July 7/2019

No photo description available.

አቶ አማን ፋሪስ ሆይ! “ዕውን ይህ ሁሉ የሆነው በዳያስፖራው ነውን?” በሚል ርዕስ የቀረበውን ፅሁፍ ለfb አንባብያን በማጋራቴ በሰጡት አስተያየት ላይ ስለ ራሴ ማለት ያለብኝ ነገር በመኖሩ ብቻ /ተገድጄ/ ነው ቀጥሎ ያለውን የማሰፍረው። ከዚህ አኳያ ሰለ ራሴ ጥቂት በማለቴና ስለ ፅሁፉ መጠነኛ ርዝመት የአንባቢን ይቅርታ ከወዲሁ እጠይቃለሁ። እንግዲህ እነሆ፦

አቶ አማን በህወሀት መራሹ ኢህአዴግ የግፍ ዘመን የትግሉ መድረክ የሆኑ – መሰረታቸው በውጪው ዓለም የሆነ – ድረ ገፆችን የማየት ዕድሉ ወይ ሁኔታው የገጠሞት/የነበሮት አልመሰለኝም። በኒያ የጨለማ ዘመናት ውስጥ ወያኔ መራሹን ኢህአዴግ ለማንበርከክ ከጠመንጃ ትግል በመለስ በነበረው ትግል እንደ አንድ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ከአስራ አምስት ዓመት በላይ በአደባባይ /በድረ ገፆች/ ሳላሰልስ በብዕር ስታገለው ኖሬያለሁ። አንድም ፀረ ህወሃት/ኢህአዴግ ፅሁፍ /ፅሁፎቹ በርካቶች ናቸው/ በብዕር ስም አውጥቼ አላውቅም። በዘመነ ወያኔ ስፅፍ የኖርኩት አሁን በምታውቁኝ ሶስት መጠሪያዬ ነው። የምፅፈው የማምንበትን በመሆኑ እኔነቴን ከነ ኢሜል አድራሻዬ ደብቄ አላውቅም። አሁንም በለውጡ ዘመን በድረ ገፆች ላይ የምፅፈው ያው እንደ ቀድሞው ስሜን ሳልሸሽግ ነው። የማምንንበትን!! ዝርዝሩ እዚህ አያስፈልግም።

ወደ fb የመጣሁት በ2018 መጨረሻ ነው። ከዛ በፊት ይህን መድረክ ተጠቅሜ አላውቅም። የመጣሁትም በዓላማ ነው፣ ለግል ጉዳዬ ሳይሆን ሀገራዊ ርዕሶችንና ሀሳቦችን ለማንሸራሸሪያ ለመወያያ ለመማማሪያና ለመተራረሚያ ሰፋ ያለ መድረክ እንዲኖረኝ በማለት። በአካውንቴ እስከዛሬ ያቀረብኳቸውን መመዘን ይቻላል፣ ከዓላማዬ የተፃረርኩ ከሆነ። የጥላቻና የዘረኝነት ወይም የአንድ ቡድን ቲፎዞ ወይ ጭፍን ኮናኝ ወይ አድር ባይ አወዳሽ የሆኑ የፅሁፍ ሥራዎች የሚቀርቡበት ወይ ፅንፈኝነት የሚላዘንበት መድረክ አይደለም ይህ የfb አካውንት። (ከሀገሬ የተሰደድኩት ዘረኝነትንና ፀረ ኢትዮጵያዊነትን በመቃወም ነውና!!)

