July 14, 2019
የማለዳ ወግ …ክቡር ሜ/ጄኔራል መሐመድ ግን ለምን ?* ጋዜጠኛ ተመስገን የህዝብ ልጅ ነው !* ለምን ማስፈራራት አስፈለገ ? ጋዜጠኛ ተመስገን ክብሩ የላቀ ነው !

የመከላከያው ጉምቱ ሜ/ጄኔራል መሐመድ ተሰማ እርስዎ የጀግናው መከላከያ ሰራዊት አባል በመሆን ታላላቅ ገድል የፈጸሙ ጀግና ሊሆኑ ይችላሉ ። ለሀገርዎ በከፈሉት መስዋዕትነት ያለኝ አክብሮት ታላቅ ነው። ከሰሞኑ የሰጡት መግለጫ ላይ የትንታጉን ጋዜጠኛ የተመስገን ደሳለኝን ስም እየጠሩ ያስተላለፉት ከሀገሪቱ ህገ መንግስት የሚጣረስ ማስፈራሪያ ግን አሳፍሮ አሸማቅቆኛል። ብዙ አልልም ፣ ግን ለምን ? ለምንስ አይበገሬውን ጉምቱ ሀገር ወዳድ ባለ ብዕር ማስፈራራት አስፈለገ ? ብየ እጠይቅዎታለሁ
ተመስገንን አያውቁትም !
================
የተከበሩ የጦር ባለሟል ሜ/ጄኔራል መሐመድ የሚያውቁት አይመስለኝም ። ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ እርስዎን ከመሰለ የጦር መኮንን የላቀ ገድል የፈጸመና የሚወደድ ብዕረኛ ነው ። ተመስገን በብዕሩ በከፈለው ብርቱ መስዋዕትነት ዛሬን እንድናይ ያደረገ ፣ ለዛሬው ለውጥ ትወልድ ይተጋ ዘንድ ያልታከተ የለውጥ ጀግናችን ነው ። ተሜ በእነ ጌታቸው አሰፋና በእነ በረከት ስምኦን የስለላ መዋቅር እየተጋፋ ዛሬን ያቀረበ ትንታግ ጎልማሳ ነው ። ተመስገን አልሸሽም ብሎ የህዝቡንና የሀገሩን በደል ከዳር እስከ ዳር ያሰተጋባ ትናንትም ዛሬም የተገፊዎች ድምጻችን ነው ። ተሜ ለማንም ሳያደገድግ ከጨቋኞች አፍንጫ ስር ሆኖ እውነትን ይዞ የሞገተ ስለ ኢትዮጵያ የኖረ ፣ የሚኖርና ስለ ኢትዮጵያ ግንባሩን ሳያጥፍ የሚሞት የጀግና ኢትዮጵያዊ የደም አጥንት ክፋይ መሆኑን አይዘንጉ ! ክቡር ጄኔራል ለመሆኑ ተሜ ልገልጸው በማይቻልኝ ሁሉ ፈተና እያለፈ ስለ ኢትዮጵያ ከነ ቤተሰቡ መስዋዕት የከፈለ ኩሩ ኢትዮጵያዊ መሆኑን አያውቁምን ?መንግስትን እንዳናምን አታድርጉን !
=======================
ክቡር ሜ/ጄኔራል መሐመድ መንግስትን ህዝብን እንዳያምን የሚያደርግና ለሚለያይ ዛቻና ማስፈራሪያ ሊያፍሩ ይገባል ።ተሜ ትናንት በክፉው ቀን ግንባሩን ለጥይት ሰጥቶ ስለ ፕሬስ ነጻነት የከበደ መስዋዕትነት የከፈለ ወንድ ነው ። ታሰሮ ተደብድቦ ፣ በህመም ተቀስፎ ለጨቋኞች ያልተበገረ ሀገር ወዳድ እንጅ ተራ ዘላን ልኩን የማያውቅ ወንበዴ አይደለም ። በዚህ ሀገርና ህዝብ በጭንቀት ባሉበት የከፋ ሰዓት ሌላ አጄንዳ መስጠተዎን ሳስበው በምክክር የማይሰራው የለውጥ አራማጁ መንግስት አካሄድ ያስፈራኛል ።በህግ አምላክ ፣ ህግ ያክብሩ !
====================
አዎ ፣ ጋዜጠኛው አይደለም ማንም ካጠፋና ጥፋት ካለ ጥፋተኛን በህግ ማዕቀፍ መጠየቅ ሲገባ ማስፈራራትና ዛቻ አግባብ አይደለም ። መከላከያ በጠራራ ጸሐይ የሚዘርፉትን ፣ የሚገሉ የሚያፈናቅሉት ከይሲዎች ያድንልን ። በመላ ሀገሪቱ ፊደራላዊ አስተዳደር በህግ ተጠይቀው መቅረብ ያልቻሉትን ወደ ህግ ፊት ያቅርብልን ! ክቡር ጄኔራል ጋዜጠኛ ተመስገን ህግና ስርአትን ተከትሎ ፣ የፕሬስ ፈቃድ አውጥቶ ፣ በህግና ስርአትን ስለ ሀገሩና ወገኑ ሰላም ፣ ዲሞክራሲና ፍትህ ሳይሰለች የሚዋደቅ ኩሩ ዜጋ እንጅ እርስዎ እንዳሉት አይደለም !
ክቡር ጄኔራል !
ህግ ካዎቁ ህግ ያክብሩ ፣ ህግ ካላዎቁ ከህግ አዋቂዎች ህጉን ይጠይቁ … ህግ ያክብሩ !!
በህግ ፊት ማናችንም እኩል ነን !
ከምስጋና ጋርነቢዩ ሲራክ
ሐምሌ 7 ቀን 2011 ዓም