July 3, 2019

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በትናንትናው ዕለት በህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ተገኝተው ስለወቅታዊው የፖለቲካ ቀውስ ለቀረበላቸው ጥያቄ ከሰጧቸው መልሶች መሃል፣ ከመፈንቅለ መንግስቱ በፊት እነዚሁ ሃይሎች ኦሮሞው የፌዴራል ሥልጣኑን ያዘው ብሎ ዘመቱብን ብለዋል። ቀጥለውም፣ ኦሮሞ ያልተገባውን ሥልጣን አልያዘም፣ ምክርቤቱም መመርመር ይችላል ብለዋል። ከሳምንታት በፊትም በደሴ ከህዝብ ጋር ባደረጉት ውይይት ላይም እኔ ወደ ሥልጣን ከመጣሁ ኦሮሞ ያልተገባውን ሥልጣን ይዞ ከሆነ በ24 ሰአት ውስጥ ሥልጣኔን እለቃለሁ ብለው ተናግረው ነበር። ይህንንም ተከትሎ ጋዜጠኞችና የማህበራዊ ሚዲያ አክቲቪስቶች በመከላከያና ደህንነነት መዋቅሩ ውስጥ የኦሮሞዎች የተብዛዛ ሥልጣንን በመተንተን ጠቅላይ ሚኒስትሩን ሲሞግቷቸው ሰንብተዋል።

ዶክተር አቢይ ምክርቤቱ ኦሮሞ ያልተገባ ሥልጣን መያዙን መመርመር ይችላል ቢሉም፣ ለምክርቤቱ የዓይን እማኝ ሆነው መቅረብ ከሚችሉ ሰዎች ግንባርቀደም የሆነውን አቶ ማስተዋል አረጋን መፈንቅለ መንግስት ካሉት ድራማ ጋር አያይዘው እስርቤት ወርውረውታል የሚል ዜና እየደረሰኝ ነው። ህገመንግስቱ የሰጠውን የሃሳብ ነፃነት በማመን የሚያየውን የዘር መድልኦና በተለይ የአማራ ሠራተኞችና ፕሮፌሽናልስ መገፋትን በመረጃ እያስደገፈ የሚከራከርን ሰው ወህኒ መወርወር መፍትሄ እንደማይሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሊረዱ ይገባል። አቶ ማስተዋል አረጋም ከደረሰበት የግፍ እስር በአስቸኳይ ሊፈታ ይገባል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተደጋጋሚ “ኦሮሞ ያልተገባውን አልወሰደም” የሚል ሃረግ ስለሚጠቀሙ፣ በሳቸው አመለካከት “ለኦሮሞ የተገባው” ምንድን ነው፣ እስቲ አብራሩልን ብዬ መጠየቅ እወዳለሁ። እኔ በግሌ፣ ኦሮሞ በ2007 እአአ የህዝብ ቆጠራ ወቅት የነበረውን ቁጥሩን በተከተለ ቀመር የሚገባውን ቦታና ሥልጣን በየእርከኑ ቢይዝ ችግር የለብኝም፣ የብዙ ኢትዮጵያውያንም እምነት ነው ። ችግር ያስከተለው ኦዴፓ “ለኦሮሞ የተገባው” ብሎ የሚያምነው የ2007 የህዝብ ቆጠራ ውጤት ሳይሆን፣ ጃዋርና ፀጋዬ አራርሳ ከደመና ዘግነው የቀመሩት ኦሮሞ ከኢትዮጵያ ህዝብ 50% ነው የሚል ጀዝባ ቀመር ስለሆነ ነው ።

ዶክተር አቢይ ፓርቲያቸውን ኦዴፓን የ2007 የህዝብ ቆጠራ ውጤትን እንዲቀበል ማድረግ ከቻሉና የፌዴራል ሥልጣኖች የኬኛና ኢትዮጵያን በፈረቃ ቀመርን ተከትለው ሳይሆን የታወቀውን የ2007 የህዝብ ቆጠራ ስሌት ተከትሎ እስከተስተካከለ ድረስ፣ የሚያጣላን ነገር እንደማይኖር ለመግለፅ እወዳለሁ። እስከዚያው ግን ለውጥ መጥቷል ብሎ ተማምኖ በጉምሩክ ውስጥ ያየውን አድልኦ በልበሙሉነት ያቀረበውን ጀግና ከሥራ ከመታገዱ አልፎ ወደ ወህኒ መወርወር አያቀባብርም። የወጣት ፕሮፌሽናሉን ሙግት ያላደመጣችሁ፣ ከታች የተያያዘውን የቪዲዮ ፋይል ተመልከቱ ። አቶ ማስተዋል አረጋ ይፈታ! ለውጥ መጥቷል ብሎ አምኖ የሚያየውን የዘር መድልኦ ከመቃወም ውጪ ያጠፋው ጥፋት ያለ አይመስለኝም።