እናም በዚህ መርህ የራሴን ሥራዎች ብቻ ሳይሆን ከተለያዩና ተዓማኒነታቸውን ከማምናቸው ሚዲያዎች – ህዝባዊ ባለቤትነት ያላቸውን – በተለያዩ ሀገራዊ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የሚያጠነጥኑትን ፅሁፎች፣ ለሚያነቡት አንዳች መልዕክት አላቸው የምላቸውን /ከግል ህይወት ሥራ መልስ ጊዜ በመውሰድ በማንበብና በመመዘን/ ለሌሎች ማጋራት ጠቃሚነቱን ማመኔ ብቻ ሳይሆን በየጊዜው በሀሳብ መንሸራሸሪያው መድረክ /በማቀርባቸው ፅሁፎች ላይ/ ተሳታፊው በመበራከቱ እኔም በንቃት ተሳትፎ አደርጋለሁ። እኔ ያልፃፍኳቸውን በእኔ አካውንት ስም ስር የፀሀፊዎቹን ስም ወይም የተገኙበትን ምንጭ አስቀምጣለሁ። (በነገራችን ላይ አንድ በእጅጉ የተገረምኩት የfb አብዛኛው ተጠቃሚ ለድረ ገፆች ዳሰሳ ወይ ጊዜ የለውም ወይም አያውቃቸውም። ሆኖም በfb ላይ የሚቀርቡትን ፅሁፎች የመመዘንና ዕይታውን /በአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ጨዋነትን በተላበሰ አቀራረብ/ የማስተላለፍ ብቃቱን አደንቃለሁ።)

ባለቤት ባልሆንኩባቸው ነገርግን እንድንጋራቸው ባቀረብኳቸው ፅሁፎች ወይም ከሌሎች የእንግሊዝኛ ፀሀፊዎች ወደ አማርኛ በመለስኳቸው የትርጉም ሥራዎቼ ላይ አንባቢ የሚሰጠው ፍረጃ፣ አስተያየት፣ ትችት በቀጥታ በእኔ ላይ መሰንዘር የለበትም። ምክንያቱም ያደረግሁት በሌላ ወገን ያለውን እይታ/ግንዛቤ/ሀቅ ማቅረብ እንጂ። ከዚህ አንፃር በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የሰነበተ /የካበተ/ ልምድ ያላቸው ፀሀፊ አቶ ግርማ ካሳ ጠ/ሚር አብይ በፓርላማ ውሏቸው በውጪ ሀገር ነዋሪ ኢትዮጵያውያን /በዲያስፖራው/ ላይ ያወረዱትን ዕርግማንና “የኢትዮጵያ ወቅታዊ ችግሮች ተጠያቂ” አድርገው ያቀረቡበትን አውድ በመቃወም “ዕውን ይህ ሁሉ የሆነው በዳያስፖራው ነውን?” በሚል ርዕስ ሀሳባቸውን ነጥብ በነጥብ አቅርበዋል። ፅሁፉም በተለያዩ የሚዲያ አውታራት ላይ ወጥቷል። እኔም ይህንን ፅሁፍ አጋርቻለሁ። ይህንን የአቶ ግርማን ፅሁፍ ነጥብ በነጥብ አበራይቶ መሞገትም ሆነ መተቸት ወይም መደገፍ የአንባቢው ፋንታ ነው።

አቶ አማን በዚህ ፅሁፍ በእኔ አካውንት ስር በሰጡት አስተያየት ላይ ሶስት ግዙፍ ስህተት ፅፈዋል። አንደኛ የፅሁፉ ባለቤት ስም በግልፅ ተቀምጦ እያለ ፅሁፉን እኔ የፃፍኩ አድርገው አቅርበዋለ። ሁለተኛ እጅግ የሚገርም ፍረጃ ፈርጀውኛል “ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥላቻና ንቀት አለህ” በማለት። ሶስተኛ በውጪ የምንገኝ ኢትዮጵያውያን ሀገር ውስጥ በሠላም የመኖር ችግር የፈጠርንባቸው በመሆኑ “ባህር ማዶ ላይ ሆኖ እኛን ስጋት ላይ መጣል ምን የሚሉት የትግል ስልት ነው? ተዉን እንጂ ጎበዝ” የሚል እሮሮ አቅርበዋል።

