July 5, 2019

BBC Amharic : ኢትዮ ቴሌኮም ከጠቅላላ የድርጅቱ አክሲዮን ድርሻ እስከ 49 በመቶውን ለሽያጭ በማቅረብ አብላጫ ድርሻውንና የቦርዱን አስተዳደር ይዞ እንዲቀጥል ተወሰነ።

ዛሬ ሰኔ 28 ቀን 2011 ዓ. ም የገንዘብ ሚኒስቴር በሰጠው መግለጫ፤ ኢትዮ ቴሌኮምን በከፊል ወደ ግል የማዘዋወሩን ሂደት ለማስፈጸም ነጻና ገለልተኛ የኮሙኒኬሽን ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን እንዲቋቋም የሚፈቅድ አዋጅ መውጣቱም ተገልጿል።

ባለሥልጣኑ ሁለት ተጨማሪ የቴሌኮሙኒኬሽን ድርጅቶችን በግልጽ ጨረታ አወዳድሮ ወደ ገበያ እንዲገቡ እንደሚያደርግና ሂደቱ በ2012 ዓ. ም ሦስተኛ ሩብ ዓመት እንደሚጠናቀቅም ተገልጿል።

አሁን መንግሥት የቅድመ ፕራይቬታይዜሽን (በመንግሥት ይዞታ ሥር ያሉ ተቋሞችን ወደ ግል የማዘዋወር) ሥራ በማከናወን ላይ ይገኛል ተብሏል።

ኢትዮ ቴሌኮም የመሰረተ ልማት መስመር ዝርጋታና የአገልግሎት አቅርቦት በተባሉ ሁለት ዘርፎች ይደራጃልም ተብሏል።

የመስመር ዝርጋታው ዘርፍ ዓለም አቀፍ መገናኛዎችን፣ አገር አቀፍ ፋይበር ኦፕቲክ፣ ለኔትወርክ ጠቃሚ የሆኑ እንደ የሞባይል ኔትወርክ ማማ (ሴሉላር ታወርስ) ያሉትን ሥራዎች የመገንባት ድርሻ ሲኖረው፤ የአገልግሎት ዘርፉ የሞባይል፣ የኢንተርኔት እና የመደበኛ ስልክ የችርቻሮ ሽያጭ ኃላፊነትን ተረክቦ እንደሚሠራ ተመልክቷል።

ዓለም አቀፍ የቴሌኮም ድርጅቶች ወደ ኢትዮጵያ ገበያ ሲገቡ፤ የውጪ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ከመሳብ ባሻገር፤ የአገልግሎት ክፍያ እንደሚቀንስ እንዲሁም የአገልግሎት ጥራትና ፍጥነት እንደሚጨምርም ተገልጿል።

የስኳር ኮርፖሬሽንን በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ ወደ ግል የማዘዋወር ሂደትን በተመለከተ የገንዘብ ሚንስቴር የድርጅቶቹን ንብረቶች ዋጋ፣ የፋብሪካውን አቅም እንዲሆም እያንዳንዱ ፋብሪካ በተቋቋመበት አካባቢ ሊከሰቱ የሚችሉ ጉዳቶችን አስመልክቶ ጥናት እየተካሄደ እንደሚገኝ በመግለጫው ተመልክቷል።

የስኳር ፋብሪካዎች አዋጅ እየተረቀቀ ሲሆን፤ ስኳር የማምረት፣ የመሸጥ፣ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡና ወደ ውጪ የሚላኩ የስኳር ምርቶችን ለመቆጣጠርም ይረዳል ተብሏል።

ከስኳር ፋብሪካዎች አምስቱ ወይም ስድስቱን ወደ ግል የማዘዋወር ሥራ ከስድስት ወር እስከ አንድ ዓመት እንደሚወስም ተገልጿል።
► መረጃ ፎረም – JOIN US