July 17, 2019 

 Source:https://voiceofgihon.com

መግቢያ፤

ሥርዓት-ጠልነት ወይም አናርኪዝም በ19ኛው ክፍለ-ዘመን አጋማሽ ኢንዱስትሪያዊ ካፒታሊዝምን እና ፖለቲካዊ ኢኮኖሚን በመቃወም በአውሮጳ የተወለደ ፖለቲካዊ ፍልስፍና ሲሆን ከፈረንሳያዊው ፔሬ-ጆሴፍ ፕራዦን ጀምሮ እንደ ኢማ ጉድዊን፣ ፒተር ክሮፖትኪን፣ ሚካኤል ባኩኒን፣ ሉሲ ፓርሰንስ ወዘተ በጽሑፋቸው እና በድርሰቶቻቸው ያበለፀጉት ፅንሰ ሐሳብ መሆኑ ይነገራል።

አናርኪዝም ገዥዎች ወይንም መንግሥታት መዋቅሮቻቸውን በመጠቀም ህዝብን ይመዘብራሉ ይበድላሉ የሚል መነሻ ያለው ሲሆን መንግሥት፣ መዋቅር፣ የአስተዳደር እርከን እንዲሁም ሌሎች እኩል ተጠቃሚነትን እና ፍትኃዊነትን የሚያጓድሉ በመሆኑ አስፈላጊ አይደሉም፤ ህዝብ መተዳደር ያለበት በራስ ገዝነት (autonomy)፣ በተጓዳኝነት (horizontalism)፣ በመተጋገዝ (mutual aid)፣ በአብሮነት (solidarity) እና ህዝቡ በሚውስዳቸው ቀጥተኛ ተግባራት (direct actions) ነው የሚል እንቅስቃሴ ነው።

አናርኪዝም ማለት ሥርዓት አልበኝነት ማለት አይደለም፤ አናርኪዝም መንግሥታዊ አስተዳደር እና መዋቅር በህዝብ ከሚያደርሰው ግፍ በመንገፍገፍ የሚመጣ ሥርዓት-ጠልነት ነው። አናርኪዝም የካፒታሊዝም ገበያ ሥርዓትንም ሆነ በተለያየ ጊዜ መጥተው የሄዱትን ሶሻሊስታዊ የገበያ ሥርዓቶች አይቀበልም። የሰው ልጅ ነጻ ሆኖ በመፈጠሩ ማናቸውንም ነገሮች በመረጠው መንገድ ማድረግ መቻል አለበት ይህንን ፍላጎቶን እንዳያከናውን እንቅፋት የሚሆኑ ነገሮች መኖር የለባቸውም ብሎ ያምናል።

ዲቪድ ዲ’ማቲዮ የአናርኪዝምን ባህርይ እንዲህ ሲል ይገልፀዋል፤ 《Anarchism takes seriously the idea that if all people are equally free and equally entitled to dignity and autonomy, then no individual or group can have the right to impose upon or violate anyone. Anarchists see that today’s crises, social, environmental, and economic, are the problems of largeness, of unaccountable monoliths in both the so-called public and private sectors》

ዲ’ማቲዮ እንዳስቀመጠው አናርኪዝም መነሻው ጭቆናን መጥላት የሆነ በመንግሥት መዋቅር ሥር ያለን ሁሉ የመቃወምና የማማረር እና ህገ-ልቦናን ተከትሎ የመተዳደር እሳቤ ነው።

በአንፃሩ ሥርዓት-አልበኝነት ማለት በሥርዓቱ መኖር ላይ ጥያቄ የሌለው ቡድን ወይንም አካል ሆነ ብሎ ህግና ሥርዓት እንዳይከበር ሲንቀሳቀስና ለማዕከላዊ መንግሥቱ ታዛዥነት ሳይኖረው ሲቀር ነው። ይኸውም የመንግሥትን አስተዳደርና መዋቅር ጭምር ተጠቅሞ እኩይ ተልዕኮዎችን የመፈፀምና ወንጀለኛ እንዳይያዝ ሽፋን መስጠት ጭምር ማለት ነው።

