንደመጡ ዘንግተው ፣ አዴፓዎችን ከዱ። የፈረንጆችን አባባል ልጠቀምና፣ they throw them under the bus.
የአዴፓ አመራሮች ይሄንን ክህደት ታዝበው ብዙ ጊዜ ከኦዴፓዎች ጋር ስብሰባ እንዳደረጉ ብዙ ጊዜ ተዘግቧል። ደስተኛ እንዳልሆኑ ብዙ ጊዜ በስብሰባዎች ገልጸዋል። ሆኖም በውስጣዊ ስብሰባዎች ከአዴፓዎች የቀረቡ ተማጽኖዎች ለውጥ ማምጣት አልቻሉም። አዴፓዎች የትም አይደርሱም በሚል ነው መሰለኝ፣ ኦዴፓዎች በጽንፈኛ አሰራራቸው ቀጠሉ።
እንግዲህ በውስጥ መስመር ነገሮችን ለመቀየር ተሞክሮ ከከሸፈ፣ ንግግርና ውይይትን እንደ ፍርሃትና ድክመት ከተቆጠረ፣ እንዴት አድርገው ነው አዴፓዎች በባህር ዳሩ ጠቅላላ ጉባዬ አናስፈጽመዋለን ብለው ያስቀመጡትን ተግባራዊ ማድረግ የሚችሉት?
በኔ እይታ አዲሱ ርእስ መስተዳደር ከዚህ በፊት የነበረውን አካሄድ ውጤት እንዳላመጣ ተረድተው፣ ከኦዴፓ ጋር ያላቸውን ግንኙነት መመርመር ያለባቸው መሰለኝ።
አንደኛ – አዴፓ ትልቅ የፖለቲካ ሃይልና ጡንቻ እንዳለው ሊሰመርበት ይገባል። አዴፓ ከፈለገ፣ ተመሳሳይ አመለካከት ያላቸውን የደሃዴን አባላትን በማቀፍ ጠቅላይ ሚኒስትር መቀየር ይችላል።
ሁለተኛ – የኦዴፓ አመራሮች ግትርነትን መርጠው፣ የኦሮሞ ጽንፈኞችን ጥቅምና ፍላጎት ለማሳካት አሁንም የሚዳክሩ ከሆነ፣ አዴፓ ቀይ መስመር በማስመር፣ በመርህ ደረጃ ከኦዴፓ ለመፋታት መዘጋጀት ያለበት መሰለኝ።
ሶስተኛ – በኦሮሞ ክልል አማራዎችና ሌሎች ኦሮሞ ያልሆኑ ማህበረሰባት፣ መብታቸው መረገጥ ብቻ አይደለም፣ እየተገደሉ፣ እየተፈናቀሉ ነው። የኦሮሞ ክልል በዚህ ረገድ ያደረገው አምስት ሳንቲም አዎንታዊ ስራ የለም። ዜሮ፣ ባዶ፣ ናዳ፣ ኒች ። እንደውም ድርጊቶቹን የሚፈጸሙት ራሳቸው የኦዴፓ አመራሮችና አባላት ናቸው። በለገጣፎ በግፍ ያፈናቀለችው የኦዴፓ ባለስልጣን ናት። በጌዴዎ ዜጎችን ያፈናቀሉ ጉጂው(ኦሮሞው) ነዋሪውና ሕዝቡ ሳይሆን የኦዴፓ አመራሮች ናቸው(አንድ የጌዴኦ እናት ዶ/ር አብይ አህመድ በነበሩበት ስብሰባ እንደተናገሩት) ። ስለዚህ አዴፓዎች፣ ኦዴፓዎች ለምን እነዚህ መሰረታዊ ማሻሻሎችን እንዳላደረጉ ገፍተው መጠየቅ ብቻ ሳይሆን፣ የጊዜ ገደብ በማድረግ መሻሻሎች ከሌሉ የራሳቸውን ሕጋዊና ሰላማዊ እርምጃ እንደሚወስድ የማስጠንቀቅ ድፍረት ሊኖራቸው ይገባል።