ከአዲስ አበባ በተመታው ነጋሪት መሰረት ውጪ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ የህዝብ ስጋት መሆኑን ነው አቶ አማን አምርረው ያስተጋቡት። አንባቢ በዚህ ፅሁፍ ሂደት እንደሚረዳው አቶ አማን (የከረሩ ቃላትን ላለመጠቀም ስለምፈልግ) በጅምላ “በሀገር ስጋትነት” ከፈረጁን ኢትዮጵያውያን በተጨማሪ በግል ያቀረቡብኝ የፍረጃ ድምዳሜ ከዕውነታው የሚጋጭና አግባብነት የሌለው መሆኑን ነው። (ስለ ዲያስፖራው ውንጀላ አቶ ግርማ ያቀረቡት መከላከያ በቂ በመሆኑ ወደ ተጨማሪ ሀተታ አልገባም።) እራሴን በሚመለከት ግን ጥቂት ዕውነታ እንዳክል ይፈቀድልኝ፥

1. ቅድመ መጋቢት 2010 ዓ/ም
* ኦቦ ለማ መገርሳ “ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው” ሲሉ፣
* ኦቦ አዲሱ አረጋ ቂጤሳ “ጣና ኬኛ” በሚለው ሀገራዊ አዝማች መርህ ይህን አስመልክቶ በፃፉት መልዕክት፣
* ኦቦ ታዬ ደንደአ በኮማንድ ፖስት ሲታሰሩ … (እና በዛን ዘመን በተፈጠሩ ሌሎች ተዛማጅ ኩነቶች) ዓላማቸውን በመደገፍ ወያኔ መራሹን ኢህአዴግ በመቃወም በውጪ ሚዲያዎች ላይ በመፃፍ ከጎናቸው ከቆሙት ኢትዮጵያውያን አንዱ ነኝ። ግለሰቦቹ የወጡበት ድርጅትም ሆነ ብሄራቸው ወይም ኢህአዴጋውያን መሆናቸው በወቅቱ ለኔም ሆነ እኔን ለመሰሉ ኢትዮጵያውያን ትርጉም አልነበረውም፣ ኢትዮጵያዊነት አጀንዳቸው እንጂ!! “ኢትዮጵያን” ያሉበት የአደባባይ ቃላቸው እንጂ!!

2. ድህረ መጋቢት 2010 ዓ/ም

* መጋቢት 24/2010 በአብይ በዓለ ሲመት የእፎይታና የደስታ እንባ ካወረዱት አንዱ ነኝ።

* መጋቢት 30/2010 ዓ/ም በዕለተ ትንሣዔ /የፋሲካ ዕለት/ አብይ ኢትዮጵያን ከፍ ባደረገ በሰባተኛው ቀን /ከቤተ ክርስቲያን አዳር መልስ/ ትንሣዔንና አብይን እንደ ምልክት በመውሰድ “አብይን ፍለጋ” በሚል ርዕስ በርካታ ገፆች ያሉት ትንታኔ አዘል ፅሁፍ ሳዘገጅ ውዬ ማታውኑ በአያሌ ድረገፆች ተለቆ አያሌ ኢትዮጵያውያን አንብበውታል። እስከ ዛሬም ስለዚህ ፅሁፍ የሚያነሱልኝ ሰዎች አሉ። /በዓመታት የፅሁፍ ታሪኬ ያለ አንዳች ውስጣዊ ሀዘንና ቁጭት በፍፁም ሀሴትና የሠላም ድባብ የፃፍኩትም ነው/ ያኔ አብይን የሚጠራጠሩት ብዙዎች ነበሩ። ብዙ ያሉትም ነበሩ። (ዛሬ የት እንዳሉ እነሱም እኛም እናውቃለን) ብዙዎችም በዚህ ፅሁፍ ምክንያት “እንዴት ጭልጥ ብለህ አብይ የተናገረውን ታምናለህ?” ብለው ሲጠይቁኝ መልሴ “አስቀድሞ ቃል ነበረ” የሚል ነበር።

