
የሱዳን ወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤትና ተቃዋሚዎች ሌሊት ሙሉ የዘለቀ ድርድር አድርገው ለወራት የዘለቀውን ግጭት ሊያስቆም ይችላል የተባለና ስልጣን ለመጋራት የሚያስችል ስምምነት ላይ መደረሳቸው ተነገረ።
ስምምነቱን ተከትሎ የገዢው ወታደራዊ ምክር ቤት ምክትል ሊቀመንበር የሆኑት ሞሃመድ ሐምዳን “ሐሜቲ” ዳጎሎ ኤኤፍፒ የዜና ወኪል “ለሃገሪቱ ታሪካዊ ወቅት” ማለታቸውን ዘግቧል።
ሮይተርስ የዜና ወኪል እንደዘገበው ይህ ስምምነት የተፈረመው ሁለቱ ወገኖች ልዩነታቸውን ለማቻቻል ሌሊቱን በሙሉ ሲደራደሩ ከቆዩ በኋላ ነው።
• የቀድሞ የመንግስት ባለስልጣናት በቁጥጥር ስር ዋሉ
• የሱዳንን መፃዒ ዕድል የሚወስኑት የጦር አበጋዝ
ስምምነቱ ለሦስት ዓመታት የሚቆይ የጋራ መንግሥት እንዲኖር የሚያደርግና ከዚያም በኋላ አጠቃላይ ምርጫ እንዲካሄድ የሚያስችል ነው ተብሏል። እዚህ ስምምነት ላይ ለመድረስ እስካሁን ያልተቻለው ለወታደራዊ አስተዳደሩ ያለመከሰስ መብት ለመስጠት በቀረበው ሃሳብ ላይ መግባባት ባለመቻሉ ነበር።
ተቃዋሚዎች እንዳሉት ከመብት ረገጣ ጋር በተያያዘ ለወታደራዊ መኮንኖች ያለመከሰስ መብት እንዲሰጥ የቀረበውን ጥያቄ ተቃውመውታል። በዚህም ሰኔ ወር ላይ ለተቃውሞ የወጡ ከ100 በላይ የሚሆኑ ሰዎች በመንግሥት ኃይሎች ተገድለዋል ብለው ይከሳሉ።
ለሦስት አስርት ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ ሱዳንን የመሩት ኦማር አልበሽር ሚያዚያ ላይ ከስልጣን ከተባረሩ በኋላ በሲቪሎች የሚመራ የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም የሚጠይቁ የተቃውሞ ሰልፎች በመላው ሱዳን ሲካሄዱ ቆይተዋል።
• የሱዳን የቀድሞ ፕሬዚዳንት አል በሽር ተከሰሱ
ሁለቱ ወገኖች የሃገሪቱ ስልጣን የበላይ አካል የሆነውን ምክር ቤት እየተፈራረቁ ለሦስት ዓመታት ለመምራት የተስማሙ ሲሆን በተጨማሪም ሕገ መንግሥትን በተመለከተ በመጪው አርብ ከስምምነት ደርሰው እንደሚፈራረሙ ይጠበቃል።
የተቃዋሚው የሱዳን ሙያተኞች ማህበር ቃል አቀባይ የሆኑት ዶ/ር ሳራ አብደልጋሊል ስለስምምነቱ ለቢቢሲ እንደተናገሩት “ስልጣን የመጋራት ስምምነቱ የመጀመሪያ እርምጃ ቢሆንም በዝርዝር ግን አልተቀመጠም። ሁለተኛው ዙር ውይይትም ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌን ይመለከታል” ብለዋል።
አክለውም በሁለቱ ወገኖች መካከል የተደረሰው ስምምነት ፍርሃትና ተስፋን እንደፈጠረባቸው ጠቅሰው ለአሁኑ “ሊያስፈነድቅ የሚችል ነገር የለም” ብለዋል።