ባህር ዳር

የአማራ ክልል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሰኔ 15/2011 ዓ. ም የተፈጠረውን ክስተት ተከትሎ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር እንዲውሉ እያደረገ መሆኑን አስታውቋል።

የጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ሳባ ደመቀ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ እስከ አሁን ከ220 በላይ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሲሆን፤ የፌደራልና የክልል ዐቃቤ ሕጎች እንዲሁም መርማሪዎች ባሉበት ተጠርጣሪዎች ላይ ምርመራው እየተካሄደ ይገኛል።

የብ/ጄነራል አሳምነው ፅጌ ሚስት መታሰራቸውን ልጃቸው ገለጸች

በቁጥጥር ሥር የዋሉት ተጠርጣሪዎች ፍርድ ቤት ስለመቅረባቸውና ክስ ስለመመስረቱ መግለጽ እንደማይችሉ ምክትል ኃላፊዋ ገልጸው፤ “የተያዙት ሰዎች ዝርዝር ውስጥ ያሉ ናቸው” ብለዋል።

ከአማራ ክልል አመራሮች መካከል ተጠርጣሪ ተብለው የታሠሩ ሰዎች ነገሩ እስከሚረጋጋ መታሰራቸው ተገልጾ እንደነበር ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ “እስከሚረጋጋ በሚል አይደለም፤ እንደ ምርመራ ቡድን በሥራ ኃላፊነታቸው ወይም በተለያየ መንገድ ተጠርጥረው የሚያዙ ሰዎችን ሌብል [የተለየ ስያሜ] አልሰጠናቸውም” ሲሉ መልሰዋል።

የጠቅላይ ዐቃዐ ሕጉ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ሳባ፤ በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሰዎች በተከሰተው ነገር ተሳትፏቸው ምን ነበር? የሚለውን የምርመራ ሂደቱ እንደሚፈታውም አክለዋል።

“ሌሎችንም ከፍተኛ ባለስልጣናት የመግደል ዕቅድ ነበረ”

እንደ ጄነራል ተፈራ ማሞና ኮለኔል አለበል አማረ ያሉ የክልሉ አመራሮች የሰኔ 15ቱን ‘የመፈንቅለ መንግሥት’ ሙከራ በተመለከተ በቴሌቭዥን ማብራሪያ ሲሰጡ ነበር። ከድርጊቱ ጀርባ ናቸው ተብለው የተጠረጠሩት ብርጋዴር ጄነራል አሳምነው ፅጌ ‘አግተዋቸው ነበር’ ከተባሉ አመራሮች መካከልም ይገኙበታል።

ሆኖም እነዚህ አመራሮች አሁን ተጠርጣሪ ተብለው በቁጥጥር ሥር ውለዋል። ስለዚህ ተቃርኖ ምክትል ቢሮ ኃላፊዋ ተጠይቀው ምላሽ ሰጥተዋል።

“በሚዲያ ያቀረባቸው አካል ለተለያየ አላማ ሊያቀርባቸው ይችላል። ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች የፀጥታውን ኃይል የሚመሩ ሰዎች ናቸው። እጅ ከፍንጅ የተያዘ ሰው ስላልነበረም ስለተፈጠረው ነገር ቀርበው [በሚዲያ] ሊያስረዱ ይችላሉ። ቀርበው ያስረዱበት አላማ እኛ ከያዝነው ጉዳይ ጋር ያን ያህል የሚገናኝ አይደለም” በማለት አመራሮቹ እንደማንኛውም ተጠርጣሪ መያዛቸውንም አክለዋል።

“በዚህ መንገድ መገደላቸው ከፍተኛ የፀጥታ ችግር መኖሩን ያሳያል” ጄነራል ፃድቃን

የጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ሳባ እንደገለጹት፤ ማንኛውም አካል ተጠርጣሪ እስከሆነ ድረስ በቁጥጥር ሥር ይውላል።

“ነገ ከነገ ወዲያ መግለጫ ከሰጠነው ሰዎች ውስጥም ማንኛችንም ልንገባ [እስር ቤት] የምንችልበት እድል እንዳለ መገመት ያስፈልጋል። ምንም መተማመኛ የለም” ሲሉም ተናግረዋል።

በተያያዘም የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽንና የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አርብ እለት በሰጡት መግለጫ፤ 218 የሚሆኑ ሰዎች ባህር ዳር ውስጥ ከተከሰተው ችግር ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አስታውቋል።