3 ጁላይ 2019

በእስራኤል ተቃውሞ

በሰለሞን ተካ ግድያ የተቆጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ቤተ-እስራኤላውያን ለተቃውሞ ትናንት አደባባይ ወጥተው ከፖሊስ ጋር ተጋጭተዋል።

ትናንት አመሻሹ ላይ የእስራኤል ፖሊስ እንዳስታወቀው በተቃውሞ ሰልፉ ምክንያት 47 ጸጥታ አስከባሪዎች ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን፤ 60 ሰዎች ደግሞ በቁጥጥር ሥር ውለዋል። ለተቃውሞ በወጡ ሰልፈኞች ላይ ስደረሰው ጉዳት ግን ያለው ነገር የለም።

የ18 ዓመቱ ወጣት ሰለሞን ተካ ሐይፋ በሚባለው ከተማ በፖሊስ የተገደለ ሲሆን ትናንት ስርዓተ ቀብሩ ተፈጽሟል።

ፖሊስ የሰለሞንን አሟሟት በአግባቡ እያጣራሁ ነው ያለ ሲሆን፤ ሰለሞን ሥራ ላይ ባልነበረ የእስራኤል ፖሊስ አባል በጥይት ተመቶ መገደሉ ታውቋል።

ፖሊስ እና የተጠርጣሪው ጠበቃ፤ ሰለሞንን ገድሏል የተባለው ፖሊስ ላይ በወጣቶች ደንጋይ ሲወረወርበት ነበር፤ በዚህም የፖሊሱ ሕይወት አደጋ ላይ ወድቆ ነበር ብለዋል።

ቤተ-እስራኤላውያኑ በበኩላቸው በቤተ-እስራኤላውያን መኖሪያ አካባቢ እጅግ በርካታ የጸጥታ ኃይሎች እንዲሰማሩ ይደረጋሉ፤ ፖሊስ አላስፈላጊ ኃይል የተቀላቀለበት እርምጃ ይወስዳል፤ ለሰለሞን ሞትም ምክንያቱ ይህ ነው በማለት ምሬታቸው አሰምተዋል።

እስራኤል ስደተኞች የማስወጣት ዕቅዷን ሰረዘች

“ወደ እናት ሃገራችን እስራኤል ውሰዱን”

ወጣቱ ሰለሞን ተካ የተገደለበት ከተማ ውስጥ የሚኖር ቤተ-እስራኤላዊ ለቢቢሲ እንደተናገረው እሁድ ሰለሞን ከተገደለ ጀምሮ ተቃውሞው እየተፋፋመ መጥቷል።

“ፖሊስ ለኢትዮጵያውያን ወጣቶች ያለው አመለካከት አግባብ የሌለውና ለአንድ ዜጋ የማይገባ ነው፤ ሰለሞን በፖሊስ እጅ የተገደለ 11ኛ ሰው ነው” ይላል።

ባለፉት ዓመታት በተደጋጋሚ ሰላማዊ ሰልፎች ቢካሄዱም አንዳችም ለወጥ አለመምጣቱን ይገልጻል። ስለዚህም በተቃውሞው እንደሚገፉበት ያስረዳል።

“ወጣቶቹ እስራኤል ውስጥ ሲኖሩ እኩልነት ተሰምቷቸው ያለ ቀለም መድልዎ መሆን አለበት። እንደ አንድ እስራኤላዊ ዜጋ ነጻነታቸው መጠበቅ አለበት” ይላል።

ሰለሞን ተካን የገደለው ፖሊስ ጉዳይ በአግባቡ ፍርድ ቤት ቀርቦ ፍትህ እንዲገኝና በዘላቂነትም ቤተ-እስራኤላውያን ያለስጋት የሚኖሩባት እስራኤል እንድትፈጠር ትግላቸውን እንደሚገፉበትም ተናግሯል።

