በፊት በር የተባረረው እስራት እና ግድያ
በጀርባ በር ሲመለስ
ዘር ለይቶ ማሰር ይቁም የዜጎች ሰበአዊ መብት በእኩል ይከበር
======================================
ማሰር፣ መግደል እና ዜጎችን ማሰቃየት የተረጋጋ አስተዳደር እና ሰላማዊ ሀገር ለመገንባት የመፍትሄ ጎዳና አይደለም። ብዙ ተመክሮወች አሉን። ሀገራችንን ቤተ ሙከራ ያደረገው የጠባብ ብሄርተኝነት አባዜ ላለፉት 50 አመታት መሪር በሆነ መልኩ አስተምሮናል። እንዳለድል ሆኖ ዘረኞቹ እና የዚህ ሁሉ ቀውስ ፈጣሪወች አጥቂ ሆነው በመቀጠላቸው አገሪቱን ካስቀመጡበት ጠባብቅ እና እንደሕዝብ ካጋጠመን ችግር፣ እንደሀገር ለመቀጠል ከደረሰብን ፈተና የተማሩ ሆነው አናያቸውም። አሁንም ጠላት ያሉትን በይለይልን ግጥሚያ አቸንፈው ለማለፍ ጠበንጃ ሲወለውሉ ይገኛሉ። እጅግ የከፋው ነገራቸው ለኔነው ለሚሉት ሕዝብም ሆነ ለልጅ ልጆቻቸው የሚያስተላልፉት ቂምን፣ በቀልን እና ዘረኝነት መሆኑን አለማወቃቸው ነው:: ለእረቀ ሰላም እና የተሰሩ ክፉ ስራወችን ለመሻር አለመዘጋጀታቸው አለመዘጋጀታቸውም ሌላ ችግር ነው። ጥብቅ ተሀድሶ ብለው የተሽከረከሩብን አመት ሳይሞላ ያው ችግራቸው ሲያገረሽም እያየን ነው።

ቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴ የጣሊያን ሹምባሽ የነበረውን እድሪስ አወቴ መሳሪያውን ወልውሎ “ኤርትራ ለኤርትራውያን” የሚል መፈክር ይዞ የማህበረ አንድነት ሰፊውን ክፍል ተቃውሞ በረሀ ሲገባ የኤርትራ አንድነት ማህበር አባላትም ሆነ የንጉሰ ነገስቱ መንግስት የተከተለው ስትራቴጅ ንቃቻ እና የት ይደርሳል በመሆኑ የተገንጣዩ ክፍል እድገት እና ጥንካሬ ግዜና ሁኔታው ተመቻቸለት የኋላ ኋላ የአገር ገንጣዮች እድገት ከጨመረ በኋላ የተለያዩ የመፍትሄ ሀሳቦች ቢቀርቡም ከውጭ ጠላት እና የአለማቀፍ ትብብር ጋር ስለተቆራኘ ስህተትን ማረም ሳይቻል ቀርቷል ሌላም አማራጭ እንዳይኖር አድርጓል።

ደርግ በህወሓት የተከተለውም ያው ተመሳሳይ ሲሆን ካሮት እና ለበቅ ከመጠቀም ይልቅ እንደሌለች መቁጠር እና ብሎም በኢትዮጵያ አንድነት እምነት በነበረው በኢሕአፓ ላይ አተኩሮ መዝመት ውጤቱ የት እንደደረሰም አይተናል። ሁሉም ሀገራዊ ችግር መፍትሄው ፖለቲካዊ ብቻ እና ብቻ ነበር አሁንም ነው።፡ማንም ማነን በኅይል ደፍቆ የዘላቂ ሰላም እና የተረጋጋ መንግስት ሊኖረው ከቶ አይችልም። የአንድ ቡድን በሌላው አሸናፊ መሆን ፍጹም እና ዘላለማዊ አይደለም። ደግሞም ከተሞክሮ ያገኘነው (ቤተ ሙከራ በተደረገችው ሀገራችን) ያየነው ሁሉ ያስተማረን ግፍ እና መከራ የበዛበት ዜጋ ሲያመር እና ወደማይመለስ ፍትጊያ ሲገባ እንጅ ሸብረክ ሲል እና ዘላለማዊ መንበርከክ ሲያሳይ አይደለም። ጥያቄው ምንም ይሁን መልሱ ፖለቲካዊ መፍትሄ ነው።፡ባጭሩ ዜጎችን በማሰር፣ ጨለማ ቤት በማጎር፣ እና ጥርጣሬን እና ጥላቻን በማሳየት የሚገኘው ትርፍ ያው ተመሳሳይ እና ለአለፉት ብዙ አመታት ያየነው ድግግሞሽ ብቻ ነው።