አዎ! አብይን በቃሉ አምኜው ተከትዬዋለሁ፣ ተሟገቼለታለሁ። ጊዜ ሰጥተን ቃሉን ከግብር እንመዝን ብያለሁ!! ይህ ፅሁፍ (አብይን ፍለጋ) አብያዊ አማንያንን ለማበራከት የራሱን መጠነኛ አሰተዋፅዖ አድርጓል ብዬም አምናለሁ።
* ሠኔ 16/2010 በአብይ ላይ የግድያ ሙከራ ቢካሄድ “አሸባሪው ህወሃት” በሚለው ፅሁፌ በአብይ ላይ የተቃጣውን የአሸባሪነት ሙከራ ኮንኜና ህወሃትን አውግዤ ከለውጡ መሪ ጎን ቆሜያለሁ።

* አብይ ከአሜሪካ መልስ ድንገት ቢጠፋብን በጭንቀት ሊፈነዱ ከደረሱት ኢትዮጵያውያን አንዱ ነኝ። (በወቅቱ በቀረቡ የሴራ ንድፎች ምክንያት ግን አልነበረም) ሁኔታው እጅግ ቢያሳስበኝ “የምናውቀውን አብይ ማየት እንፈልጋለን” በሚል ርዕስ ያዘጋጀሁት ፅሁፍ በድረ ገፆች ላይ ተለቋል። በተመሳሳይ ጊዜ አቶ ኦባንግ ሜቶ ተመሳሳይ ይዘት ያለው ፅሁፍ በድርጅቱ በኩል በድረ ገፆች ላይ መልቀቁ ትዝ ይለኛል። ሌሎችም አሉ፣ ለአብነት እኒህ ይበቃሉ።
*********
ወደ fb ስንመጣ በመጀመሪያ “ፖስት” ያደረግሁት ፅሁፍ “እስኪነጋ” የሚል ነው። (ይህ ፅሁፍ አስቀድሞ በድረ ገፆች ላይ ለንባብ በቅቷል) እስኪነጋ ከአብያዊው መንግሥት ጋር እንድንጓዝ። አቶ አማን ጊዜ ካሎት ወደ ሗላ ሄደው (ከአካውንቴ) ይፈልጉ። የfb መለያዬ “ሊነጋ ሲል” የሚለውም ምስል ያለምክንያት ያደረግሁት አይደለም። በfb እስከምቆይበት ጊዜ ወይም በኢትዮጵያ “እስኪነጋ” ይኸው ምስል መለያዬ ይሆናል። በኢትዮጵያ ንጋቱ መቼ ይሆናል? የሚለኝ ቢኖር መንጋቱን ማብሰሪያ ብዬ የማምንባቸውን ነቁጦች በዛው ፅሁፍ አንጥቤያለሁ።
**********
ይሁንና ከጊዜ ወደ ጊዜ በለውጡ አራማጆች የሚነገሩና የሚተገበሩ ዕምነቴን እየሸረሸሩት፣ ተስፋዬን እያደበዙት መምጣታቸውን ልክድ አልፈልግም። ዕውነቱን ተናግሮ የመሸበት ማደር እንዲሉ (ምናልባት እንደ ተሰደዱ መኖር ፥ በሚል ካልተቀየረ ?)

(የዕምነቴ መሸርሸርም “ቃል የዕምነት ዕዳ” በሚል ቃላቸውን አምነን የተከተልናቸው ደጋግመው ቃላቸውን አጥፈዋልና ነው! ከቃላቸውም በተቃራኒ ቆመው ከመነሻቸው ያፈነገጡ ምግባር ፈፅመዋልና! ለዚህ የትየሌ ማስረጃዎችን ማቅረብ ይቻላል። የተነሳሁበት ጉዳይ ግን አይደለም።)

ከለውጡ አራማጆች እንዲሻሻሉ፣ እንዲታረሙ፣ እንዲገቱ /አላስፈላጊ ከሆኑ ውሳኔዎች ድርጊቶች ወዘተ/የሚጠየቁ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ የለውጥ አደናቃፊ ወዘተ የሚሉ ታርጋ የሚያሰጡ መሆናቸው ደግሞ እጅግ አሳዛኙ ክስተት ሆኗል። በተለይ ደግሞ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በውጪ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና በሀገርቤቱ ህዝብ መካከል የበርሊን ግንብ እየታነፀ ይመስላል።

