

እስክንድር ነጋ ሊሰጠው የነበረው መ
14 July 2019
‹‹ኦዴፓ ያደራጀው የቄሮ ቡድን የለም››
የኦዴፓ ጽሕፈት ቤት ሕዝብ ግንኙነት መምርያ ኃላፊ
ከሁለት ሳምንታት በፊት በተፈጸመው ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች ግድያ ምክንያት የታሰሩ ሰዎችን በሚመለከት ጋዜጣዊ መግለጫ ለመስጠት በቢሮው ውስጥ በዝግጅት ላይ እያለ፣ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) ያደራጃቸው ቄሮዎች በፈጠሩት ረብሻ ምክንያት መስተጓጎሉን እስንክድር ነጋ ገለጸ፡፡
ኦዴፓ ያደራጀው የቄሮ ቡድን እንደሌለና ቄሮ ቀደም ብሎ የነበረውን ትግል ሲያግዝና ሲታገል የነበረ የወጣት ስብስብ እንጂ የተደራጀ ቡድን አለመሆኑን ደግሞ፣ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) ጽሕፈት ቤት የሕዝብ ግንኙነት መምርያ ኃላፊ አቶ ታዬ ደንደኣ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
እስክንድር ለሪፖርተር እንደገለጸው፣ በሐሰት ተጠርጥረው በእስር ላይ የሚገኙ የባለአደራ ምክር ቤት (ባልደራስ) አመራሮች፣ አባላትና ሌሎች በርካታ ወገኖች በታሰሩበት ቦታ፣ እየደረሰባቸው ያለውን ስቃይ በሚመለከት ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ለመስጠት ረቡዕ ሐምሌ 3 ቀን 2011 ዓ.ም. አራት ኪሎ በሚገኘው ኢቶጲስ ጋዜጣ ቢሮ ውስጥ በዝግጅት ላይ ነበር፡፡ መግለጫውን እንደሚሰጥና በእስረኞች ጉዳይ መሆኑን በድረ ገጾች ማሳወቁን ተከትሎ፣ ማክሰኞ ሐምሌ 2 ቀን 2011 ዓ.ም. ምሽት ጀምሮ የተለያዩ ማስፈራሪያዎች እንደደረሱትም ገልጿል፡፡
ማስፈራሪያው የተለመደና በተለያዩ መንገዶች እየተነገረው መሆኑን በመገንዘብ፣ መግለጫውን ለመስጠት ማልዶ ከቢሮው ሲደርስ ሲቪል የለበሰ ፖሊስ ወደ ቢሮው እንዳይገባ ክልከላ አድርጎበት እንደነበርም ተናግሯል፡፡ ከፖሊሱ ጋር ከተነጋገረና ብዙ ከተጨቃጨቀ በኋላ፣ ወደ ቢሮው እንደገባ በርካታ ጋዜጠኞች እንደመጡና መግለጫ በመስጠት ላይ እያለ ኦዴፓ ያደራጃቸው የቄሮ ቡድን አባላት የተለያዩ ሰው ማጥቂያ ስለቶችንና ሽጉጦችን፣ እንዲሁም ለታዳጊ ወጣቶችና ብዙም ማገናዘብ ለማይችሉ ታዳጊ ሕፃናት አዕምሮ ጥበቃ ሲል ሊናገረው የማይፈልገውን ማጥቂያ መሣሪያ ይዘው ወደ ቢሮ መግባታቸውን አስረድቷል፡፡
መንግሥት ጭምር ካለፈው አንድ ዓመት ወዲህ ተገቢ ያልሆነ ሕግ መሆኑን ተቀብሎና አቋም ወስዶ በመሻሻል ላይ የሚገኝን የፀረ ሽብር ሕግ ከመሬት በማንሳት በርካታ ዜጎችን ማሰሩን፣ ይኼም የህሊና እስር መሆኑን ገልጿል፡፡ ታሳሪዎቹ እንዴት በስቃይ ውስጥ ታስረው እንደሚገኙ ለጋዜጠኞቹ በመግለጽ ላይ እያለ ቡድኑ ጥሶ ገብቶ ለመደብደብና ሕገወጥ ዕርምጃ ለመውሰድ መሞከሩ ሕገወጥነት ነው ብሏል፡፡ ተዘጋጅተውና አስበውበት ስለመጡ በሌሎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ በሚል እሱ በሌላ በር ወጥቶ በመሄዱ፣ ከሚደርሰው አደጋ ጋዜጠኞቹንም ሆነ የቢሮ ሠራተኞችን መታደጉን ተናግሯል፡፡