ዛሬ ጎራ ለይተው የቆሙ ድርጅቶች የእርዮተ አለም ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ልዩነት ያላቸው አይደሉም። በህወሓት/ኢሕአዴግ ተፈብርኮ የተሰጠ የዘር ልዩነት ላይ መሰረት ያደረጉ ድርጅቶች ናቸው።፡እናም አንዱ በአንዱ ላይ ሲነሳ እና አንዱ ሌላውን መጉዳት ሲጀምር እኛ እና እነሱ በሚል የሚፈራረጅ ቀይ መስመር ያለፈ ኢ-ሞራላዊ እና ኢ-ፍትሀዊ የሆነ ፍልሚያ እናያለን።፡ከዚህ ፍልሚያ የሚታዩት በአለማቀፍ ጸያፍ እና ዘርን ተመርኩዞ የሚሰሩ ወንጀሎች ተደጋግመው በሀገራችን ሲተገበሩ ያሳለፍናቸው 28 አመታት ያሳዩን አስተምሮወች አሉ እነዚያ ቆሻሻ የሆኑ ድርጊቶች የሀገራችን ሕዝብ ስልጡን እና ንቁ ባይሆን ለአለም መፈራረጃ መማሪያ የክፉ ተግባር ምሳሌ ልንሆን የምንችለው ገና ድሮ ነበር። ይህ ደግሞ በስልጣን ላይ ባሉት የዘር ድርጅቶች ሀላፊነት በማይሰማው ተግባር ላይ አላማ ብሎ የሙጥኝ ማለት ከመሆኑ ውጭ ሌላ ልዩ የውጭ ኃይል የጫነብን አይደለም።፡

መፍትሄውም ባስቸኳይ የተረቀቁ እና ምልአተ ሕዝብ ያላመነባቸውን ዘር ተኮር ህግጋት በማፍረስ እና ዘር ተኮር ጥቃቶች ለምሳሌ ዜጎችን ከማሰር፣ እስከመግደል የመሳሰሉትን በአስቸኳይ በማቆም ነው። ጉዳዩ ለመቸ እንደሚተው ባናውቅም እነዚህ ዘርን የተመረኮዙ ህግጋት መወገድ የነበረባቸው ይፋዊ በሆነ፣ ግልጽ እና ተጠያቂነት ያለው አንድ ተቋም በመፍጠር ነው። ግዜውም አሁን ነው። የሽግግር ግዜ ሲባል አሸጋጋሪም አራሚም፣ ህግ አስከባሪም ያው ለ28 አመታት የሀገሪቱን የኖረ እና ልምዳዊ ስርአት ንዶ በዘር ያደራጀው መንግስት ነው። ለዚህም ይመስለኛል የህገመንግስት ጥያቄ በተነሳ ቁጥር ሥስ ብልታቸው ሆና ሲንቀጠቀጡ የሚስተዋሉት። አንዳንዴም ህገመንግስቱን ያልደገፈ መቀመጥም እዚህ አገር መኖርም የለበትም እስኪሉ የዘለቅ አጉራ ዘለል ንግግሮች የሚደመጡት። የሽግግር መንግስት ሲባሉ እንደጥቃት ይቆጥሩት እና እንዴት ተሞክሮ ወደሚል ፉከራ ይዘልቃሉ። ጉዳዩ ግን ማንም ይምራ ከሁሉም (Stakeholders) የተውጣጣ አካል ይኑር እና ችግሩን ባስቸኳይ አይቶ የመፍትሄ ሀሳብ ያቅርብ ማለት ነው። ኢትዮጵያ አትፈርስም። ሊያፈርሧት ተደራጅተው የዘመቱት ዘረኛ ገዥወቿ ናቸው። ከሚሰሩት እራስን ለመጥቀም ከሚደረግ እሽቅድድም ይታቀቡ ማለትም እላፊ ንግግር አይደለም የልቁም የሚታይ ጉድፋቸው እንጅ

ሀገራችን የብዙ ሊቃውንት እና በአለማቀፍ ደረጃ ስም የሰሩ ምሁራን ሀገር ናት።፡ የሁለቱ ታላላቅ እምነቶች ተፋቅረው የኖሩባት እና አሁንም የቀጠሉባት ሀገር ናት።፡ መፍትሄም ለመሻት የይስሙላ ስብሰባወችን በመጥራት ሳይሆን አስቸኳይ መፍትሄወችን ከነዚህ ዜጎች ጋር በመሆን በማፈላለግ የሚገኝ ነው። የፖለቲካው ኃይሎች የመልሶ ማጥቃት እና ስረጃ ተግባር ከገደል አፋፍ አደረስን እንጅ ከነበርንበት ፎቀቅ አላረገንም። ከሁሉም በላይ ተረኛ ባለጉልበት ካለፈው ባለጉልበት መማር ቀርቶ የተለያዩ ምክንያቶች በመደርደር እና ኃላፊነቱን ወደ ኃይልም፣ ሀብትም፣ መሳሪያም ወደሌለው ክፍል በመግፋት ለግዜው የማሳጣት ስራ ሊሰራ ይቻል ይሆናል። ውጤቱ ግን በጎነት አይኖረውም።

