July 3, 2019

Source: https://fanabc.com

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 25፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኤርትራና ሱዳን የሚዋሰኑባቸውን ድንበሮች ለመክፈት ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተነገረ፡፡   የሱዳን ወታደራዊ ምክር ቤት ምክትል ሊቀመንበር ሌተናት ጄኔራል ሞሀመድ ሃመዳን ዳጋሎ በኤርትራ ይፋዊ የስራ ጉብኝት አድርገዋል፡፡   ምክትል ሊቀምንበሩ በጉብኝታቸው ከኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር በበርካት ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ማድረጋቸውን የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስትር አቶ የማነ ገብረ መስቀል በትዊተር ገፃቸው አስፍረዋል፡፡   መሪዎች ውይይቱን ተከትሎ ሁለቱን ሀገራት የሚገናኙባቸውን ድንበሮች ለመክፈት እና ይህንን የሚቆጣጠር ኮሚቴ ለማዋቀር ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተጠቁሟል፡፡   ፕሬዚዳንት ኢሳያስ የሱዳን የፓለቲካ ሀይሎች የሽግግር ሂደቱ ሰላማዊ እንዲሆን የመደገፍ ሃላፊነት እንዳለባቸው መግለፃቸው ነው የተነገረው፡፡   በፈረንጆቹ 2018 ጥር ወር ኦማር አልበሽር ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን ለመከላከል በካሳላና እና በሰሜን ኩርዱፋን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጃቸውን ተከትሎ ሱዳን ከኤርትራ ጋር የሚያዋስናትን ድንበር መዝጋቷ ይታወሳል፡፡   ነገር ግን ፕሬዚዳንት ኦማር ሀሰን አልበሽር ሱዳን በከፍተኛ ህዝባዊ ተቃውሞ እየተናጠች በነበረችበት ወቅት ማለትም በነጮቹ 2019 ጥር ወር ላይ ከኤርትራ ጋር የሚዋሰኑበት ድንበር እንዲከፈት ውሳኔ አሳልፈው ነበር፡፡