አጀንዳችን————-

=====================
ህወሓት/ኢሕአዴግ አሁንም ገዥ ቡድን ነው። የኢትዮጵያን ሕዝብ አሁንም ትናንትም ለ28 አመታትም የገዛ በጠብመንጃ አፈሙዝ ነው። የተንበረከከውን እና ይጠቅማል ያለውን ጨው እና ስኳር፣ እምቢ ለሀገሬ ለወገኔ፤ ለዘረኝነት አልገዛም ያሉ ምሁራንን እንደብረት ቀጥቅጦ እና አቅልጦ አጠፋቸው ወይንም በጥይት ደብድቦ ገደላቸው ቀሪወቹን እንደነ እስክንድ ነጋ፣ ዶክተር ታየ ወልደሰማያት ያሉ አይበገሬ ታዋቂወችን በሀሰት ምስክር እየገዛ በጨለማ ቤት ለአመታት አጎራቸው ወዘተ።

ህወሓት እና የፈጠረቻቸው ፍጡሮች አንድ አይነት ባህል እና የትግል ተመክሮ ነው ያላቸው። ማታ በጨለማ ገድለው ቀን በአደባባይ ከዘመድ አዝማድ ጋር ሙሾ ይወርዳሉ። አይኔን ግንባር ያርገው ብለው ይምሉ ይገዘታሉ የሚበላ፣ የሚታለል ከተገኘ። እንደእስክንድር እና ታየ ወልደሰማያት ወይንም እንደነ ፀጋየ ገ/መድህን (ደብተራው) አይነት ግንባራቸውን የማያጥፉ ሲኖሩ ደግሞ አውሬ ባህርያቸውን አውጥተው በአደባባይ ያሰጡታል። ይሉኝታ፣ ስለሀገር ስለሕዝብ የሚል አስተሳሰብ ኖሯቸውም ፈጥሮባቸውም አያውቅም። እንደሀረግ የሚቅለሰለሱት እና ሰው ሊሰማው የሚፈልገውን የሚናገሩት ፍጡሮች የእነሱን የሚነካ ሲመጣ አውሬነታቸው ገሀድ ይወጣል። ለዚያም ነው ታድሰናል ባሉ ማግስት ያየነው የሰማነው ጉድን የሰው ፍጡርን ከአውሬ ጋር ያሰሩ፣ በወንድልጅ ሥስ ገላ ጠርሙ ያንጠለጠሉ፣ ፈጣሪያችንን እናትን የማይደረግ ጭካኔን የፈጸሙ፣ የሰውልጅን ጥፍር በጉጠት የነቀሉትን፣ ለወራት እና አመታት የሰውን ፍጡር ብርሀን እንዳያይ ያደረጉት ወዘተ..ወዘተ ገመናቸውን አውጥተው የዘከዘኩት። በይበልጥም በቅድስት ሀገር ኩሩ እና ፈጣሪ በሚከበርበት ሕዝብ ግብረ ሶዶማዊነትን የፈጸሙ የሞራል ጠብታው ጨርሶ ከሰውነታቸው ታጥቦ የወጣ በሚመስል ጉግ ማንጉግ መሪወች ሕዝባዊው አመጽ ግሎ እና ፍሞ ጉሩምቧቸው ስትያዝ በስብሰን ነበር በጥብቅ ተሀድሶ ግን ተጠምቀን መጥጥተናል ያሉን።፡ ከእነዚህ የሞራልም ሆነ የሰውነት ባህርያት ከሌላቸው ግብዛን እውነት ይገኛል ብሎ አፍ ከፍቶ የሚያዳምጥ ዛሬም ካለ የጅል ጅልነት ይመስለኛል።

ከመሀላቸው የሞራል እንጥፍጣፊ የነበራቸውን በየግዜው እና ዘመኑ ገድለው እዚህ እንደደረሱም እናውቃለን። እነ ሙሴን እነ አትክልት ቀጸላን የራሳቸው የአመራር አባል የነበረን፣ የደህንነት ሹማቸውን ወዘተ። ባጭሩ የእሥስት ባህርይን የድርጅታቸው ባህል አድርገው ከልጅነት እስከ አዛውንትነት የኖሩት ጠባቦች መቸውንም ከበሰበሱበት ሊጠሩ እንደማይችሉ ግልጽ ነው “በስብሰናል” የሚለው የራሳቸው ቃልን ለመጠቀም እንጅ የብልግና ስድብ ለማድረግ ፈልጌ አይደለም።

