
ሰኔ 21 ቀን 2011 (06/28/2019)
“ የምትመኘውን ነገር ተጠንቀቀህ ተመኝ፤ የተመኘኽው ነገር እውን ሊሆን ይችላልና” አሜሪካዊ አባባል።
በቅድሚያ፤ በሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. ብርቅዬ በሆኑ የሃገር ዜጎች ላይ በተፈፀመው ግድያ፤ ልባቸው ለተሰበረው የሟች ቤተሰቦች፤
ወዳጅ፤ ዘመድ፤ እና ጓደኞች፤ እንዲሁም በጥልቅ ላዘነው የኢትዮጵያ ሕዝብ መጽናናትን እመኛለሁ።
ረያ ካርሰን የተባለች እውቅ ደራሲ፤ “The Bitter Kingdom” በሚለው መጽሃፏ “Peace is such hard work.
Harder than war. It takes way more effort to forgive than to kill.” ትላለች። በግርድፉ ሲተረጎም “
ሰላም፤ ከባድ ሥራ ነው። ከጦርነትም ይከብዳል። ከመግደል ይልቅ፤ ይቅርታ ማድረግ፤ እጅግ ብዙ ጥረት ይጠይቃል” ማለት
ነው።
በሃገራችን የፖለቲካ ባሕል፤ እርስ በእርሳችን መገዳደል፤ አዲስ ባይሆንም፤ የሰኔ 15 ቀኑን፤ አሳዛኝ ግድያ፤ የተለየ
የሚያደርገው፤ አብዛኛው ሕዝብ እና መንግሥት ይቅር ሰለመባባል፤ እየሰበኩ ባሉበት እና፤ ወደ አዲስ የፖለቲካ አስተሳሰብ
እንዲሁም አዲስ የፖለቲካ አቅጣጫ ተስፋ ሰንቀን መንገድ በጀመርንበት ጊዜ መሆኑ ነው። ለመገዳደል አዲስ አይደለንም፤
በጠላትነት ለመፈራራጅ እና፤ ተቧድነን፤ ለመተላልቅ ዝግጁ ነን። በሃሳብ ተሟግተን ለመሸናነፍ፤ ብዙ የሚቀረን ይመስላል።
ሌላው ቀርቶ፤ ዛሬ እንኳን፤ ከዚህ ከደረሰብን መሪር ሃዘን ባለመማር፤ በየጥጋችን፤ በየጎጣችን፤ ተቧድነን፤ የጦርነት ታምቡር
እንደልቃለን። ሁሉም ጀግናው የእኔ ብሔር ነው፤ ጡንቸኛው እኔ ነኝ ይለናል። ሰከን ያሉ ሰዎች፤ ገላጋይ እንዳይሆኑ፤
የማህበራዊ ሚድያው፤ ትኩስ ጀግና፤ እንደሱ ያላሰበውን፤ እሱ እውነት ብሎ የተቀበለውን፤ ያልተቀበለውን፤ ያለምንም
ምህረት፤ ያላትማል። ትዕግስት የለም፤ “የሃሰት መረጃ ፋብሪካዎች” እንደ አሸን ፈልተዋል። ሁሉም ጣት ጠቋሚ ነው። ሁሉም
በብሽሽቅ የጀገነ ነው። በዚህ የቁልቁለት መንገድ ላይ ሆነን ግን እንዴት ነው ወደ መቻቻል ፖለቲካ የምንሄደው? እኔ ያልኩት
ብቻ መደረግ አለበት በሚል ግብዝነት፤ “ከእኔ በላይ ሃገር ወዳድ የለም” በሚል አጉል ጀብደኝነት፤ ሃገር መገንባት አንችልም።
ስንት ደም የፈሰሰበትን፤ ስንት ዋጋ የተከፈለበትን፤ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን የመገንባት እና፤ ሥልጣን የሕዝብ የማድረግ
ሕልም፤ እውን ለማድረግ የምችልበትን መንገድ እያጠበብን፤ ስለ ዲሞክራሲ፤ ስለ ሰብዓዊ መብት፤ ሰለመናገር እና መሰብሰብ
ነፃነት ብናወራ፤ ወሬ ብቻ ከመሆን አያልፍም። ምን ያህሉ የፖለቲካ ልሂቆቻችን ናቸው፤ ከራሳቸው፤ ከድርጅታቸው፤
እንዲሁም ከጎጣቸው በላይ፤ ለሃገር የሚያስቡት?