አራተኛ- የኦዴፓ አመራሮች በአማራ ክልል ያሉትን ሚሊሻዎች ለመበተን ፍላጎት ሊኖራቸው እንደሚችል፣ በአዴፓ ላይም ጫና እንዳደረጉ ይነገራል። የአዴፓ አመራሮች በአማራ ክልል ያሉ ሚሊሻዎችን የምንበትነው በትግራይና በኦሮሞ ክልል ያሉትም ሲበተኑ ነው የሚል የማያወላዳ አቋም በመያዝ ፣ አገር አቀፍ የሚሊሻዎች ብተና እንዲኖር እንጂ በአማራ ክልል ብቻ ተለይቶ የሚደረግ ብተናን በጭራሽ እንደማይቀበሉ ማሳወቅ አስፈላጊ ነው።
አምስተኛ- ኦዴፓ እንደ አቶ አዲሱ አረጋ ያሉትን እንዲያባረር፣ እንደ ጃዋር ላሉ ጽንፈኞች የሚያደርገውን እንክብካቤና መንግስታዊ ጥበቃ እንዲያቆም ፣ መጠየቅ ያለባቸው መሰለኝ።
ሰድስተኛ – አዴፓዎች ኦዴፓዎችን ለማስደሰት በአምቦ ሲባል እንደሰማነው፣ ለአንድ ጎሳ ልዩ ጥቅም አዴፓ ይታገላል የሚል አይነት ደካማ ፣ አሳዛኝ አስተያየቶች ከመስጠት መቆጠብ አለባቸው። አዴፓ ለአማራ ልዩ ጥቅም ብሎ የትም ቦታ እንደማይታገለው፣ የሚታገለው ለእኩልነት እንደመሆኑ፣ ለኦሮሞ ልዩ ጥቅም እንታገላለን እያሉ ለእኩልነት ቆሚያለሁ ማለት ዉሸት ነው። የኦሮሞ ልዩ ጥቅም የሚባለውን ሊታገሉት ነው የሚገባው እንጂ ሊደግፉት አይገባም። በአዲስ አበባ የኦሮሞ ልዩ ጥቅም ይጠበቅ ማለት፣ አማራው፣ ጉራጌው፣ ትግሪው በአዲስ አበባ ሁለተኛ ዜጋ ይሁን ማለት ነው።
ሰባተኛ – አዴፓ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ የሚሉትን እንደ ምክንያትና መልካም አጋጣሚ በመውሰድ ፣ “ሳናጣራ አናስርም” የሚለው ተረስቶ፣ ዜጎች በጅምላ እየታሰሩ ነው። ለውጥ መጣ ይሉናል። ግን ለውጠነዋል ያሉት አገዛዝ የሚፈጽመውን እየፈጸሙ ነው። አዴፓ በዚህ ጉዳይ ላይ መስመር ማስመር መቻል አለበት። ሕግ እንደጣሱ እስካልተረጋገጠ ድረስ፣ ያዉም እነ መለስ ዜናዊ ህዝብን ለማሸበር ባጸደቁት የጸረ-ሽብርተኛ ሕግ ላይ ተመርኩዘው፣ ዜጎችን ማሰር እንዲቆም ማስድረግ አለበበት ባይ ነኝ።
ከላይ የተቀመጡ ጥያቄዎችን ኦዴፓ ለመፈጸም ፍቃደኛ ካልሆነ ፣ አዴፓ አስፈላጊም ከሆነ ከግንባሩ ከኢሕአዴግ ለመውጣትም መዘጋጅት አለባቸው ባይ ነኝ። ከኢሕአዴግ ይልቅ የሚበልጠው ሕዝብ ነው።ይሄን የማድረግ ደግሞ የአገርቷ ሕግ ፣ የምርጫ ቦርድ ሕግ ይፈቅድላቸዋል።