July 16, 2019

አዲስ አበባ ፣ ሃምሌ 8 ፣ 2011 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል በጥረት ኮርፖሬት ስር የሚተዳደሩ ከአስር በላይ ኩባንያዎች በአክሲዮንና በሽያጭ ወደ ግል እንዲዛወሩ መወሰኑን የኮርፖሬሽኑ ምክትል ስራ አስፈፃሚ አስታወቁ።

ምክትል ስራ አስፈጻሚው አቶ አባተ ስጦታው ኩባንያዎቹን በአክሲዮንና ሙሉ በሙሉ ሽያጭ ወደ ግል ለማስተላለፍ መወሰኑን ከኢዜአ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

የክልሉ ህዝብ በአሰራር ግልፀኝነት መጓደል ምክንያት በጥረት ኮርፖሬት ኩባንያዎች ላይ ጥርጣሬ እንደነበረው ምክትል ስራ አስፈጻሚው ጠቅሰዋል።

ኩባንያዎቹ ለህዝቡ የተሟላ ጠቀሜታ ይሰጡ ዘንድም በአክሲዮንና በሽያጭ ወደ ግል እንዲተላለፉ መወሰኑን አስታውቀዋል።

በጥረት ኮርፖሬት ስር ከሚተዳደሩት ኩባንያዎች መካከል አምባሰል ንግድ ስራዎች፣ ጥቁር አባይ ትራንስፖርት፣ የባህር ዳርና ኮምቦልቻ ጨርቃጨርቅ ኩባንያዎች እና ሌሎችም የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች ይገኙበታል።

ከ20 ዓመታት በፊት በ20 ሚሊየን ብር ካፒታል የተቋቋሙት የጥረት ኮርፖሬት ኩባንያዎች በንግድና ትራንስፖርት፣ በማምረቻው ዘርፍና በግብርና ምርቶች ማቀነባበር ላይ የተሰማሩ ናቸው።

በአሁኑ ወቅት ለ12 ሺህ ሰዎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል የፈጠሩት እነዚህ ተቋማት በአክሲዮንም ሆነ ሙሉ በሙሉ ለመግዛት ፍላጎት ያላቸው የክልሉ ባለሀብቶች በንቃት በመሳተፍ ራሳቸውንም ሆነ ህዝባቸውን እንዲጠቅሙ ምክትል ስራ አስፈፃሚው ጥሪ አቅርበዋል።

የአማራ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ትልቅ ሰው ይታያል በበኩላቸው የጥረት ኮርፖሬት ኩባንያዎች በክልሉ ህዝብ ላይ አመኔታ አጥተው መቆየታቸውን ጠቅሰው፥ አሁን ላይ ለህዝብ ጥቅም እንዲሰጡ እየተሰራ ነው ብለዋል።