“ለኦሮሞ ያልሆነች ኢትዮጵያ፤ ለትግራይ ያልሆነች ኢትዮጵያ፤ ለአማራ ያልሆነች ኢትዮጵያ፤ ለሶማሌ ያልሆነች
ኢትዮጵያ፤ ወዘተ፤ ትበጣጠስ” በሚል ፈሊጥስ፤ እንዴት ወደፊት መራመድ እንችላላን? ስለአያቶቻችን እና አባቶቻችን፤
ብልህነት፤ ይቅር ባይነት እና መቻቻል፤ ነጋ ጠባ፤ የሚደሰኩር ትውልድ፤ ስለኢትዮጵያውያን ታላቅነት፤ ደረቱን ነፍቶ የሚናገር
ትውልድ፤ እንዴት በራሱ ትውልድ ውስጥ መቻቻልን፤ ይቅር መባባልን ከልብ ተቀብሎ ተግቶ አይሰራም? የዛሬይቱ ኢትዮጵያ፤
ገና ሲታሰብ እንኳን እጅግ የሚያደክም ብዙ ችግሮች እና ፈተናዎች አሉባት። እንኳን እየተናቆርን፤ ተባብረን እና ተዋደንም፤
ችግሮችዋን ለመፍታት ዘመናት ይፈጅብናል። ታድያ፤ መቼ ነው ቆም ብለን የምናስበው? ዛሬ እኮ፤ የፖለቲካ ብልጣ ብልጥነት
በማሳየት፤ አንዳችን አንዳችንን ለመብለጥ የምንተጋበት ጊዜ መሆን የለበትም። እንደ አውሮፓውያኑ እና፤ እንደ አሜሪካኖቹ
እኮ ሃገራችን፤ የፖለቲካ ቁማር የምትሸከምበት ትከሻ የላትም። መቼ ነው፤ ይህ የመጠላለፍ ፖለቲካ፤ የመገዳደል ፖለቲካ
ይሚያበቃው? ሰኔ 15 2011 ለፈሰሰው ደም ተጠያቂዎች ሁላችንም ነን። አንድ ቡድን፤ አንድ ብሔር፤ አንድ አካል ነው ብለን
የምናስብ ከሆነ ተሳስተናል። እጅግ በጣም ተሳስተናል።
እስቲ ሁላችንም፤ ባለፈው አንድ ዓመት የመጣንበትን መንገድ ዞር ብለን እንይ። ምን ያክል ወገን ተፈናቀለ? ምን
ያህሉ ሞተ? ምን ያህሉስ ተሰደደ? እንደ ዜጋ ሃላፊነት ባለመውሰዳችን፤ የሃገሬ ጉዳይ፤ የእኔም ጉዳይ ነው ባለማለታችን፤ ኮሽ
ባለ ቁጥር፤ መፍትሔ ፈላጊ ከመሆን ይልቅ፤ ሰዎችን ለማውገዝ እና ለማንጓጠጥ የምንሽቀዳደም መሆናችን ነው፤ ዛሬ
ለደረስንበት አሳዛኝ ወቅት ምክንያቱ። እከሌ ነው ብለን፤ ወደ ሌላው ጣት እንጠቁም ይሆናል፤ እራሳችንን በመስተዋት
ብንመለክት ችግሩ እኛው እራሳችን ሆነን እናገኘዋለን። በተደጋጋሚ እንደተነገረው፤ የአለን አንድ ሃገር ነው። ሌላውን ጎጥ
ጎድቼ፤ የእኔን ጎጥ እጠቅማለሁ፤ በለን የምናስብ ከሆነ፤ አርቀን ማሰብ ተስኖናል ማለት ነው። አንዱን ጎድቶ ሌላውን መጥቀም
አይቻልም። ምክንያቱም ነገ፤ እድሉ፤ እጣው ይዞራል እና፤ የዛሬው ተጎጂ ነገ ደግሞ ጎጂ ይሆናል እና፤ ልክ እንደአሁኑ፤ ዕጣ
ፋንታችን ተመሳሳይ አዙሪት ውስጥ መሽከረከር ይሆናል። ከዚህ አዙሪት ውስጥ ግን መውጣት እንዴት አቃተን? ለተቀረው
ዓለም መፍትሔ የሚያበጁ፤ ኢትዮጵያውያን እንዴት ለሃገራቸው መድሃኒት አጡ?