ሀ) በ”የኦሮሞ ክልል” የነገሰው ሥርዓት-አልበኝነትና በአማራ ህዝብ ላይ ያለው አደጋ

ኢትዮጵያ ውስጥ የወያኔ ኢህአዴግ መንግሥት ኃይለማርያም ደሳለኝን በአብይ አህመድ ከተካ ወዲህ አገሪቱን መቆጣጠር ባለመቻሉ ሥርዓት-ጠልነት እና ሥርዓት-አልበኝነት ሰፍነዋል። በጥቅሉ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የተፈናቃይ ቁጥር መመዝገቡ ይህንን የሚያሳይ ነው(Over 3 million internal displacements)። ይህ ሥርዓት-ጠልነት እና ሥርዓት አልበኝነት በተለያየ አካባቢ የተለያየ መልክ ያለው ነው። “በኦሮሞ ክልል” የተንሰራፋው ሥርዓት-አልበኝነት ሲሆን በተረኛነት ስሜት የተፈጠረ ሐብት እና መሬት የማግበስበስ እንዲሁም ግዛት የማስፋት እና ከህግ ራዳር ውጭ የመሆን እንቅስቃሴ ነው።

ሥርዓት አልበኝነቱ ሥርዓቱን በሚደግፉ ሥርዓቱም በሚደግፋቸው ኃይሎች የሚፈፀም በመሆኑ የሥርዓት አልበኝነቱ አሉታዊ ተፅዕኖ ጎልቶ የሚታየው በሥርዓት-አልበኛው “የኦሮሞ ክልል” ሳይሆን በተቀረው ኢትዮጵያዊ በተለይ ደግሞ በተለያዩ አካባቢዎች ኑሮውን ባደረገው አማራው እና በደቡብ ህዝብ እንዲሁም በየጊዜው ተገደሉ ሲባል በምንሰማው የውጭ አገር ዜጎች ላይ ነው። ለአብነትም የቡራዩውን ጭፍጨፋ፣ የሻሸመኔውን ስቅላት፣ የለገጣፎውን ማፈናቀል፣ ከ20 በላይ የሆኑ ባንኮች ዝርፊያ፣ የጌዲዮ ህዝብ ረሃብ፣ የህንድ ኢንቨስተሮች መገደልና አስከሬናቸው መቃጠል፣ የቻይና ዜጎች ላይ የደረሰው ከፍተኛ ጉዳትና ግድያ እና የመሳሰሉትን በማንሳት ተረኞች በማናለብኝነት ያነገሱትን ሥርዓት-አልበኝነት ማሳየት ይቻላል። በመሆኑም በ”ኦሮሞ ክልል” የተከሰተው ሥርዓት-ጠልነት ወይም አናርኪዝም ሳይሆን ሥርዓት አልበኝነት ነው።

ይህ ሥርዓት-አልበኝነት አሁን ባለው ሁኔታ ከቀጠለ የሚሊዮኖችን ህይዎት የሚቀጥፍ እና ለስደት የሚዳርግ የእርስበርስ ጦርነት ሊያስከትል ይችላል። በዚህ ደግሞ ግንባር ቀደም ተጎጅ የምንሆነው አንድ ወደ ፊት ሁለት ወደኋላ እየተመለስን በቁርጠኝነት መደራጀት ያልቻልነው አማሮች ነን።

ለ) ሥርዓት-ጠልነት እና ሥርዓት-ጠልነትን ታክኮ የመጣው ጥቅመኝነት “በአማራ ክልል” የፈጠረው የጥፋት ድባብ

በአንፃሩ በ”አማራ ክልል” እየታየ ያለው የ”ኢህአዴግ”ን ሥርዓት በአጠቃላይ በልዩ ሁኔታ ደግሞ የኦሮሞን ተረኛ ብሔርተኞች እና ህወሓቶችን በመጥላት የመጣ ሥርዓት-ጠልነት ወይንም አናርኪዝም ነው። ለሥርዓት-ጠልነቱ መወለድ ገፊ ምክኒያት ህወሓት በአማራ ህዝብ ላይ ያደረሰው ግፍ እና የአማራ ህዝብ በሌሎች ወንድምና እህት ሕዝቦች በጠላትነት እንዲፈረጅ ማድረጉ ነው።
የአማራ ህዝብ የህወሓት-ወያኔን ሥርዓትና በተረኝነት የመጣውን የኦዲፒ-ወያኔ ሥርዓት በመጥላቱ ምክኒያት ወደ ተለያዩ አካባቢዎች በመጓጓዝ ላይ የነበሩ ምርትና ሸቀጦችን የማስቆም እንቅስቃሴ ማድረጉ የሚታወስ ነው። የአናርኪዝም አይዲዮሎጅ ፈላስፋዎች እንደሚከራከሩት ይህን ዓይነት እንቅስቃሴ “direct action” የሚባለው እና ማኅበራዊ ፍትኅን በራስ ለመወሰን (የደቦ ፍርድ የሚባለውን) የሚደረግ ጥረት አካል ነው። በእርግጥ ነጋዴዎቹ ንብረታቸውን እስካልተቀሙ ድረስ የንግድ መሥመር መዝጋት ሊያስወቅስ የሚችል ነገር አልነበረውም እንደ ሠላማዊ የትግል ሥልት ሊታይ የሚችል ነው። ነገር ግን ከመሥመር ከመዝጋት እልፍ ያሉ የራስን ህዝብ የሚጎዱ እንቅስቃሴዎች የተደረጉ እና እየተደረጉ ያለ በመሆኑ በሥርዓት-ጠልነት መነሻነት የመጣው አናርኪዝም ሥርዓት አልበኝነትን ደርቦ የህዝብ ትግል አደጋ ላይ እንዳይወድቅ ያሰጋል። ስጋቱን በሁለት ነባራዊ ምክኒያቶች በትኩረትና በጥልቀት ማየት ያስፈልጋል።

