መነሻ ገጽ

3 July 2019 ታምሩ ጽጌ

የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ተፈቱ

በምርጫ ቦርድ የተመዘገቡና ሕጋዊ መሆናቸው የተረጋገጠ የፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎችና ኦዴፓን ወክለው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጭምር የፈረሙበት የቃል ኪዳን ሰነድ እየተጣሰ ነው ሲል፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አስታወቀ፡፡

‹‹ተጠርጥራችኋል›› ተብለው ከሌሎች የአብን አመራሮች ጋር ሰኔ 21 ቀን 2011 ዓ.ም. በአማራ ክልል በምዕራብ ጎጃም ዞን ሰከላ ወረዳ በክልሉ የፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር ውለው፣ አንድ ቀን ታስረው ካደሩ በኋላ በማግሥቱ ሰኔ 22 ቀን 2011 ዓ.ም. የተለቀቁት የአብን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ክርስቲያን ታደለ፣ እንዴት የቃል ኪዳን ሰነዱ እንደተጣሰ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

አቶ ክርስቲያን እንደሚናገሩት፣ አብን በምርጫ ቦርድ የተመዘገበና ዕውቅና የተሰጠው ሕጋዊ ፓርቲ ነው፡፡ በመሆኑም ፓርቲውም ሆነ የፓርቲው አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች ሕገወጥ ተግባር ከፈጠሩ እንዴት መጠየቅ እንዳለባቸው በቃል ኪዳን ሰነዱ ላይ ተቀምጧል፡፡ በተለይ አመራሮች ሕገወጥ ተግባራት ላይ ተሰማርተው ወይም ፈጽመው ከተገኙ ድርጊቱ የተፈጸመበት ክልል፣ ዞን ወይም ወረዳ በሚመለከተው አካል በኩል ለምርጫ ቦርድ ማሳወቅ አለበት ብለዋል፡፡ ችግሩ የከፋና ሕግን የተላለፈ ከሆነ፣ ድርጅቱን (ፓርቲውን) በአግባቡ ሕግን ተከትሎ ተጠያቂ ማድረግ ሲገባ፣ በተለይ ኦዴፓ በሚያስተዳድራቸው አካባቢዎች ያለ በቂ ምክንያት የአብን አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች እየታፈሱና እየታሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ንቃተ ህሊናቸው ከፍ ያሉ ምሁራን አመራሮቹንና አባላቱን ‹‹ለሰላምና መረጋጋት ሥጋት ናችሁ›› እየተባሉ መታሰራቸውን የጠቆሙት አቶ ክርስቲያን፣ አቶ ሀብታሙ ተሰማና አቶ ይሁንልኝ እንየው የሚባሉት የአብን የአዳማ (ናዝሬት) ከተማ ሰብሳቢና ምክትል ሰብሳቢ ስለታሰሩበት ምክንያት አስረድተዋል፡፡ አመራሮቹ የታሰሩት በአማራ ክልል ምንጃር አረርቲ ውስጥ በአማራ አርሶ አደሮችና በኦሮሞ ተስፋፊ ብሔርተኞች መካከል ተፈጥሮ በነበረ ግጭት ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አመራሮቹ ፍርድ ቤት መቅረባቸውን ገልጸው፣ ፖሊስ የከሰሳቸው ግን በግጭቱ ወቅት አብን የገንዘብ ዕርዳታ ያደርግ እንደነበርና ያንን ገንዘብ ያደርሱ የነበሩት እነሱ መሆናቸውን በመግለጽ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

አብን ሕጋዊ ፓርቲ መሆኑንና መከሰስም ሆነ መክሰስ እንደሚችል እየታወቀ፣ አመራሮችን እያፈሱ ማሰር ግን ተገቢ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡ የዘር ጥቃት በሚመስል ሁኔታ የነቁና የሚንቀሳቀሱ የፓርቲውን አመራሮችና ደጋፊዎች ማሰር ተገቢ አለመሆኑንም በድጋሚ አክለዋል፡፡ ድርጊቱ የፖለቲካ እስር መሆኑን፣ በተለይ በተለያዩ ቦታዎች የታሰሩ ከ300 በላይ አባላትና ደጋፊዎች ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውንና ቤተሰቦቻቸው እንደማይጠይቋቸው ተናግረው፣ ይኼ የመብት ጥሰትም ጭምር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ሁሉንም ሁኔታ ለኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ማሳወቃቸውንና መንግሥት ሕጋዊ ዕርምጃ በመውሰድ ችግሮቹን ያስተካክላል የሚል ዕምነት እንዳላቸው ገልጸው፣ መንግሥት ይኼንን ድርጊት የማያስተካክል ከሆነ በሰላማዊና በሕጋዊ መንገዶች ፓርቲያቸው የሚወስናቸው ዕርምጃዎች እንደሚኖሩም አስታውቀዋል፡፡

አቶ ክርስቲያን እሳቸው በምን ምክንያት እንደታሰሩና እንዴት እንደተፈቱ ተጠይቀው እንዳስረዱት፣ ወደ አማራ ክልል የሄዱት በክልሉ አመራሮች ላይ በተፈጠረው ግድያ ምክንያት ለቀብር ነው፡፡ በዚያው አጋጣሚ ግን በተለይ የክልሉ ሕዝብ አስደንጋጭ ሁኔታ ውስጥ በመግባቱ ወደ ሰላምና መረጋጋት እንዲመለስ በአካባቢው ባለው መዋቅራቸው አማካይነት፣ ከክልሉ አመራሮች ጋር ተቀራርበው እንዲሠሩ ለአብን አመራሮች አቅጣጫ ለመስጠት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ በሕዝቡ ላይ የደረሰውን ከፍተኛ መደናገጥ በመቀራረብ፣ በመመካከርና ሰላምንና ደኅንነቱን ከማስጠበቅ አኳያ ያንን ማድረግ እንደ ፓርቲም፣ እንደ ሰውም ተገቢ እንደነበር አክለዋል፡፡