ኦዴፓ ማደራጀቱንና የቄሮ ቡድን መሆኑን እንዴት እንዳወቀ የተጠየቀው እስክንድር በሰጠው ምላሽ፣ ኦዴፓ ያደራጃቸው ቄሮዎች የሚይዙት ሰንደቅ ዓላማ መንግሥት የሚጠቀምበትን ባለ ኮከቡን ነው ብሏል፡፡ የዚያንም ቀን የያዙት እሱን ባንዲራ መሆኑን፣ ሁሉም የኦዴፓ አባላትና ሁሉም ቄሮዎች ሳይሆኑ ለውጥ አለ ብለው የሚምኑና መንግሥት የሚጠቀምበትን ሰንደቅ ዓላማ እንደሚያምኑበት የሚናገሩት ኦዴፓ ያደረጃቸው ቄሮዎች ብቻ መሆናቸውን ስለሚያውቅ፣ እነሱ መሆናቸውን እንዳረጋገጠ ተናግሯል፡፡
የደረሰበትን ችግር በሚመለከት ለፖሊስ ስለማሳወቁም ተጠይቆ፣ ለፖሊስ እንዳላመለከተ ተናግሯል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የእሱ እምነት መካሰስ ሳይሆን፣ እነሱም ሆነ እሱ ባላቸው መብት ተጠቅመውና ባላቸው ሐሳብ ላይ ተወያይተው ባይስማሙ እንኳን፣ በሕዝብ ፊት ቀርበው ሕዝብ እንዲዳኛቸው የሚፈልግ መሆኑን ገልጿል፡፡
እነሱም ሆኑ እሱና የእሱ ጓደኞች ያለ ምንም ተፅዕኖ በነፃነት መንቀሳቀስ እንጂ፣ መደባደብ፣ መፈነካከትና መጎዳዳት እንደማይፈልግ የገለጸው እስክንድር በውዝግብ፣ በንትርክና በድብድብ የሚፈታ ነገር እንደሌለ ገልጿል፡፡ ችግሮች የሚፈቱት በምርጫና በምርጫ ብቻ መሆኑንም ተናግሯል፡፡ በፖለቲካ አረደድ፣ በርዕዮተ ዓለም፣ በራዕይና በምርጫ ውጤት መሠረታዊ ልዩነት እንዳላቸው ተናግሮ ልዩነቱ ጤናማ ቢሆንም፣ መጥፎ የሚሆነው የሚገለጽበት ሁኔታ መሆኑንም አስረድቷል፡፡ መደራደርና መነጋገር እንደሚፈልግ፣ መወያየት ከቻሉ ሊስማሙ እንደሚችሉና እስከ ምርጫ ድረስ በሰላም ሊኖሩ እንደሚችሉም አክሏል፡፡ ያደረጉት ነገር ትክክል አለመሆኑንም አውቀው ይቅርታ እንዲጠይቁም አሳስቧል፡፡
መንግሥት ተጠርጣሪዎቹ በባህር ዳርና አዲስ አበባ ላይ ከተፈጸመው ግድያ ጋር ተያያዥነት ባላቸው የሽብር ተግባር ወንጀሎች መጠርጠራቸውን በመጥቀስ በፀረ ሽብር አዋጁ መሠረት ፍርድ ቤት ቀርበው 28 ቀናት ለተጨማሪ ምርመራ ቀጠሮ ተሰጥቶባቸው እያለ፣ እንዴት የህሊና እስረኞች ሊባሉ እንደተቻለ እስክንድር ተጠይቆ፣ እሱ ሰበብ ነው ብሏል፡፡ ‹‹ኢሕአዴግ ተቃዋሚዎቹን ለመደፍጠጥ የተጠቀመበት ዘዴ ነው፡፡ ዓለም ያወቀው መሆኑንና የራሱ የውስጥ ችግር መሆኑን እያወቀ ሲቪሎችን ያለምንም ጥፋታቸው በማሰሩ፣ ሁሉም የህሊና እስረኞች ናቸው፤›› ብሏል፡፡
ቢሮ ድረስ ተገኝተው ጋዜጣዊ መግለጫውን እንዳይሰጥ በመረበሽ ያቋረጡት ኦዴፓ ያደራጃቸው ቄሮዎች ናቸው ስለመባሉ ማብራሪያ እንዲሰጡ የተጠየቁት የኦዴፓ ጽሕፈት ቤት የሕዝብ ግንኙነት መምርያ ኃላፊ አቶ ታዬ ደንደአ እንደገለጹት፣ ኦዴፓ ያደራጀው ቄሮ የለም፡፡ ‹‹ቄሮ የተደራጀ ኃይል አይደለም፡፡ ወጣት የኅብረተሰብ ክፍል ነው፡፡ ቀድሞ በነበረው ችግር ጊዜ አንድ ላይ የተሰባሰበና የታገለ እንጂ የተደራጀ አይደለም፡፡ ይኼ ዝም ተብሎ ስም ለማጥፋት የተደረገ ነው፤›› ብለዋል፡፡
አዲስ አበባ የሚያስተዳድሯት የሕዝብ ፓርቲዎች እንዳሉ የገለጹት አቶ ታዬ፣ ሁሉም የኢትዮጵያ ወጣት የሚኖርባት ከተማ ከመሆኗ ውጪ የተለየ ወጣት እንደሌለም አክለዋል፡፡ አደረጃጀቱም በዚያው ልክ በመሆኑ ኦዴፓ ላይ የቀረበው ክስ መሠረተ ቢስና ከኦዴፓ ጋር የሚያገናኘው ነገር እንደሌለም ገልጸዋል፡፡ ለእስክንድር መልስ መስጠት የሚመጥን ባይሆንም፣ ራሱን መንግሥት እንደሆነ በመሰየሙ የሚቃወመው ሰው ካለ መቀበል እንዳለበትም አክለዋል፡፡