July 14, 2019

አሁን አሁን ሳስተውል ሰዎች የሚሆነውን እንደ ባለ አእምሮ ማስተዋል የተሳነን ይመስላል፡፡ የምንደግፈውም የምንቃወመውም ያለምክነያት እየሆነ ያለው በዝቷል፡፡ ነገሮች ሕግና ሥርዓት እንዲኖራቸው እየሰራ ያለ መሆኑን ምልክት በማይታይበት ይበልጠውንም በተግባር የምናያቸው ጸረ- አገርና ሕዝብ ሆነው እያየን ከዚህ ይልቅ በወሬ እንድንሞላ የፈቀድን ይመስላል፡፡ የሰሞኑን የወያኔና አዴፓ ቁማርም ሊሆን ይችላል ግን እውነት እንኳን ቢሆን በተግባር ከምናየው ይልቅ በሚነግሩን እንድንመሰጥላቸው ከማድረግ ያለፈ ብዙም ፋይዳ ያለውን ነገር ሆኖ አይቀጥልም፡፡ ምን አልባትም በአሳምነው ነው ተብሎ የተፈረጀውን የራሳቸውን ሴራ ትኩረት ለመቀየር የተደረገች ድራማም ትሆናለች፡፡ ከሁሉ በፊት እውነትና ፍትህን እንፈልጋለን፡፡ የዚህች የባህርዳርና የአዲስ አበባ የከፍተኛ ባለስልጣናትና ጀነራሎች እንዲሁም በዚሁ ሳቢያ በግፍ የተገደሉ ሌሎች ዜጎች ጉዳይ የፈለጋቸውን ነገር በራሳቸው ሚዲያና ጥሩ ይኖንልናል ባሏቸው መስመሮች ሁሉ በሚጡም ሁሉም መረጃ ተብለው እየቀረቡ ያሉት ነገሮች አሳዛኝ ቢሆኑም ብዙ ነገር እንድንታዘብ እድል ሰጥቶናል፡፡ ከመጀመሪያው መፈንቅለ መንግስት ተብላ ከታወጀችባት ሰዓት አንስቶ እስካሁንም እየወጡ ያሉት መረጃዎች እንዴት አንዱም እንኳን ለነጻ አእምሮ ላላቸው ዜጎች እልዋጥ ማለት ብቻም ሳይሆን መፈንቅለ መንግስት እያሉና እንደለጋቸው እየፈጠሩ ክስ የሚያቀርቡትን ለሴራው ዋና እንደሆኑ እያረጋገጠ የመጣ ይመስላል፡፡  ይህን ሴራ ተከትሎ በበርካታ ዜጎች ላይ በተለይም አማራ በሆኑ ላይ እንዲሁም አብይን በሚተቹ ላይ በተራ ውንጀላ ለክት ባአስቀመጡት የሽብር ህግ እያሰቃዩ ይገኛሉ፡፡ አዴፓ የተባለው ዛሬ በወያኔ ላይ ደነፋ ተብሎ ሁሉም አድናቂ የሆነለት ቡድን በተግባር ከዚህ ከምጠቅሰው ሴራ በኋላ ዋና የዜጎች አሳሪና አዋካቢ ነው፡፡ ስለዚህ ጉዳይ አንዳች ነገር ሳይናገር በወያኔ ላይ በመደንፋት እየሆነ ያለውን እውነት ሊያዘናጋን የሞከረ ይምስላል፡፡ እኔ የጠላቴ ጠላት ወዳጄ የሚል ነገር አይገባኝም፡፡ ወያኔን ተናገረልን ብሎ ይሄን ያህል መፈንደቅ እንደሕዝብ እየሆነብን ያለውን አለማስተዋል ቀጥሎም ራስን በወያኔ ሕግና ደንብ የተፈጠረውን ዛሬም ወደፊትም አዴፓ የተባለው ቡድን ዋና አባል የሆነበትን ኢሕአዴግ የተባለን በሐገርና ሕዝብ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደረስን ቡድን ተጨማሪ እድል በመሥጠት የራስን መከራ ማራዘም ነው፡፡ በተግባር ወያኔ ያስቀመጣቸው አንዳቸውም ሕግ በሉት ድንብ ሌላ ቀርቶ ሴራ ሳይቀር እንደወረደ እየተተገበረ ነው ያለው፡፡ አዴፓ የሚጠቀምበት ሥም የነበረውን በአዴንን ያወጣለት ወያኔ ነው፡፡ ዓርማው አድርጎ እንዲጠቀምበት የክልሉ ባንዲራ በሚል የቢጫና ቀይ ባለኮከብ ምልክት ባንዲራ የሰጠው ወያኔ ነው፡፡ ከወያኔው ባንዲራ ጋር በጣም ተመሳሳይም ነው፡፡ አማራ እንደሕዝብ ከአረንጓዴ ቢጫና ቀዩ ባንዲራ ውጭ ለክልሉ የራሱ ባንዲራ ያስፈልገዋል ከተባለ እንኳን በመጀመሪያ አረንጓዴ ቢጫና ቀይ ያረፈበት ምልክት ያለውን መሆን በተገባው፡፡ ባለኮከቡን የወያኔን ባንዲራ አማራ እንደማይቀበለው በይፋ አሳይቷል፡፡ አማራ ብቻም ሳይሆን አብዛኘው ኢትዮጵያዊ እንደማይቀበለው ግልጽ ሆኗል፡፡ የሚፈልጉት አሉ፡፡ አዴፓ መጀመሪያ ሕዝቡን በተግባር የሚፈልገውን ያድርግ፡፡