የዛሬ አጀንዳቸው

ህወሓት እህት የምትለውን የአንድ ማህበር አባሏን ተሳደበች። አጸፋውም ተመለሰላት በምላሹም ይሁን በኦሪጅናሉ ምልልስ ሕዝብ የማያውቀው አልተባለም። አንድ ነገር ግን ግልጽ ሊሆን ይገባል አጀንዳ የማስቀየሩ አዲስ ታክቲክ። ጠቅላይ ሚኒስቴሩ በውጭ የሚኖረው ዜጋ እስራት arbitrary arrest arbitrary detention ይቁም ብለው የጮሁ ዜጎችን በፓርላማ ወጥተው ሀገር ሊበትኑ ማለታቸው የሚታወስ ነው። የእርሳቸው ቃል የሆኑም በማህበራዊ ሚዲያው ብዙ ሲሉ መሰንበታቸው ይታወሳል። የህወሓት እና በአዴን መግለጫወች በበኩሌ አጀንዳ ቀያሽ እና የዜጎችን እስረኞች ይፈቱ ጩኸት አስለዋጭ አዲስ የመነጋገሪያ አጀንዳ መሆኑ ነው። ከምር ሀገር እያፈረሱ ያሉት ኢሕአዴጎች እንጅ ሀሳብ እና ሰበአዊ መብት ይከበር ባዮች አለመሆናቸው ግልጽ ሆኖ ሳለ ጠብመንጃ ያልያዙ ለምን ዜጎች ይገደላሉ፣ ይታሰራሉ የሚሉት መሆን የለባቸውም። መሪውስ የታሉ የህወሓት ፉከራ አዘል መግልጫ ሲወጣ?አንድ ነገር ግን እርግጠኛ ነው የፈረደባቸው ስርአቱን እና ኢሕአዴግን ይቃወማሉ ብለው የጠረጠሯቸውን በማሳደድ ላይ ናቸው። በአደባባይ እና በአለም ፊት የሽብር ህግ የሚሉትን እነርሱው ግፈኛ ብለው ያወገዙትን ገለን ቀብረነዋል ካሉት አውጥተው እየተጠቀሙበት ነው። የባልደራስ አባላትን ያለምንም ማብራሪያ አይን ያወጣ የትናንት ዘረኞችን ተግባር እየፈጸሙ ነው። የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ከተራ አባላት እስከ መሪወቹ ወደ እስር እየተወረወሩ ነው። አንዳንዶቹ እንደነ መቶአለቃ ማስረሻ ሰጤ እና መሰል ዜጎች እየተሳደዱ መሆናቸውን ማህበራዊ ሚዲያው አድርሶልናል ወዘተ። እናም ይህን በውስጥ እየተፈጸመ ያለን አዲስ የአፈና ዘመቻ ድምጹ እንዳይሰማ ለተገፉት እና ለተጋዙት ልሳን ሆኖ እንዳይነገር የ diversion አንዱ ታክቲክ በሌላ አጀንዳ ሰውን መጥመድ ማለት ነው። እናም ስለሚታሰሩት እንዳንናገር አዲስ መነጋገሪያ ፈጠሩልን ማለት ነው። እንደኔ እምነት ኢሕአዴግ ይታደሳል የሚል እምነት ካጣሁ ዘመናት ተቆጥሯል ኢሃዴግ ማታለሉን እና ማስመሰሉን ግን ይቀጥልበታል። ይህ ስርአት እስካልተወገደ ድረስ ሀገር አደጋ ላይ መሆኗ፣ ዜጎች ሰላም ማጣት እና መፈናቀል ቀጣይ ይሆናል። ባንድ እራስ ሁለት እንድንል በፓራማ ወጥተው ነጻ ሚዲያን ለመክሰስ በቁርጥ የተናገሩት መሪ እና ስልጣን በያዙ ማግስት ዜጎች ከአድማስ አድማስ ከአይን ያውጣህ ብለው የጸለዩላቸው ዛሬ ዲያስፖራውን ሲረግሙ ለመክሰስም ሲነሳሱ ማየት እና መስማት እንዴት ያሳዝናል? የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕን ያህል ነቀፌታ የገጠመው መሪ ብዙ የለም። የቴሌቪዥን ኔትወርኮች ቀን ከሌሊት በእርሳቸው ተግባራት ነቀፌታ ተጠምደው ይውላሉ። ማህበራዊ ሚዲያ ትዊተር እና ሌሎችም እንደዚሁ ያውም ተራ ዘለፋ እና እላፊ ንግግሮች የተሞሉንበት። ግን በሀሳብ ብዙሀነት ተወልዶ ያደገ የሰወች የተለያየ ሀሳብ ክቡር ነው እንጅ የሚያማርር አይደለም ብሎ ያምናል እናም ትራምፕም ሲችሉ በስድብ አጸፋ ይመልሳሉ ካልቻሉ ግን ቂም እን በቀል ይዘው ና ተወገር ተከሰስ አልላሉም። ሌላው አስደማሚ የትናንት ተቃዋሚ እና የዴሞክራሲ ትግሉ ተሳታፊወች አይን ያወጣ ዘረኝነትን፣ የዜጎችን መታሰርን ደግፈው ሲቆሙ፤ በሕዝብ ድጋፍ ለዴሞክራሲ ትግሉ እንዲረዳ የተቋቋሙ ሚዲያወች የእነ እከሌ መታሰር ተገቢ ብለው ሲያስተጋቡ፤ የገዥወችን የፕሮፖጋንዳ ከረጢት እነርሱም ተባብረው ሲሞሉ ማየትም ሌላው አሳፋሪ ተግባር ነው።