በቅድመ መጋቢት 2010 ዓ/ም የትግል ዘመን የኦሮሞ ድርጅቶችና የህግ ባለሙያዎች ለንደን ላይ ተሰብስበው “የታመመች ኢትዮጵያን ማዳን ሳይሆን መጨረስ ነው ዓላማችን” ያሉት ፅንፈኞች ዛሬ አዲስ አበባ ተቀምጠው በምቹ ሶፋ በተሽከርካሪ ወንበር በሾፌር በሚነዳ መኪናና በአጃቢ ወታደሮች እየተንደላቀቁ “መንግሥትነታቸውንም” በአደባባይ ሲናገሩ፤ የኢትዮጵያ ተቆርቋሪ ሆኖ እነሱን በውጪው ዓለም ሲፋለም የኖረውን ዲያስፖራ “ሀገር ሊያጠፋ ነው” እያሉ “ከመጋረጃው ጀርባ ሆነው” ሲያስተባብሩና ሲያዘምቱ እንደማየት የሚያም የለም።

“መጀመሪያ በኢትዮጵያዊነታችን መደራደር አለብን” ሲሉ የኖሩ እኒሁ የውጪ ሀገር ፖለቲከኞች ዛሬ የት ናቸው? እዛው አዲስ አበባ ገብተው የለምን? ስለ ኢትዮጵያ የማቀቁትንና በኢህአዴግ ፍዳ የተቀበሉትን ሞራልና ሰብዕና ለመግደል ቄሮን አስፈቺ ሀይል በማድረግ “ፌስታላቸውን አንጠልጥለው እንዲፈቱ አደረግናቸው” ሲሉ የማይሰቀጥጣቸው (ቀድሞ የደገፍናቸው) “የለውጡ አስኳል” የሚባሉት መሪዎች ናቸው።

“ኦሮሞ አማራ ወዘተ እንጂ ኢትዮጵያዊ የሚባል የለም” በማለት የአንድን ሀገር ድፍን ህዝብ ህልወና በአደባባይ በውጪው ዓለም ሳሉ የካዱ ዛሬ አዲስ አበባ ላይ ፈላጭ ቆራጭ ሆነው እነሱን ከአውስትራሊያ እስከ አሜሪካ ሲፋለም የኖረውን ዲያስፖራ ሀገር ቤት በተከፈተላቸው ሚዲያ ሲረባረቡበትና የኢትዮጵያ ህዝብ ጠላት አድርገው ሲያቀርቡት እንደማየት ምን አንጀት የሚያቆስል አለ?! “ቃል የዕምነት ዕዳ” አለመሆኑን ቃላቸውን አምነን በጥፍራችን የቆምንላቸው “ዲሞግራፊ” ወሳኝ ነው ሲሉን “ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው”ን ጎርፍ የወሰዳት ያኔ ነው። ብዙ ማስረጃ ማቅረብ ይቻላል፥ “ቃልና ግብር ለየቅል” ሆኖ ለመገኘቱ። ግን መነሻዬ አይደለምና በዚሁ ይገታ።

አቶ አማን ሆይ! ለመሆኑ የአብይን በቀን የአንድ ዶላር ጥሪ የትኛው የህብረተሰብ ክፍል የተቀበለው ይመስሎታል?በውጪው ዓለም በመቶ ሺዎች ወይም ሚሊዮን የሚቆጠረውና ራሱን በብሄር ያደራጀው የኦሮሞ ማህበረሰብ እንደ ማህበረሰብ ለአብይ ጥሪ አምስት ሳንቲም የሰጠ ይመስሎታል? አይምሰሎት። አፍቃሪ ህወሀት ራሳቸውን በብሄር ያደራጁ የትግራይ ማህበረሰብ እንደ ማህበረሰብ ለአብይ ጥሪ አምስት ሳንቲም የሰጡ ይመስሎታል? አይምሰሎት። ከእኒህ መኻል ግን ስንትና ስንቶች ናቸው ዛሬ አዲስ አበባ በመከረኛው ታክስ ከፋይ የኢትዮጵያ ህዝብ ገንዘብ በሆቴሎች የሚንፈላሱት፣ በአጃቢዎች የሚንጎማሉት? ብዙ ለማለት ቦታው አይደለም እንጂ…

