የሀገር አለኝታን እያብጠለጥሉ (ጀግናን ለመውለድ ይቸግራል)
የኮሎኔል ደመቀ አውጋዦች እነማን ሊሆኑ ይችላሉ?
መወቃቀስ ልክ እና ስርአት ቢኖረው ምን ትላላችሁ?
ለዚህ መጣጥፍ ያበቃኝ ሁነኛ ነገር ምናልባት ለብዙወች ቀላል ሊሆን ይችላል ግን በበኩሌ የምርግ ያክል የከበደ እና ያስከትላል የምለውም የዚያን ያክል የከፋ ሆኖ ስለታየኝ ነው። ማህበራዊ ሚዲያውን ስገልጥ የኮሎኔል ደመቀ ፎቶ ወደታች ተዘቅዝቆ አየሁ። በዚህ አላቆምሁም አከታትየም የህወሓቷ አዲስ ጠበብት የሆነው ባሻው ተናጋሪ ጌታቸው ረዳ የተባለ ያስተላለፈውን ማስጠንቀቂያ እና ዛቻም ተመለከትሁ። ወረድ ብየም የጠቅላይ ሚኒስቴሩን የፓርላማ ንግግር አዳመጥሁ። ነገሮች መጦዛቸውን እና መደበላለቃቸውን ገላጭ ከዚህ በላይ አያስፈልገኝም።
በበኩሌ መጀመሪያ ሰበአዊ መብት ይከበር ባይ ነኝ እናም አሁንም የታሰሩ ይፈቱ እላለሁ። ይህ በሰሞኑ የተከሰተ ጉዳይ በስርአቱ ሾፌሮች በራሳቸው ውስጥ የተፈጠረ እንደሆነ ግልጽ ነው። የስርአቱ ባለቤቶች ገመናቸው በአደባባይ ወጦ እስኪሰጣ እና ለሀገር ጠንቅ መሆን እስኪችል መጠበቃቸው። እርስ በእርስ ተፋጅተው ለሀገር እና ለሕዝብ መለያየት ምክንያትም እየሆኑ መምጣታቸው። በዚሁ በድርጅታቸው ውስጥ በተነሳ መተራመስ እና መፋጀት ሌላውን እስርቤት ማስገባታቸው። የእራሳቸውን የቅራኔ አያያዝ እና አፈታት እና አይን ያወጣ ድክመት በሌሎች ማሳበብ እና እንግልት ውስጥ መክተት። ይህም አግባብነት የሌለው ሀገራችንን መልሶ ወደትርምስ የሚወስድ፤ ዜጎች እፎይታ አግኝተው ወደ ስራ ትጋት እና ኑሮን ማቸነፍ ከመሄድ ይልቅ አሁንም የስጋት እና የሰላም እጦት ላይ እንዲያተኩር ያደርገዋል። የሀገርን ኢኮኖሚም አምራቹ በሌላ የስነልቦና ችግር ላይ ሲጠመድ ከኢኮኖሚው ይልቅ ደህንነቱ ላይ ቅሚያ ይኖረዋል።
ይህን ካልሁ በኋላ በህወሓት እና ዘረኛ ድርጅቶች አላማ አማራ ችግር ነው በሚል አሁንም የነደፉትን የትግል ፕሮግራም ሳይቀይሩ የቀጠሉ እንደሆነ ይታወቃል። ዜጎች በአማራነታቸው ላለፉት 28 አመታት በብዙ ቦታወች ተፈናቅለዋል፣ ተገድለዋል፣ ታስረው አገር ለቀው እንዲሰደዱ ሆኗል። ለአለፉት 28 አመታትም ስርአቱን ለመጣል ሰፊ መስዋእትነት ተከፍሏል። ያ ሁሉ ጥረት ሳይሳካ ቆይቶ በ2016 (2008) በሰሜን ጎንደር፣ ጎጃም፣ እና ወሎ በአማራው ክልል ለተቀጣጠለው ትግል የመጀመሪያው ኤንጅን የኮሎኔል ደመቀ ለገዳይ አለመንበርከክ እና ፍጹም ቁርጠኛ የሆነ የአይበገሬ ተግባር ነበር። እናም ህወሓት እግሯ የነቀለም ይህ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ግዝፈት እና ጥልቀት ስላገኘ ነበር። ከዚህ በፊት ያልሁትን ልድገመው። ጠላታችን ህወሓት አፈገፈገች እንጅ እጅ አልሰጥችም። ወደተሻለ ቦታ ጥግ ይዛ ስራዋን ቀጠለች እንጅ ትግል ለምኔ ብላ አልተቀመጠችም። አሁንም ጠላቴ “ትምክህተኛው” አለች እንጅ ጸፀት ኖሯት ተሳሳትሁ ሳይሆን አሁንም ትግሌን ቀጥየ ጠላቴን እፋለማለሁ በማለት ሰፊ ወታደራዊ እና የሀብት ክምችት በማዘጋጅት ላይ ናት። ይህ በዚህ እያለ በማህበራዊ ሚዲያ እየታየ ያለው ጠላቶች የቀደዱለትን ቦይ ተከትሎ የሚነጉድ እና ሰድቦ ለሰዳቢ የሚሰጥ ሁኔታወችን መፍጠር በየትኛውም ሎጅክ ጤነኛ ሊሆን አይችልም።