አብይ ዛሬም እመኑኝ ይለናል፡፡ እንግዲህ በወሬ እንደሚፈቱን ስለገባቸው እንዲሁ ቀጥለዋል፡፡ እመኑኝ ሲል ይሄ ስንት ጊዜው እንደሆነ ባይገባኝም ከሚባለው በላይ ራሱም ሊያምን ከሚችለው በላይ ሕዝብ አምኖት ነበር፡፡ በተግባር የከሀዲነት ሥራና ሴራን እያሴሩ እመኑኝ ማለት እስከ የት እንደሚቀጥል አይገባኝም፡፡ ዛሬ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የነበረውን ድባብ ስመለከት ከተመራቂ ተማሪዎች እንኳን ብዙዎች በአብይ ደስተኛ አልነበሩም፡፡ ከነበረው የተማሪ ብዛት አንጻር ለአብይ ሲጮሁ የነበሩት የሚያንሱት ነበሩ፡፡ ይሄ እውነታ ከዓመት በፊት ሆኖ ቢሆን ምን እንደሚመስል ማነጻጸሪያ በሆነን፡፡ የሆነ ሆኖ እመኑኝ የሚለው ሰው በተግባር ሕዝብን በመካድ ራሱ ያልታመነ እንጂ እኛ ኢትዮጵያውያን ከሀዲዎች አደለንም፡፡ ዛሬ ከአብይ ጋር የሚያጫፍሩት በአብዛኛው ለእውነትና ለሕሊና የቆሙት እንዳልሆኑ እናያለን፡፡ ሰሞኑን በእስክንድር ነጋ መግለጫ ላይ የሆነውን አይተናል፡፡ በመግለጫው ላይ ረብሻ የፈጠረው ጭራሽ በሚዲያ እንደ ልዩ እንግዳ ቀርቦ ቃለ መጠይቅ ሲደረግለት አይተናል፡፡ ይሄንን ነው ሰውዬው እመኑኝ የሚለን፡፡ ያለ እፍረትና ነውር የመንግስትን መዋቅር በራሱ ወሮበሎች አስይዞ እኛን እመኑ ይለናል፡፡

ሌላው ጀነራል ተማም ያው የተለመደውን የአሳምነውን ገዳይነት ሌላ ምስክር ሆነው ቀርበዋል፡፡ ቢያንስ ወታደራዊ  ስነምግባር አለ፡፡ እነዚህ ሰዎች ምን እየሰሩ እንደሆነ በትክክል የሚያውቁም አይመስለኝም፡፡ ጀነራሉ በድፍረትና ያለጥርጥር አሳምነውው ነው ማለታቸው ብቻም ሳይሆን እንዴት እንደሰራውም ነው ለጋዜጠኞች መግለጫ ሲሰጡ የነበረው፡፡ እንግዲህ ፍትህ ወዴት አለች፡፡ ከዚህ በኋላ ፍርድ ቤትስ ለምን ይኬዳል? የፍትህ አካሉን ጨምሮ በሥሩ ያደረገው ራሱን ግብረሀይል የሚለው ንዑስ በይፋ በአደባባይ የሐሰት መረጃ በማቅረብ ፍርዱንም ራሱ እየሰጠ በግልጽ  እናያለን፡፡ ጀነራሉም ይሄንኑ ነበር እያጸደቁ የነበሩት፡፡ በተመሳሳይ እኚሁ በአገር ደህንነት ትልቅ ቦታ አላቸው የሚባሉት ጀነራል ተመስገን ደሳለኝ የተባልን ጋዜጠኛ በግልጽ ሲዝቱበት አይተናል፡፡ ሲጀምር እንኳን በወታደራዊ ሥርዓት ኖሬያለሁ የሚል ማንኛውም ተራ ሰው እንዲህ የግሰብን ሥም እየጠራ ማስፈራራት ወንጀል እንደሆነ ማወቅ አለበት፡፡ በሌላ አገር ቢሆን ይሄ አይነት ድርጊት ከፍተኛ ወንጀል ሆኖ ጀነራሉን ፍርድ ቤት ባቀረበ ነበር፡፡ እንግዲህ እንዲህ ባለ ሁኔታ ያለን የአገርና ሕዝብ ፍትህ ነው ለውጥ እየተባለ ያለው፡፡

