
Woodys Aeroimages አጭር የምስል መግለጫ ከዚህ ቀደም የተነሳ እና አሁን የተነሳው የቦይንግ “737 ማክስ” አውሮፕላን ስያሜ በ “737-8200” መቀየሩን ያሳያል
ቦይንግ ለራይናኤር ሊያስረክብ ያዘጋጀው 737 ማክስ አውሮፕላን አፍንጫው አካባቢ የስም ለውጥ እንደተደረገበት ታየ።
ትዊተር ላይ ሰዎች እየተጋሩት ያለው ምስል እንደሚያሳው፤ በቦይንግ ማምረቻ ፋብሪካ ውስጥ የራይናኤር አርማና ቀለም የተቀባው አውሮፕላን 737 ማክስ የሚለው ስም 737-8200 በሚል ተቀይሮ ይታያል።
737 ማክስ ከደረሰበት ሁለት አደጋ በኋላ በዓለም ዙሪያ እንዳይበር ታግዶ እያለ፤ ስሙን በመቀየር ገበያውን ለመቀላቀል እየሞከረ ነው በሚልም መነጋገሪያ ሆኗል።
ቦይንግም ሆኑ ራይናኤር ምንም ያሉት ነገር የለም።
• ቦይንግ 737-8 ማክስ አውሮፕላኖቹ በሙሉ እስከ ግንቦት እግድ ተጣለባቸው
• ስለምንጓዝበት የአውሮፕላን አይነት እንዴት ማወቅ እንችላለን?
ካለፈው መጋቢት ጀምሮ ማክስ አውሮፕላኖች ከነበረባቸው የሶፍትዌር ችግር ጋር በተያያዘ የኢንዶኔዢያና የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላኖች ተከስክሰው 346 ሰዎች ከሞቱ በኋላ አንድም ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን በሮ አያውቅም።
ራይናኤር፤ 135 ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖችን ያዘዘ ሲሆን፣ የመጀመሪያዎቹ አምስቱ እስከ ህዳር ድረስ አልቀው ይሰጣሉ ተብሎ ቀጠሮ ተይዞላቸው ነበር።
በዋሺንግተን በቦይንግ ሬንቶን የአውሮፕላን ማምረቻ ቅጥር ግቢ ውስጥ የተነሳው ምስል፤ በፊትና አሁን የነበረውን የአውሮፕላን ገፅታን የሚያሳይ ሲሆን፤ የራይናኤር ቦይንግ ማክስ 8 አውሮፕላን ላይ የስም ለውጥ መደረጉ በግልፅ ይታያል።
ምንም እንኳ አንዳንድ አካላት ቦይንግ 737 ማክስ 8 በሌላ ስም ገበያውን ሊቀላቀል ነው ቢሉም፤ ቦይንግ ራሱ አውሮፕላኑን እንደገና በሌላ ስም ለማውጣት ስለመወሰኑ ምንም ያለው ነገር የለም።
ባለፈው ወር ፓሪስ ላይ በነበረው የአውሮፕላኖች አውደ ርዕይ፣ የዓለም አቀፉ አየር መንገዶች ቡድን 200 ማክስ አውሮፕላኖችን በቅናሽ ሊገዛ መሆኑን አሳውቆ ነበር። የአውሮፕላኖቹ ስም ቢ737 እንደሆነ በወቅቱ ተገልጿል።
የአሜሪካ የፌደራል አቪየሽን አስተዳደር አውሮፕላኑ ዳግም ወደ በረራ እንዲገባ ፈቃድ መስጠት የሚጠበቅበት ሲሆን፤ ይህ ከመሆኑ በፊት ግን ባለፈው ወር በአውሮፕላኑ ላይ አዲስ ችግር ተገኝቶ ይህንን ለመጠገን እስከ መስከረም ጊዜ እንደሚፈልግ ቦይንግ አስታውቆ ነበር።
ቦይንግ የማክስ አውሮፕላኖች ደህንነትነን ለማረጋገጥ የሶፍትዌር ማሻሻያ ማድረግ ብቻ በቂ መሆኑን ተቆጣጣሪ አካላቱን ማሳመን ይጠበቅበታል።