በተቃራኒ ሀሳብ ለበጎ ብሎ ያቀረበን መዝለፍ ባህላችንም አይደለም። በይበልጥ የኮሎኔል ደመቀን ፎቶ ቁልቁል ተገልብጦ በማየቴ ጎበዝ ጀግናን ገድሎ ፈሪ መሪ እንዲሆን ይፈለጋል? ወይንስ ሁልግዜ ጀግናን እየገደልን አገር እና ወገንን አውላላ ሜዳ መጣል ለምዶብን ነው? በላይ ዘለቀን በመጨረሻ ሰአት መንግስቱ ነዋይ በገመድ ይስቀሉት እንጅ ሽፈራውን ገድለው እጅጉን አቁስለው እሱን እጁን የያዙት የራሳችን ሰወች አርበኛ የምንላቸው ስማቸውን ለመጥራት ከታሪካችን የማይመጥነው አርበኞች ነበሩ። አንድ ወንድምን መስደብ ማዋረድ ጀግንነት የሚመስለው ፈሪ ካለ ተሳስቷል ጉዳት ለሕዝባችን ነው። በይበልጥም በጠላቶቹ ለተነጣጠረበት ሕዝብ። ምንም ዋጋ ተከፍሎ ውሾን ያነሳ ውሾ ተብሎ የሕዝባችንን አንድነት መጠበቅ ትልቅ ነገር ነው። ግራ ቀኙን እያብጠለጠልን የጠላታችን የህወሓትን ስራ ከሰራንላት ክፉ ታሪክ የማይሽረው በደል ይሆናል።
እንደኔ በትናንትናው ውሎ በጠቅላይ ሚኒስቴሩ የተነገሩ አረፍተነገሮች አግባብነት የሌላቸውን መንቀስ ይቻላል። በጅምላ በውጭ የሚኖሩ ወገኖችን የዘለፉበት ተገቢ አልነበረም። የጅምላ ወቀሳ ችግሩ ብዙ ነው። በይበልጥም እርሳቸውን በከፍተኛ ቁጥር ደግፎ የተቀበላቸውን ስርአቱ ለስደት የዳረገውን ዜጋ የመውቀስ ልክ እና ስፍር ይፈልጋል። በበኩሌ ለምሰራው ሀላፊነት ይሰማኛል።፡በተጨማሪ ለማስገንዘብ እርሳቸው እና ጓዶቻቸው ለዚህ ስርአት በሚሰሩበት ዘመን ጭምር የታገልን ለወገናችን የጮህን፣ ሀገር እንዳትፈርስ በአለም አደባባዮች እግዞ ያልን ዜጎች በዚህ መልክ መዘለፍ አግባብ የለውም ባይ ነኝ። ይታረም ልክ እና መጠንም ሊኖር ይገባል ለምንሰነዝረው ወቀሳም ይሁን ነቀፌታ። በአንድ መሪ ላይም እንዲህ አይነት ስሜት እንዳይታይ እንመክራለን።
የግል እምነቴ፦ በማህበራዊ ሚዲያ ለምትሳተፉ የወዳጅ እና ጠላት ፍረጃን አግባብ በሆነ ልንተገብር ይገባል። ወዳጅ ሊሆን የሚችልን ወገን ያላግባብ መገፍተር የሚጠቅም ለጠላት ነው። አንድን ሰውም ሆነ ቡድንን ከመዝለፍም ከመፈረጅም በፊት ጉዳት ከጥቅሙ ሚዛን ላይ አስቀምጦ ማየት ይጠቅማል። በጥቅል ግን በይበልጥ በአማራ ስም አማራን መከፋፈል ይቁም። በማወቅ ባለማወቅ የሚሰነዘሩ ጎጅ አስተሳሰቦች ይገደቡ።
ሁላችንም የምናውቀው የህወሃት ፋይናንስ በዲጅታል ሚዲያ ጠንክሮ እየሰራ ስለሆነ እርስ በእርሳችን እንዳያባሉን ብሎም ይህን መከረኛ ሕዝብ እንዳይነጣጥሉ ስርአት ይኑር እላለሁ በበኩሌ። በእርግጠኝነት ጠላት አሁን እጅግ የሚያሰጋው ተደራጅቶ የሚጠብቅ ከህወሓት መንደር ነው። እነሄርማን ኮህን ግዜ ጠብቀው አላዘኑልንም ዘለፉን እንጅ። እናም እየተስተዋለ ይሁን።
እግዚያብሔር ኢትዮጵያን ከክፉ ይጠብቅ