ወገን ወገኑን በሚያፈናቅልበት ሃገር፤ እንዴት ከድህነት መውጣት ይቻላል? ወገን ወገኑን በሚገድልበት ሃገር፤ እንዴት
በሰላም መኖር ይቻላል? ሁሉም ለጎጡ ወግኖ፤ ለእኔ ጎጥ ብቻ በሚል ሕዝብ ውስጥ እንዴት፤ የተባበረች አንድ ሃገር መፍጠር
ይቻላል? ለማኤሪካውያን ጥቁሮች ነፃነት ታጋይ የነበሩት ማርቲን ሉተር ኪንግ በማያሻማ ሁኔታ እንዳስቀመጡት፤ እንደ
ወንድማማች አብረን ለመኖር መማር አለብን፤ አለበለዚያ እንደ ቂል እርሰ በእርስ እንጠፋፋለን። እኛ እየተከተልን ያለነው
የቂል መንገድ ነው። ለምን? ማናችንም ዘላለማዊ አይደለንም። ለቀጣዩ ትውልድ እስከመቼ ነው ቂም እና የመገዳደል ባሕል
ትተንለት የምንሄደው? ይህንን ሁላችንም ቆም ብለን ማሰብ አለብን። ያለፈው ሳምንት በባሕር ዳር እና በአዲስ አበባ
ለተከሰተው አሳዛኝ ክስተት፤ ወደድንም ጠላንም፤ የእያንዳንዳችን የጣት አሻራ አለበት። ችግሩ የሁላችንም ነው፤ መፍትሄው
የሚመጣውም ከሁላችንም ነው። ይህን አምነን መቀበል አለብን። ይህ እንደማይደገምም በማያሻማ ሁኔታ ቃል መግባት
አለብን። በእንደዚህ ዓይነት አሳዛኝ ሁኔታ ለተሰዉት ብርቅዬ ዜጎች፤ “ነፍሳችሁን ይማር” ማለት፤ ጉንጫ አልፋ ነው የሚሆነው።
እነሱን የምናከብረው፤ እርስ በርስ ይቅር ስንባባል ነው፤ እነሱን የምናከብረው፤ የግድያ አዙሪቱን ስናቆም ነው።
ስለጀግንነታቸው በማውራት አይደለም የምንዘክራቸው፤ የምንዘክራቸው፤ ለሰላም እና ለመቻቻል የቆምን፤ የሰላም አርበኞች፤
የሰላም ጀግኖች መሆናችንን በተግባር ስናሳይ ነው። አንድ ነገር ከሆነ በኋላ መቆጨቱ ማንባቱ ትርጉም የለውም። እምባ ጠራጊ
ከመሆናችን በፊት፤ ሲጀመር፤ ያ እምባ እንዳይፈስ ነው ተግተን መስራት ያለብን።
በመገዳደል የፖለቲካ ባሕል፤ ማንም አሸናፊ ሆኖ የሚወጣ የለም። ይህንን ከሲሪያ፤ ከየመን፤ እንዲሁም ከራሳን ታሪክ
መማር አለብን፤ ቀይ ሽብር እና ነጭ ሽብር እኮ የትላንት፤ ድርጊታችን ነው። ሃገራችን በድህነት አረንቋ የምትታመሰው፤ ከዚሁ
የግድያ አዙሪት ውስጥ አልወጣ በማለታችን ነው። በቀልን ከውስጣችን እናሰወጣ። ከፍተኛ ቦታ የሰጠናቸው፤ ጎጠኝነት፤
ሥልጣን፤ መጠላለፍ፤ ተንኮል፤ የፖለቲካ ቁማር፤ እንዲሁም የአድማ ፖለቲካ፤ ከአስተሳሰባችን ተፍቀው ወጥተው፤ ፍትሕ፤
