July 8, 2019

Source : ዘ-ሐበሻ

ህዝብና የመከላከያ ሰራዊትን ባልተገባ መንገድ ለማጋጨት የሚሰሩ ግለሰቦችና የመገናኛ ብዙሀን ላይ ክስ ሊመሰርት መሆኑን የመከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር የኢንዶክትሪኔሽን ዳይክቶሬት ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄነራል መሃመድ ተሰማ የሀገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክተው በዛሬው ዕለት መግለጫ ሰጥተዋል ።

በመግለጨቻቸውም የህግ የበላይነት የማስከበር ተግባር ከሁሉም በላይ የወቅቱ ቁልፍ የሰራዊቱ ተልዕኮ መሆኑን ተናግረዋል።

በቅርቡ በባህር ዳርና በአዲስ አበባ በመንግስ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ላይ በተፈፀመው ግድያ ተፈጥሮ የነበረው አለመረጋጋት ወደ ቀደመ ሰላሙ እንዲመለስ እንዲሁም ተጠርጣሪዎችን ለመያዝና የህግ የበላይነት እንዲከበር ሰራዊቱ ከፍተኛ ስራ መስራቱን ገልፀዋል።

በቀጣይም ሰራዊቱ የህግ የበላይነትን ለማስከበርና በድርጊቱ የተሳተፉ ተጠርጣሪዎች ለህግ እንዲቀርቡ ለማድረግ ከመቼውም ጊዜ በላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት የሚሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ህብረተሰቡ ሰራዊቱን በጥርጣሬ እንዲመለከት የሚያደርጉ ሀሰተኛ መረጃዎችንና የስም ማጥፋት ዘመቻዎችን በተለያዩ መገናኛ ዘዴዎች እያሰራጩ የሚገኙ አካላትን ወደ ህግ ለማቅረብ ስራዎች መጠናቀቃቸውን አንስተዋል።

እነዚህ አካላት በህዝቡና መከላከያ ሰራዊት መካከል መተማመን እንዳይኖር ብሎም ሀገሪቷ ወደ ቀደመ ሰላሟ እንዳትመለስ እያደረጉ ነው ያሉት ሃላፊው፥ ለዚህም በርካታ መረጃዎች መኖራቸውን ገልፀዋል።

በዚህ መሰረትም የተቋሙንና የሠራዊቱን ስም በማጥፋት የተለዩ ግለሰቦች መኖራቸውን ነው ሜጀር ጄነራል መሃመድ የተናገሩት።

በዙፋን ካሳሁን/ አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 1፣ 2011 (ኤፍ ቢ ሲ)