የዓይን እማኞች ለእስራኤል መገናኛ ብዙሃን ተናገሩት ብሎ ሎስ አንጀለስ ታይምስ እንደዘገበው፤ የጦር መሣሪያውን በማውጣት ሲያስፈራራ የነበረውና ውጥረቱን የፈጠረው ፖሊሱ ነው።

ለእስራኤል ቴሌቪዥን ቃሉን የሰጠ የዓይን እማኝ የፖሊሱ ሕይወት አደጋ ላይ አልነበረም ብሏል። “ለመተኮስ እንዲመቸው በደረቱ ከተኛ በኋላ ሰለሞንን ከቅርብ ርቀት ተኩሶ መታው” በማለት ለእስራኤል ቴሌቪዥን የአይን እማኝ ቃሉን እንደሰጠ ሎስ አንጀለስ ታይምስ ዘግቧል።

ዋላ የተሰኘው የእስራኤል መገናኛ ብዙሃን በበኩሉ ተጠርጣሪው ሰለሞን ተካን ተኩሶ ከመግደሉ ከአራት ደቂቃዎች በፊት ወደ አደጋ ግዜ ስልክ በመደወል በድንጋይ ጥቃት እየተሰነዘረበት እንደሆነና በአስቸኳይ የፖሊስ እርዳታ እንዲደረግለት ጠይቆ ነበር ብሏል።

እስራኤል

ትናንት ቤተ-እስራኤላውያን ባደረጉት የተቃውሞ ሰልፍ ትላልቅ መንገዶችን በመዝጋታቸው ከፍተኛ የሆነ የትራፊክ መጨናነቅ ተከስቶ እንደነበር ዘ ጄሩሳሌም ፖስት ዘግቧል።

ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ ባስተላለፉተ የቪዲዮ መልዕክት በወጣቱ ሞት ሃዘናቸውን ገልጸው፤ ተቃዋሚዎች መንገድ መዝጋት ማቆም እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል።Skip Twitter post by @netanyahu

End of Twitter post by @netanyahu

ፖሊስ እንደሚለው ከሆነ የጸጥታ ኃይሎች ለተቃውሞ አደባባይ የወጡትን ሰልፈኞች ከመበተን ተቆጥበው ቆይተዋል። ይሁን እንጂ ሰልፈኖቹ አመጽ ሲያስነሱ፣ ድንጋይና በነዳጅ የተሞሉ ተቀጣጣይ ጠርሙሶችን መወርወር ሲጀምሩ፣ ጎማ ሲያቃጥሉ፣ በጸጥታ አስከባሪዎችና ንብረት ላይ ጉዳት ማድረስ ሲጀምሩ እርምጃ ለመውሰድ ተገድጄያለሁ ብሏል።

በማኅበራዊ ሚዲያዎች የተለቀቁ ምስሎች በፖሊስና በሰልፈኞቹ መካከል ግጭት ሲከሰት ያሳያሉ።

እስራኤል አፍሪካውያን ስደተኞችን ከእስር ለቀቀች

ትናንት በሰለሞን ስርዓተ-ቀብር ላይ በርካታ ቤተ-እስራኤላውያን የተገኙ ሲሆን፤ የሰለሞን ወላጅ አባት ተካ ቫርካሃ ስለ ልጃቸው አሟሟት የሚያጣራ ገለልተኛ አካል እንዲቋቋም ጠይቀዋል።

የሰለሞን አባት በሃዘን በተሰበረ ልብ ልጃቸውን ለመከላከል በቦታው ስላልነበሩ ልጃቸውን ይቅርታ መጠየቃቸውን የእስራኤል መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል። ”ሰለሞንን ይቅርታ መጠየቅ እፈልጋለሁ። ፖሊስ ሲገድለው ልንከላከልለት በቦታው አልነበርንም” ብለዋል።

”ወደ እስራኤል የመጣነው ልጆቻችን እንዲገደሉ አይደለም። በልጆቻችን መገደል ለምን እንሰቃያለን? ልጅ የምቀብረው ለምንድነው?” ሲሉም ጠይቀዋል።