አቶ አማን ሆይ ኢትዮጵያን የሚሉ ኢትዮጵያውያን ለሀገራቸውና ለህዝባቸው ስጋት ሆነው አያውቁም! ወደፊትም አይሆኑም። (በነገራችን ላይ ከላይ እጀ መንገዴን ባነሳሁት በአንድ ዶላሯ ጉዳይ አንተሰ ምን አርገኻል ቢሉ፥ የተጠየቅሁትን ዓመታዊ ድርሻ ከፍያለሁ፣ ጥያቄው ስለ ኢትዮጵያ በመሆኑ!!!)

እና አቶ አማን ሆይ እኔ በኢትዮጵያ ላይ ስዘምት አልኖርኩም። በኢትዮጵያ ላይ በዘመቱባት ህወሃት ኢህአዴግና ኢትዮጵያን መበተን ዓላማችው ባደረጉ ፅንፈኞች ጋር ግን በምችለው ሁሉ በውጪው ዓለም ስተናነቅ ኖሬያለሁ። ይህ አቋሜ ዛሬ ከመቼውም በላይ ፅኑዕ ነው፣ ከመቼውም በላይ ስጋት ስላለ። የኢትዮጵያ ስጋት ዲያስፖራው አይደለም፣ ስጋቱ ያለው እዛው እንጂ! የሆነ ሆኖ እኔ በማንም ላይ ጥላቻና ንቀትን የማሳይ ሰው አይደለሁም፣ ሁሉንም እንደ ምግባሩ እምመዝን እንጂ!
*************
አዎ! ስለ አብይ በአደባባይ ጥብቅና ቆሜያለሁ። አዎ! ስለ አብያዊው መንግሥት ደጋግሜ ደግፌ ፅፌያለሁ። ዛሬ ግን ጥብቅና ሳይሆን ቆም ብዬ ብዙ ጥያቄ እጠይቃለሁ። ይህ ግን አብይን መጥላት አይደለም። ሠማይን እረስልን፣ ጨረቃን ዳቦ አድርግልን የሚል ጥያቄ አይደለም። አብይ በሰዋዊና በመንበረ ሀይሉ ማድረግ ሲችል ስላላደረጋቸው እና ከቃሉ በተቃራኒ እንዲሆኑ ስለፈቀደላቸው ሀገራዊ ጉዳዮች እንጂ! አብይን ቆም ብለህ ዙሪያ ገባህን ተመልከት፣ ችግር አለ፣ ስታስተምረን አድምጡ ብቻ ሳይሆን እኛም ሳንፈረጅ የምንልህን ስማ – የሚሉ ሁሉ ለውጥ አደናቃፊ የሚባሉት ለመንድን ነው? አብያዊው መንግሥት ማስተካከልና ራሱም መስተካከል ያለበት ጉዳይ አለ ሲባል፤ በለውጡ አራማጆች በኩል በእሽቅድምድም ከዘር ጋር የሚያያዘው ለምንድን ነው? በመጨረሻም አቶ አማን ሆይ በውጪ ያለውን ኢትዮጵያዊ እንደ ጭራቅ በመሳል ከሀገሩና ከህዝቡ ለመነጠል፣ለማግለል፣ ለማስጠላት የሚደረገው ደባ በኢትዮጵያ አምላክ ፊት ዋጋ ያስከፍላል! ይኸው ነው ነጥቤ!
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!