
ኢትዮጵያና ኤርትራ ደም አፋሳሽ የድንበር ጦርነት ካደረጉ በኋላ ጉዳያቸውን ለግልግል ዳኝነት አቅርበው ውሳኔ ከተሰጠም በኋላ ፍጥጫቸው ለሁለት አስርት ዓመታት ዘልቆ ያለምንም ግንኙነት ቆይተው ነበር።
ኢትዮጵያን ለሦስት አስርት ዓመታት ሲያስተዳደር የቆየው ኢሕአዴግ ለዓመታት በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች ሲካሄድ የቆየውን ተቃውሞ ተከትሎ ባካሄደው የመሪ ለውጥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ወደ ስልጣን ሲመጡ ከወሰዷቸው ቀዳሚ እርምጃዎች መካከል ከኤርትራ ጋር ያለውን ግንኙነት ማሻሻል ዋነኛው ነው።
በዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ከዛሬ ነገ ጦርነት ይቀሰቀሳል ተብሎ ሲሰጋበት የነበረውን ፍጥጫ በማርገብ በዓለም ዙሪያ አድናቆትን ያስገኘላቸውን ጉዞ ወደ አሥመራ ልክ የዛሬ ዓመት አደረጉ።
• ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በአዲስ አበባና ሃዋሳ ጉብኝት ያደርጋሉ
• ሻምፓኝ እና ፅጌረዳ ያጀበው የአዲስ አበባ-አሥመራ በረራ
• ወደ አሥመራ ለመጓዝ ማወቅ የሚገባዎ 6 ነጥቦች
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍተኛ የመንግሥታቸውን ባለስልጣናት አስከትለው ባዳረጉት በዚህ ጉዞ ከሃያ ዓመታት በኋላ ኤርትራን ለመጎብኘት በመጓዝ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ መሪ ሆኑ።
ይህ ጉዞ የተደረገው የዛሬ ዓመት ልክ በዛሬዋ ዕለት ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በጉዟቸው ተበላሽቶ የቀየውን የሁለቱን ሃገራት ግንኙነት የሚያሻሽሉ ስምምነቶችን ከኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር መፈራረማቸው ይታወሳል።
በኢትዮጵያ በኩል በተነሱ ጥያቄዎች ምክንያት ተግባራዊ ሳይሆን እንደቆየ ይነገር የነበረውን የአልጀርሱን የድንበር ኮሚሽን ውሳኔ ኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ መወሰኗን ተከትሎ የተደረገው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የአሥመራ ጉዞ የሁለቱን ሃገራት ግንኙነትን ለማሻሻል ትልቅ እርምጃ እንደሆነ ይታመናል።
ተከትሎም ከጦርነቱ መቀስቀስ ጀምሮ ተዘግቶ የቆየው የሁለቱ ሃገራት ድንበር ተከፍቶ ከሁለቱም ወገን እንቅስቃሴ ሲጀመር ለዓመታት ተለያይተው የቆዩ ቤተሰቦች እንዲገናኙ እንዲሁም የድንብር ላይ የንግድ እንቅስቃሴ እንዲጀመር ምክንያት ሆኗል።
በብዙ መልኩ ከአካባቢያዊና አህጉራዊ ተቋማት ተገልላና እራሷን አግልላ የቆየችው ኤርትራ፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይን ጉብኝት ተከትሎ ከሌሎች የአካባቢው ሃገራትና ተቋማት ጋር ያላትን ግንኙነት ለማሻሻል ጥረት ማድረግ ጀምራለች። ኢትዮጵያም ባደረገችው ድጋፍ በኤርትራ ላይ ተጥለው የቆዩ ማዕቀቦች የተነሱ ሲሆን ከሌሎች ሃገራት ጋር ያላትም ግንኙነትን ለማሻሻል በር ከፍቷል።
የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር በኤርትራ ያደረጉትን ጉብኝትና በሁለቱ መሪዎች መካከል የተፈረሙ ስምምነቶች ዝርዝር ይዘት ሳይታወቅ በተከፈቱት የድንበር መተላለፊያዎች በኩል የሚደረገው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ በጣም ከፍተኛ እንደነበረ ተነግሯል።
• ካለፈቃድ በዛላምበሳ ድንበር በኩል ማለፍ ተከለከለ
ለዓመታት ተለያይተው የቆዩ ቤተሰቦች ለመገናኘት ጊዜ ሳያጠፉ ነበር ድንበር ማቋረጥ የጀመሩት። በተጨማሪም ነጋዴዎች በሁለቱም ወገን የሚፈለጉ የተለያዩ ምርቶችና የሸቀጦችን በማዘዋወር በድንበር አካባቢ ያለው የንግድ ልውውጥ እንዲጧጧፍ ምክንያት ሆነ።
ከዚህ ባሻገርም ለኤርትራዊያን ወጣቶች ሽሽት ምክንያት የሆነውን የብሔራዊ አገልግሎት ለማምለጥ ይጠባበቁ የነበሩ በርካታ ወጣቶችም ነጻ በተለቀቁት የድንበር መተላለፊያዎች በኩል ወደ ኢትዮጵያ መሻገራቸው ይነገራል።
ይህ ነጻ የድንበር ላይ ዝውውር ግን ለወራት ነበር የቆየው። አንድ በአንድ ኢትዮጵያንና ኤርትራን የሚያገናኙት የድንበር መተላለፊያዎች የተዘጉ ሲሆን ለዚህም ከሁለቱ መንግሥታት ይፋዊ ምክንያት ባይሰጥም፤ ሃገራቱ የቪዛና የቀረጥ ጉዳዮችን መልክ ለማስያዝ የወሰዱት እርምጃ እንደሆነ ይነገራል።
አንድ ዓመት ስለሞላው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ የአሥመራ ጉዞና የሁለቱ ሃገራትን ግንኙነት ለማሻሻል ስለተወሰዱ እርምጃዎች ቢቢሲ ኒውስ ዴይ የኢትዮጵያና የኤርትራ ጉዳይን በቅርበት የሚከታተሉትን የዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑትን ዶክተር ዮሐንስ ወልደማሪያምን አናግሯቸዋል።
የሁለቱ ሃገራት የድንበር መተላለፊያዎች መዘጋታቸውን የሚያረጋግጡት ዶ/ር ዮሐንስ፤ አሁንም ድረስ ነገሮች አልጠሩም ይላሉ። ስምምነቱን ተከትሎ ድንበሮች በተከፈቱበት ወቅት “ሰዎች እንዳሻቸው መንቀሳስ መጀመራቸው ኢሳያስን ሳያስጨንቃቸው አልቀረም የድንበር በሮቹ የተዘጉት ከኤርትራ በኩል ነው” የሚል እምነት እንዳለቸው ዶ/ር ዮሐንስ ይናገራሉ።
በሁለቱ ሃገራት መካከል ሰላም ሲወርድ ኤርትራ ህዝብ ቀዳሚው ነገር የድንበር ማካለል ሥራ ነው የሚሉት ዶ/ር ዮሐንስ፤ አሁንም ድረስ ድንበር የማካለሉ ሥራ አልተሰራም ለዚህም ምክንያቱ “ፕሬዝድንቱ ቅድሚያ የሚሰጡት ጉዳይ አለመሆኑ ነው” ይላሉ።
ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በደረሰችው ስምምነት ከሕዝቡ ይልቅ ፕሬዝደንት ኢሳያስ ተጠቃሚ መሆናቸውን ይናገራሉ። “ተጥሎ የነበረው ማዕቀብ ተነስቷል፣ ዓለም አቀፍ መገለሉ ቀርቷል። ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይም ቢሆን ከኤርትራ ጋር የተደረሰው ስምምነት ዓለም አቀፍ እውቅናን አስገኝቶላቸዋል” ይላሉ።
ዶክተር ዮሐንስ እንደሚሉት ከሆነ “የኤርትራ መንግሥት ለህዝቡ ምን እየተከናወነ እንደሆነ የገለጸው ነገር የለም። ኤርትራዊያ ስለሁለቱ ሃገራት ስምምነት መረጃ የሚያገኙት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃንን እየሰሙ ነው። የኤርትራ መንግሥት ምንም ያለው ነገር የለም” ይላሉ።