3 July 2019
የአየርላንድ መንግሥት በኢትዮጵያ በ2012 ዓ.ም. ይደረጋል ተብሎ የሚጠበቀውን ምርጫ ለመደገፍ ከተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም (ዩኤንዲፒ) ጋር የ700,000 ዩሮ (23 ሚሊዮን ብር) የድጋፍ ስምምነት፣ ሐሙስ ሰኔ 27 ቀን 2011 ዓ.ም. ይፈራረማል፡፡
ዩኤንዲፒ ‹‹የኢትዮጵያን ዴሞክራሲ ለማጠንከር ምርጫን መደገፍ›› በሚባለው ፕሮግራም ቀጣዩ ምርጫ ተዓማኒ፣ ነፃና ፍትሐዊ እንዲሆንና የምርጫ ቦርድን ከምርጫ ጋር ተያይዞ ሊመጡ የሚችሉ ግጭቶችን የመተንበይና የመከላከል አቅም ለማሳደግ ድጋፍ እያደረገ ሲሆን፣ የአየርላንድ መንግሥት ድጋፍም በዚህ ፕሮግራም ሥር ተግባራዊ የሚሆን ነው፡፡
ሐሙስ ዕለት በአየርላንድ ኤምባሲ በሚደረገው የስምምነት ሥነ ሥርዓት፣ አዲሱ የዩኤንዲፒ የኢትዮጵያ ተወካይ ቱርሃን ሳሌህና የአየርላንድ አምባሳደር ሶንጂ ሃይላንድ ተገኝተው እንደሚፈራረሙ ታውቋል፡፡
ግንቦት 11 ቀን 2011 ዓ.ም. ዩኤንዲፒ ከገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴና ከኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ጋር ባደረገው ስምምነት፣ ለቀጣዩ ምርጫ የ40 ሚሊዮን ዶላር የድጋፍ ፕሮጀክት መቅረፁ ተገልጾ ነበር፡፡
ከዚህ ውስጥ 34.6 ሚሊዮን ዶላር በተለያዩ የልማት አጋሮች እንደሚሸፍን፣ ዩኤንዲፒ ደግሞ ሁለት ሚሊዮን ዶላር እንደሚሸፍን፣ እንዲሁም በፕሮጀክት ትግበራ ወቅት የተቀረው 3.3 ሚሊዮን ዶላር እንደሚሰበሰብ በወቅቱ ተገልጾ ነበር፡፡
ለዚህ ፕሮግራም አሥራ አንድ አገሮች ድጋፍ እንደሚያደርጉ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ስምንቱ ምን ያህል የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡
ከአሁን ቀደም የእንግሊዝ መንግሥት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጄረሚ ሃንት በኢትዮጵያ ባደረጉት ጉብኝት፣ ለምርጫ ድጋፍ የሚሆን 15.5 ሚሊዮን ፓውንድ በዩኤንዲፒ በኩል መለገሳቸው ይታወሳል፡፡ የእንግሊዝ መንግሥት ድጋፍ ለዚህ ዓላማ ከየትኛውም አጋር ከተገኘው ገንዘብ ትልቁ ነው፡፡