ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ፅጌ

መንግሥት ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም ባህር ዳር ላይ ለተፈፀመው የአማራ ክልል ከፍተኛ ባለስልጣናት ግድያና የመፈንቅለ-መንግሥት ሙከራ ዋነኛ ተጠያቂ ናቸው ያላቸው የብርጋዴር ጄነራል አሳምነው ፅጌ ባለቤት ወይዘሮ ደስታ አሰፋ በፖሊስ መያዛቸውን ልጃቸው ማኅሌት አሳምነው ለቢቢሲ ገለፀች።

ማኅሌት እንደተናገረችው እናቷ በፖሊስ ከቤታቸው የተወሰዱት ትናንት ሐሙስ ዕለት አዲስ አበባ ውስጥ ኮልፌ አቅራቢያ በተለምዶ አሸዋ ሜዳ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ነው።

አዴፓ እነ ብርጋዴር ጄነራል አሳምነው ፅጌን “የእናት ጡት ነካሾች” አለ

“ሌሎችንም ከፍተኛ ባለስልጣናት የመግደል ዕቅድ ነበረ”

ማኅሌት እናቷ በመጀመሪያ የተወሰዱት እዚያው አካባቢ ወደሚገኘው አሸዋ ሜዳ ፖሊስ ጣቢያ የነበረ ቢሆንም ዛሬ ጠዋት አያቷ ወደ ፖሊስ ጣቢያው ሄደው ሲጠይቁ “ወደ ሌላ ቦታ” መወሰዳቸው እንደተገለፀላቸው ትናገራለች።

የብርጋዴር ጄነራል አሳምነው ልጅ ማኅሌት ለቢቢሲ እንደተናገረችው ከጥቂት ቀናት በፊት መላ ቤተሰባቸው ለሃዘን ላሊበላ በነበረበት ወቅት አያቷ (የእናቷ እናት) እና የቤት ሰራተኛ እንዲሁም የጎረቤት ምስክር ባለበት ቤታቸው በፖሊስ ተፈትሾ አንድ የቤት መኪና፣ ላፕቶፕና የተለያዩ ማስረጃዎች መወሰዳቸውንም ገልፃለች።

ማኅሌት ጨምራም እንደተናገረችው ፖሊስ በድጋሚ ለምርመራ በማግስቱም ወደ መኖሪያ ቤታቸው መጥቶ ነበር።

ቢቢሲ ስለወይዘሮ ደስታ አሰፋ በፖሊስ ቁጥጥር ስር መሆን በተመለከተ ከፌደራል ፖሊስም ሆነ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ለማጣራት ያደረግነው ሙከራ ለጊዜው አልተሳካም።

“ብ/ጄኔራል አሳምነውን ቀድቻቸዋለሁ” ጋዜጠኛ ፋሲካ ታደሰ

“በዚህ መንገድ መገደላቸው ከፍተኛ የፀጥታ ችግር መኖሩን ያሳያል” ጄነራል ፃድቃን

የአባቷ ወንድም የብርጋዴር ጄነራል አሳምነው ቀብር ላይም እንዳልተገኙና ቤተሰብ እስካሁም የት እንዳሉ ባለማወቁ መጨነቁንም አክላለች።

ብርጋዴር ጄነራል አሳምነው ጽጌ በባህር ዳር ከተማ ውስጥ ተሞክሯል የተባለው መፈንቅለ መንግሥት መሪ እንደነበሩና በክስተቱ ለሞቱት ከፍተኛ የአማራ ክልል ባለስልጣናት ተጠያቂ መሆናቸው በተደጋጋሚ ተገልጿል።

ከጥቃቱ የተረፉ ከፍተኛ የክልሉ ባለስልጣናትም ብርጋዴር ጄነራል አሳምነው ጥቃቱን በአካል ሲመሩ እንደነበር ምስክርነት የሰጡ ሲሆን የእርሳቸው ነው ተብሎ በድምጽ በወጣው ማስረጃም በአመራሩ ላይ እርምጃ መወሰዱን ሲናገሩ ተደምጧል።

ብርጋዴር ጄነራል አሳምነው ከግድያው ጥቂት ቀናት በኋላ ከባህር ዳር ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኘው ዘንዘልማ በሚባል ስፍራ ከጸጥታ ኃይሎች ጋር በተደረገ የተኩስ ልውውጥ መገደላቸውን መንግሥት ማስታወቁ ይታወሳል።