በመጨረሻም የዲያቆን ዩሴፍን ንግግር ሰማሁ፡፡ እንደእውነቱ ዲያቆን የሴፍ ከልብ በመነጨ መጨነቅ እየተናገሩ እንደሆነ አረዳለሁ፡፡ እንዳሉትም በእኛ ምክነያት ሕዝብና ሕዝብ ተጋጭቶ ለሚጠር ጥፋት በንስሀ እንኳን የምንድነው አደለም፡፡ እንዳሉትም በየፌስቡኩና ዩቲዩቡ የሚነገሩ ነገሮች እጅግ የሚከብዱ ናቸው፡፡ ያም ቢሆን ግን የኢትዮጵያ ዋና ችግር እነሱ አደለም፡፡ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ እየሆነ ያለው የዜጎች መፈናቀልና መገደል ሌላው ሁሉ ሴራ በአካል በየቦታዎች እየተዘዋወሩ ሴራዎችን በሚያዘጋጁና በሚያስፈጽሙ በመንግስት መዋቅር ላይ ስልጣን የያዘው አካል ከኋላ የሚደግፋቸው እንደሆኑ ሊረዱ ይገባል፡፡ ለጌዲዩ ሕዝብ መፈናቅል ፌስቡክና ዩቲዩብ አደሉም፣ ለቤኒሻንጉል ጭፍጨፋና መፈናቀል ዩቲውብና ፌስቡክ አደሉም፣ ለከሚሴና አጣዬ ሽብር ፌስቡክ ላይ ተሴሮ አደለም፣ ለችልጋው መፈናቀልና ግድያም ፌስቡክና ዩቲዩብ አደሉም፡፡ በአጠቃላይ እስካሁን አገሪቱ ውስጥ ለሁኑት ሁሉ ጥፋቶች ፌስቡክና ዩቲዩብ ላይ በሚለፈልፉ ስነምግባር የሌላቸው ግለሰቦች ምክነያት ነው ብሎ ነገሮችን አለቦታቸው ማሳበብ የእውነታውን ትኩረት ማዛባት ነው፡፡ ከዚህ በተቃራኒው ይልቅ የማህበራዊው ሚዲያ ተመሳሳይ ችግር ብዙ ጊዜ የተደገሰላቸውን አዲስ አበባን የመሳሰሉ ከተሞችን ቀድሞ መረጃውን በማውጣት ከብዙ ነገር የታደገ ይመስለኛል፡፡ እርግጥም ዜጎች ቤታቸውን አፍርሶ ሜዳ ላይ ሲጥል፣ ዜጎች በቡራዩና አካባቢው ሲገደሉ ለሕዝብ ይፋ በማድረግ፣ ዛሬ እስክንድር ነጋና ጓደኞቹ እየተፋለሙት ያለውን ነውርና ሥርዓት የለሽ የአብይን ቡድን በማጋለጥ እንዲሁም ሕዝቦች የተጎዱባቸውን ቦታዎች ለምሳሌ የጌዲዮን ይፋ በማድረግን እርዳታ እንዲደርስላቸው በማድረግ ከፍተኛ የሆነ አውንታዊ ሚና ተጫውቷል አሁንም እየተጫወተ ነው፡፡ እንደተባለው በፌስቡክና ዩቲዩብ ስነምግባር የጎደላቸውን ማስቆም ተገቢ ነው፡፡ አሁን ላለው በኢትዮጵያ ውስጥ እየተፈጸመ ላለው የዜጎች መገደልና፣ መፈናቀል እንዲሁም ፍትህ ማጣት ግን በዋናነት በመንግስት ስልጣን ላይ በአሉ እየተደገፈ በአካል እንደልቡ በየቦታው እየተንቀሳቀሰ ሽብር በሚፈፅ ቡድን መሆኑን ሁሉም ዜጋ ተረድቶ ይሄንኑ ለማስቆምና ለሕግ ለማቅረብ መሥራት አለበት እላለሁ!

ቅዱስ አምላክ እግዚአብሔር ኢትዪጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅ! አሜን!

ሰርፀ ደስታ

https://youtu.be/rJVm_xVVI6U