ሰላም፤ ይቅር ባይነት፤ እና መተሳሰብ እዚህ ከፍ ያለ ቦታ ላይ ሊቀመጡ ይገባቸዋል። እንተሳሰብ፤ አንድ እንሁን ማለት፤ አንድ
ዓይነት አስተሳሰብ ይኑረን ማለት አይደለም፤ የሃሰብ ልዩነቶቻችንን በውይይት እና በመቻቻል እንፍታቸው፤ ለማለት እንጂ።
በምንስማማው ላይ ተስማምተን፤ በማንስማማው ላይ ተቻችለን ሃገራችንን እንገንባ፤ ለቀጣዩ ትውልድም የተሻለ ነገር
እናስረክብ።
ከዓመት በፊት የተጀመረው የለውጥ ጉዞ፤ በምንም መልኩ፤ በመንግሥትም ይሁን በሌላ ሃይል ሊቀለበስም ሆነ
ሊዘገይ አይገባውም። ይህ ብዙ ዋጋ የተከፈለበት፤ እጅግ ብዙ ብርቅዬ ዜጎቻችንን ያጣንበት መሰረታዊ የመብት ጥያቂዎች እና፤
ሥልጣንን ለሕዝብ የማስረከብ ሥራ፤ አሁንም ገፍቶ መቀጠል አለበት። መንግሥት፤ ባለፈው አንድ ዓመት ባሳየው ሆደ ሰፊነት
እና፤ የመቻቻል የፖለቲካ ባሕል እንዲዳብር፤ የወሰዳቸው በጎ እርምጃዎች፤ አሁንም ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው። ባለፈው
አንድ አመት፤ በብዛት ክርክር እና ውዝግብ ያስነሳው “መንግሥት እርምጃ ይውሰድ፤ ሕግ ያስከብር” የሚሉ ጥሪዎች እና
ውትወታዎች ነበሩ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አሕመድም፤ “መንግስት ዲክታተር ለመሆን ጫፍ ላይ ነ ያለው” ሲሉ እባካችሁ
ጉልበት እንድንጠቀም አትግፉን፤ ዓይነት ተማጽኖ በተደጋጋሚ አሰምተዋል። ሰሚ ግን አልተገኘም። ብዙው የፖለቲካ “ሊቅ”
ሲወተውት የነበረው “ሕግ አስከብሩ”፤ መንግስት ደካማ ነው፤ እያለ ነበር። እነሆ’ ካለፈው እሁድ ጀምሮ፤ በአፈሳ እና እስራት
ታጅቦ፤ መንግሥት ጉልበቱን አፈርጥሞ ብቅ ብሏል። አሜሪካኖች፤ “የምትመኘውን ነገር ጠንቀቀህ ተመኝ፤ እውን ሊሆን
ይችላል እና” ይላሉ። አሁን ደግሞ፤ እነዛው ሕግ አስከብሩ፤ መንግስት ተዳክሟል፤ ሲሉ የነበሩ ሃይሎች፤ መንግሥት ሕግ ጣሰ
ማለት ጀምረዋል። ይህ “የገመድ ጉተታ” የሚመስል ነገር እስከመቼ እንደሚቀጥል ግልጽ አይደለም።
አንድ ግን መታወቅ ያለበት ነገር አለ። መንግሥት ሕግ ያስከብር ማለት፤ ያለአግባብ ይሰር ወይም ይግደል ማለት
አይደለም። ሕግ ያስከብር ማለት፤ በወንጀል ጠርጥሮ የሚያስራቸውን ዜጎች በማስረጃ ይጠይቅ፤ ሰብዓዊ መብታቸውን
