
Getty Images
በአሜሪካ የጥላቻ ንግግር የሚያሰራጩ ኢትዮጵያዊያንን በሕግ ተጠያቂ የማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩን የኢትዮጵያ አሜሪካዊያን የዜጎች ምክር ቤት አስታውቋል።
ያነጋገርናቸው የምክር ቤቱ ህዝብ ግንኙነት አቶ አምሳሉ ፀጋዬ፤ ወንድም ወንድሙን በማጣላት፤ ብሔር ከብሔር በማጋጨት እንደ ሃገር ለመቀጠል ፈታኝ ሆኗል፤ ይህንን የሚያደርጉ ግለሰቦችን ለማስተማር ብዙ እየተሞከረ ቢሆንም ነገሩ ከቁጥጥር ውጭ እየሆነ ስለመጣ ምክር ቤቱ ግለሰቦቹን ወደ ህግ ለማቅረብ መዘጋጀቱን ይናገራሉ።
• ፌስቡክ የአፍሪካ የዴሞክራሲ ሥርዓት ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ ነው?
• “ሽብር ምንድን ነው ፣ አሸባሪ ማን ነው?” ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ
እርሳቸው እንደሚሉት በአሜሪካ የጥላቻ ንግግር በሌላ ማህበረሰብ በማሰራጨት፤ ሞትና መፈናቀልን ማስከተል በሕግ እንደሚያስቀጣ ይገልፃሉ።በዚህ ረገድ የሚጠቅሱት ፈርስት አመንድመንት የተሰኘው የአሜሪካ ህግን ነው።
እሳቸው እንደሚሉት ምንም እንኳን በፈርስት አመንድመንት የመናገር ነፃነት የተጠበቀ ቢሆንም በዚሁ ህግ ላይ በመናገር ነፃነት የማይካተቱ ድርጊቶችም ተዘርዝረው ይገኛሉ።
“ግድያ፣ ዛቻ፣ ማስፈራሪያ፣ ብሔርን ከብሔር (ማኅበረሰብን ከማኅበረሰብ) የሚያጋጭ ከሆነ፤ የጥላቻ ንግግሩ ያስከተለው የጉዳት መጠን ተለይቶ ግለሰቦቹን ተጠያቂ ለማድረግ ይቻላል” ይላሉ አቶ አምሳሉ።
የሕግ ሂደቱን የሚከታተል የጠበቆች ቡድን ያለ ሲሆን በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ማስረጃዎችን በማቅረብ የጥላቻ ንግግርን የሚያሰራጩ ሕግ ፊት እንዲቀርቡ እንደሚያደርጉም ያክላሉ።
“አብዛኞቹ እዚህ የሚኖሩ ለአገር የሚያስቡ ናቸው፤ ነገርግን የመጡበትን ማህበረሰብ በመርሳት ያ – ማህበረሰብ ቢፈርስ ደንታ የሌላቸው ጥቂቶች አሉ ” የሚሉት አቶ አምሳሉ በህጉ መሰረት ቅጣቱ ከእስር ወደ አገር ተጠርንፎ እስከመመለስ የሚደርስ እንደሆነ ይናገራሉ።
በሕጉ መሠረት ጥላቻን መንዛት ፤ የግድያ ዛቻና ቅስቀሳ፣ የወሲብ ፊልም፤ ወንጀል ለመፍጠር መደራጀትን መሠረት ያደረገ ቅስቀሳን የሚያደርግ ከተጠያቂነት እንደማያመልጥ ያስረግጣሉ።
እርሳቸው እንደሚሉት እንቅስቃሴው አሜሪካን አገር ብቻ ለሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና የመኖሪያ ፈቃድ ያላቸውን ኢትዮጵያውያንን ትኩረት ያደረገ ነው። ይሁን እንጂ በሌሎች አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ተመሳሳይ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ እየተነጋገሩ መሆናቸውንም ገልፀውልናል።
ጉዳዩን በተመለከተ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ንግግር አድርገው ከሆነ ጥያቄ ያነሳንላቸው አቶ አምሳሉ” ምንም ምክክርም ሆነ ንግግር አላደረግንም” በማለት የዜግነት ግዴታቸውን ለመወጣት ብቻ እንቅስቃሴውን እንደጀመሩ ነግረውናል።
ከምክር ቤቱ ጋር ግንኙነት ባይኖራቸውም በሚኖሩበት ሜኒሶታ ግዛት ተመሳሳይ እንቅስቃሴ ማድረግ እንደ ጀመሩ የነገሩን ደግሞ የአንድ ጥብቅና ቢሮ ባልደረባ የሆኑት አቶ ነጋሳ ኦዱዱቤ ናቸው።
እርሳቸውም ከአቶ አምሳሉ ጋር ተመሳሳይ ኃሳብ ነው ያላቸው፤ ‘ፈርስት አመንድመትን’ ጠቅሰው የጥላቻ ንግግር የሚያሰራጩን ከሕግ ፊት ማቅረብ እንደሚቻል ያረጋግጣሉ።
• “ሽብር ምንድን ነው ፣ አሸባሪ ማን ነው?” ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ
“በአሜሪካ የመናገርና ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ለብዙ ዘመናት የተከበረ ነው፤ ይሁን እንጂ ‘ፈርስት አሜንድመንት’ ላይ የተወሰኑ ገደቦች አሉበት” ይላሉ።
ከእነዚህም መካከል የሀሰት ንግግር፣ ስም ማጥፋት፣ ለወንጀል የሚያነሳሱ ንግግሮች፣ ወደ ኃይል ተግባር የሚያነሳሱና የሌላውን መብት የሚጥሱ ንግግሮች በሕጉ ተገድበው ይገኛሉ።
ተፅዕኖው ኢትዯጵያ ውስጥ በሚታይ ድርጊት ግለሰቦችን አሜሪካ ላይ ፍርድ ቤት ማቅረብ የሚያዋጣ ክርክር ነው ወይ? ስንል የጠየቅናቸው አቶ ነጋሳ ” የጁሪዝዲክሽን (የፍርድ ቤቶች የማየት ስልጣን) ጉዳይ አከራካሪ ነው። ነገር ግን ከሶ ፍርድ ቤት ከቀረበ በኋላ መከራከር ይቻላል፤ ውጤቱ ኢትዮጵያ ነው ብሎ መከላከል ይቻላል” ሲሉ ይህ በፍርድ ሂደት እንደሚታይ ይናገራሉ።
ከዚህም ባሻገር አብዛኛው ኢትዮጵያዊ የሚኖረው ጥገኝነት ጠይቆ በመሆኑ ይህንን ከሚቆጣጠረው ‘አሜሪካ ኢምግሬሽን ሰርቪስ’ (ዩ ኤስ ሲ አይ ኤስ) በክስ ሂደቱ ሊካተት እንደሚችል ይናገራሉ።
“እንደ ኢትዮጵያዊያን አገሪቷ ወደ ፍቅርና ሰላም እንድታመራ የሞራል ግዴታ አለብን” የሚሉት አቶ ነጋሳ ነገሩን ወደ ህግ ከመውሰድ ይልቅ የሚያዋጣው የኢትዮጵያ ደህንነት ግድ እንደሚለው ዜጋ መመካከር ነው ይላሉ።