በሌላ በኩል በምዕራብ ጎጃም ዞን ሰከላ ወረዳ የአዴፓ አመራሮች የቆየና የግል አለመግባባትን እንደ አዲስ በማስመሰል በወቅቱ የተፈጠረውን ሐዘንና አለመግባባት እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቅመው፣ ያሰሯቸውን የአብን አመራሮች ለመጠየቅና ለማነጋገርም ጭምር መሄዳቸውን አቶ ክርስቲያን ተናግረዋል፡፡

እሳቸው እንደ አመራር ያንን ለማጣራትና ችግሩን በመነጋገር ለመፍታት፣ እንዲሁም በቀጣይ በሚያግባቡ ነገሮች ላይ እንዴት አብረው መሥራት እንዳለባቸውና ልዩነቶቻቸውን አክብረው እንዲቀጥሉ ለመነጋገር፣ ከሌሎች ሁለት አመራሮች ጋር ወደ ሥፍራው በሕዝብ ትራንስፖርት እያመሩ እያሉ፣ መንገድ ላይ በክልሉ የፀጥታ ሠራተኞች መያዛቸውን ተናግረዋል፡፡

የፀጥታ ሠራተኞቹ፣ ‹‹ለፍተሻ ተባበሩን›› ብለው ከትራንስፖርት ካስወረዷቸውና ከፈተሿቸው በኋላ፣ እነሱን ለይተው ከፊት ለፊታቸው የቆመ አምቡላንስ ውስጥ እንዲገቡ እንደጠየቋቸው አቶ ክርስቲያን አስረድተዋል፡፡ ‹‹ለምን? ምን አጠፋን?›› የሚል ጥያቄ ሲያቀርቡ፣ ‹‹ተጠርጥራችኋል›› በመባላቸው፣ ‹‹ከተጠረጠርንማ መወሰድ ያለብን በፖሊስ መኪና እንጂ ለወላዶች ማመላለሻ በተመደበ አምቡላንስ አይደለም፤›› የሚል ምላሽ መስጠታቸውን ገልጸዋል፡፡ እነሱ የሚወሰዱት በአምቡላንስ እንደሆነ ሲነገሯቸው፣ ‹‹ከዚህ በፊት ወስዳችሁ ሊሆን ይችላል፣ ነገር ግን እኛ በዚህ አንሄድም፡፡ አምቡላንስ የራሱ የተመደበበት ሥራ አለው፤›› በማለታቸው ተሳፍረውበት በነበረው የሕዝብ ትራንስፖርት ወደ ወረዳው እንዳደረሷቸው አስረድተዋል፡፡

ወረዳው ጽሕፈት ቤት ሲደርሱ የወረዳው ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ከእሳቸው ጋር የነበረውን አመራር፣ ‹‹እንዴት ይኼንን ሽፍታ ይዛችሁ ትመጣላችሁ?›› ሲሉ፣ እነሱ ተፎካካሪና ሕጋዊ ፓርቲ መሆናቸውን በማስረዳት እንደዚያ ማለታቸው ተገቢም ሕጋዊም እንዳልሆነ ሲነገሯቸው፣ ‹‹የምታቀርቡት የሕግ ጥያቄ እዚህ አይሠራም፤›› በማለት ምላሽ እንደሰጧቸውም አክለዋል፡፡ የአካባቢው ሕዝብ መታሰራቸውን ሰምቶ ወደ ጽሕፈት ቤቱ በመምጣት ላይ ስለነበር፣ ተጨማሪ አታካራ ውስጥ ላለመግባት ዝምታን መርጠው ታስረው ማደራቸውንም ተናግረዋል፡፡

ቅዳሜ ሰኔ 22 ቀን 2011 ዓ.ም. የታሰሩበትን ምክንያት ሲጠይቁ ፈርተውና ጠርጥረው እንጂ ምንም ጥፋት እንዳላጠፉ ነግረዋቸው፣ እሳቸውን (አቶ ክርስቲያንን) በመልቀቅ የአካባቢው ተወላጅና ነዋሪ የነበረውን የአብን አመራር ግን የቆየና ለእሳቸው የማይነግሯቸው የተጠረጠረበት ጉዳይ እንዳለ እንደነገሯቸውም አስረድተዋል፡፡ አመራር ሆነው የዓላማ ጓደኛቸውን ትተው እንደማይሄዱ ሲገልጹላቸው፣ ሰኞ ሰኔ 24 ቀን 2011 ዓ.ም. እንደሚፈቷቸው ቃል ገብተውላቸው ቢለያዩም ቃላቸውን አክብረው እንዳልፈቷቸው ገልጸዋል፡፡ ፍርድ ቤት በማቅረብም ለተጨማሪ ምርመራ ሰባት ቀናት ጠይቀው፣ እንደተፈቀደላቸውም ማወቃቸውን ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን ድርጊቱን የዞኑም ሆኑ የክልሉ አመራሮች ሳያውቁ በቂም በቀል የሰከላ ወረዳ ኃላፊዎች እንዳደረጉት ተናግረዋል፡፡

በሰከላ ወረዳ ታስረው የሚገኙ የአብን አመራሮች የወረዳው ሰብሳቢ አቶ ሐሳቡ ሞላ፣ የምዕራብ ጎጃም ዞን ማኅበራዊ ጉዳይ አስተባባሪ አቶ ከፍአለው ገበየሁ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