ዜጎችን በማሰር የሚመጣ መፍትሄ በየትኛውም ተመክሯችን ቀና ጎዳና የለውም። እናም አሁኑኑ ሊገታ እና ፖለቲካዊ መፍትሄ ሊዘየድ ግድ ነው።
አንባገነንነትን ሊያሽሞነሙኑ የከጀሉ ምሁራንም በተመክሯችን ውጤታቸው የከፋ እንደነበር ከመኢሶኑ የኀይሌ ፊዳ፣ ከበደ መንገሻ፣ ንግስት አዳነ ወዘተ ድርጅት ተምረናል።፡ ቀይ ሽብርን ባሳወጁ እና የሚሊዮኖች ነፍስን በቀሰፉ አመት ሳይሞላ ያ ደም የለመደው ሰይፍ ወደ እነርሱ እንደዞረ እና ብዙ ብርቅ ምሁራንን ያጣንበት ታሪክም ሌላው ተመክሯችን አንድ ክፍል ነበር። የዛሬ ምሁራን ዘር እና ጎጥ ለይተው ለስልጣን ከሚያጎበድዱ በሀገር ላይ ያጠላውን አደጋ መፍትሄ ቢሹለት ታሪክም ግዜም የማይረሳው ስራቸው ይሆናል። የከሰረን የማጎብደድ ታሪክ አክ ብሎ የተፋን ዳግም ጎዳና መከተል ለማንም አይበጅም።

ዘረኝነትን አቅፎ እና ደግፎ (በመንግስት ደረጃ) ከየት የሌለ የሌላ ገመና አየሁ ብሎ ጮቤ መርገጥ በእውነት የዛሬ ባያሳፍር ነገ ውጤቱ ወራዳነት ነው።
ህገመንግስታችን ይከበር የሚሉትን ወደጎን ትቶ ፍየል ወዲ ቅዝምዝም ወዲያ እንድንል ሌላ ላይ ዱላን ማሳረፍ መፍትሄ አይደለም እናም ስንቃወምም ሆነ ስንደግፍ በራስ መተማመን፣ ሀቅ እና ምሁራዊ እውነትን መከተል ተገቢም ለሀገር እና ወገን ከጥፋት የሚያወጣም ብቸኛ ጎዳና መሆኑን ልንገነዘብ ይገባል።፡ኃይሌ ፊዳና ጓደኞቻቸው ተቀምጠው የሰቀሏቸውን የጦር መኮንኖችን በሌሊት ተጉዘው ሊያመልጧቸው አልቻሉም። ኢትዮጵያ ባለ እድል ሀገር ናት በግማሽ ክፍለዘመን በተደረገ ያላቋረጠ የዴሞክራሲ ትግል ከሦስት ያላነሱ የለውጥ ገጠመኞች አግኝተናል። ግን እድለ ጠማሞች ሆነን አሁንም ከዘረኛ ገዥወች እና ዘረኛ ቡድኖች ማምለጥ እና የግማሽ ምእተ አመት የተመኘነውን የነጻነት ጎዳና ማግኘት አልቻልንም:: ይህን የነጻነት ጥማት እውን ለማረግ፣ ሀገራችንንም ከገባችበት ቅርቃር ለማውጣት የምሁራን ስራ እና ተግባር መስዋ’እት እየሆኑ እንደነ ማንዴላ፣ ማርቲን ሉተር ኪንግ፣ ማህተመ ጋንዲ ከሕዝብ የለውጥ ፍላጎት ጎን መቆም እና በክብር ማለፍ የሚጠበቀው እንጅ ለባለግዜ እየሰሩ አሳፋሪ ህልፈት መቀበል አይደለም። ወይንም እንደነ አለሙ አበበ ከአንዱ ወደሌላው አሸናፊ እየተሽከረከሩ የአንባ ገነኖች ቆሻሻ ተሸካሚ የታሪክ ስላቅ መሆንም እጅግ ያስከፋል።

ዘር ተኮሩ እስራት እና ማሳደድ ሊቆም ይገባል። መፍትሄው ማሰር እና ማሳደድ አይደለም። የችግሩ ፈጣሪ የሆነውን ዘረኛ ስርአት እና ህገመንግስት አሽቀንጥሮ መጣል ነው። ዜጎችን ማሳደዱ፣ ይቁም!

ፈጣሪ ቅድስት ሀገራችንን ይጠብቅ!