ያክብር፤ ከወንጀል ነፃ ከሆኑ፤ በአስቸኳይ ይፍታቸው። ወንጀል ሰርተዋል የተባሉትም በአስቸኳይ፤ ክስ ይመስረትባቸው።
ክሳቸውም፤ ለሕዝብ ግልጽ በሆነ፤ ፖለቲካዊ ባልሆነ ግን ሕጋዊ በሆነ የፍርድ ሂደት ይረጋገጥ። ሕግ በማስከብረ ጎን ደግሞ፤
ቀደም ብሎ መስፋት የጀመረው የፖለቲካ ምህዳር እንዳይጠብ፤ ባለሥልጣኖች፤ ያላቸውን የመንግሥት ሃይል ተጠቅመው፤
በማንም ላይ ፖለቲካዊ እርምጃ እንዳይወስዱ ማስገንዘብ፤ መከታተል፤ ሥልጣናቸውን ያለአግባብ በሚጠቀሙም ላይ፤ ተገቢ
እርምጃ መውሰድ ማለት ነው።
ሌሎቻችንም፤ በሃገሪቱ ፍትሃዊ ስርዓት እንዲኖር ግፊት ማድረጋችንን መቀጠል፤ ተጠርጣሪ የተባሉ ሰዎች ሲታሰሩ፤
ምንም መረጃ ሳይኖረን “ጎጤ ስለሆነ ነው የታሰረው” የሚለውን ትርከት ማቆም፤ የሃሰት ዜናዎችን አለመቀበል አለማሰራጨት፤
እንደ ዜጋ ሃላፊነት መውሰድ፤ የሚሰማንን ነገር ስርዓት ባለው መንገድ መግለጽ፤ ብሔር ተኮር ጥቃት ማቆም፤ ሕግ ማክበር፤
ከጥላቻ ፖለቲካ መታቀብ፤ የሚያጠፉ ሰዎችን መገሰጽ፤ ወንጀል ሲፈፀም፤ ለሕግ አስከባሪ አካላት ማሳወቅ፤ የሌሎችን መብት
ማክበር፤ እና እንደ ዜጋ፤ ግዴታችንን መወጣት ይጠበቅብናል። ይህቺን ሃገር፤ ማዳን፤ መገንባት፤ ማሳደግ፤ እና ከትውልድ
ትውልድ ተሻጋሪ የሆኑ ተቋማት ልንገነባ የምንችለው፤ በሁላችንም ጥረት፤ አስተዋጽኦ፤ እና ትግል፤ እንጂ በጥቂት ግለሰቦች፤
ቡድኖች፤ በመንግሥት፤ ወይም በፖለቲካ ድርጅቶች፤ ብቻ አይደለም። ላለፈው አንድ ዓመት፤ ተስፋ የሰነቅንበት ለውጥ
እንዲመጣ፤ ሁላችንም ጮኸናል፤ ሁላችንም እንደየመጠኑ ዋጋ ከፍለንበታል። ለውጡን ያመጣው ግለስብ፤ አንድ ቡድን፤
ወይም አንድ ብሔረሰብ አይደለም። ለውጡም የመጣው ባለፉት ጥቂት ዓመታት ብቻ በተደረገ ትግል አይደለም። እዚህ
ለመድረስ፤ ወደ ግማሽ ምዕተ ዓመት ገደማ ፈጅቷል፤ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ሕይወት ገብረናል። በተለይ “ለውጡን
ያመጣሁት እኔ ብቻ ነኝ” የሚሉ ሃይሎች ቆም ብለው ያስቡ። ከተባበርን፤ ሃገራችንን ከውድቀት እናድናለን፤ እንደቂሎች
ከተናቆርን፤ ሃገር አይኖረንም። ኢትዮጵያን ዳግማዊት ሶሪያ የማድረግ እና ያለማድረግ፤ ምርጫው የእኛና፤ የእኛ ብቻ ነው።
ቸሩ እግዚአብሔር ኢትዮጵያን እና ሕዝቦቿን