ለማንኛውም አጀንዳ ሲሰጡን አጅንዳቸውን ተቀብሎ ማስተጋባት ቢቆም። አህያ ቢራገጥ ይሏል ባደባባይ የተነገረው በጠረጴዛ ድርድር የሚረግብ እንጅ በአንድ ገዥ ፓርቲ ውስጥ ያለ ቅራኔ ፈችም ተከታታይም ተቆርቋሪም አለው። አዴፓወች አፍረው እና ከምር ከሆነ ችግሩ ገብስ ነው። ሕዝብ ከጭቆናው ገመድ መላቀቅ ዛሬ ይፈልጋል ቀላሉም ነገር ዜጋን ለትግል ማሰለፍ እየተካሄደ ላለው ትግልም አጋር እና ጋሻ መሆን ነው። ሲበዛም ታሪክን መቀየር እና እንደአያት ቅዳያቶቻችን አርበኞቹ ሶማ እና ጃዊ ቋራ እና በለሳ ሞልቶ ነው። አዴፓወች አምረው ከሆነም እና ከምር አስበው ካደረጉ ሰብስበው ያስገቧቸውን ንጹሐን እንዲፈቱ አብረው ይጩሁ ወይንም ስልጣናቸውን ተጠቅመው ይልቀቁ። የገዥወችን አጀንዳ ማስቀየር ስልት ግን በቃ ብለን ልሳን ለሌላቸው ዛሬም እንደትናንቱ ልንጮህ ግድ ይለናል።

ሌላው የዘረኞችን አስተሳሰብ መጋራት፣ ዜጎችን በዘራቸው፣ በሚናገሩት ቋንቋ ለይቶ መስደብ የዴሞክራሲያውያን ባህርይ አይደለም። ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሁሉ የተነሱበት አያት ቅድም አያቶቹ ደማቸውን አፍሠው፣ አጥንታቸውን ከስክሰው ለአቆዩን ሀገር ፍቅር እና አልኝታ ነው የሚሉትን ክፍል ነው። በ 1960 ወቹ ተነስተው የተደራጁ የዘር ድርጅቶች (የዘር ነው ያልሁ) ጸረ አማራ ጸረ ኢትዮጵያ ሲሆኑ እና ያለስሙ ስም ሰጥተው ያለእምነቱ እምነት፣ በሌለበት ዋለ ብለው የሰደቡትን መልክ እና አይነት መጠቀም እጅግ የወረደ እና የሞራል ዝቅተኝነት መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። እንደዚያ እንድንሆን አይጠበቅም። ሕዝብ ወገን ነው ሕዝብ ከሕዝብ ጠላት ሆኖ አያውቅም። ዳዋ በበላ እንዳይሆን ይጠበቃል።

እናም አጀንዳችን ስለዴሞክራሲ፣ ስለሰበአዊ መብት፣ ስለሰላም እና ፍትህ መጮህ መታገል ነው። አጀንዳችን ጠላቶቻችን አይቀርጹልንም ስለነሱ አንጮህም ነርሱ ባስቀመጡልን እና ባሳዩን መንገድ አንነጉድም።፡የልቅም አሁንም ህወሓት/ኢሕአዴግ የተባለ ጉግ ማንጉግን ጠበቅ አርጎ መታገል እና የተንገዳገደው እስከ ቅራቅንቦው ህገመንግስት ማስወገድ ግዜውም አሁን እንጅ ነገ አይደለም። እፎይታ ባገኘ ቁጥር ከማሰር እና ከመግደል እንደማይመለስ አሳይቶናል

ፈጣሪ ቅድስት ሀገራችንን ይጠብቅ!