የመጀመሪያው የአማራ ህዝብ ትግል ከመነሻው በነበረው መንፈሥ ህልውናን የማስቀጠል፤ የኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ መገለልን የመከላከል፤ ፍትኅና እኩልነትን የማረጋገጥ ሁለንተናዊ ትግል መሆኑ ቀርቶ በተወሰነ መልኩ ጥቅም ወደ ማሳደድና ግለሰባዊ ፍላጎትን ማርኪያነት መሸጋገሩ ነው። በማይጠበቅ መልኩ ለህዝብ ትግል ይጠቅማሉ ተብለው የታመኑ ግለሰቦች በጥቅም ወጥመድ ውስጥ ተዘፍቀው ተገኝተዋል። ለህዝብ ትግል የነበረው መንሰፍሰፍና ቀናዒነት የራሥን ህዝብ ወደ መበደል፣ ባለሃብቶችን ወደማስገደድና መዝረፍ፣ መታበይ እና ከእኔ በላይ ላሳር ባይነት ወርዷል። እንዲህ ዓይነት የባህርይ ለውጥ በአታጋይ አካላት ላይ መንፀባረቁ ሥርዓት-ጠልነቱን መልኩን ወደ ጥቅመኝነት እየተቀየረ መምጣቱን ያሳያል።

በሌላ በኩል ጠንቀኛ የሆኑ አጀንዳዎች በህዝብ ትግል ስም እየተራመዱ ይገኛሉ። ከሳሽና ተከሳሽን ለመለየት በሚያስቸግር ሁኔታ እርስበርስ መፈራረጅ እና ጣት መጠቋቆም በዝቷል። ከውስጥም ከውጭም ያሉ ኃይሎች አስርገው የሚያስገቧቸው አጀንዳዎች የህዝባችን አንድነት ሊፈትኑ ወደሚችሉበት አዝማሚያዎች እያመሩ ይገኛሉ። ችግሩ በስፋትና በጥልቀት እንዲሁም በጉልህ የሚታይ ቢሆንም አጀንዳዎቹን ለይቶ አውጥቶ ፊትለፊት በቆራጥነት ተጋፍጦ ለማረም አልተሞከረም እንዲያውም ስውር አጀንዳ ያላቸው ቡድኖች የፕሮፓጋንዳ የበላይነት በመውሰድ ችግሩን ለመጋፈጥና መፍትሔ ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት እያደናቀፉና በሥርዓት-ጠልነቱ ላይ ሥርዓት-አልበኝነት እንዲደረብበት እያደረጉ ይገኛሉ። በህግና ሥርዓት መከበር (Due process of law) ጥርጣሬ ያለው ማኅበራዊ እሳቤ እንዲፈጠርም እየገፋፉ ይገኛሉ። ሰኔ 15 ያየነው የአራቱ ከፍተኛ አመራሮች ግድያና ከ50 በላይ የሚሆኑ የ”ክልሉ” የፀጥታ ባልደረቦች ሞት እንዲሁም ሁኔታውን ተከትሎ እየተፈፀመ ያለው የጅምላ እስር እና ያንን ተከትሎ የመጣው እሰጣገባ ዋና ማሳያዎች ናቸው።

በሌላ በኩል ምንም እንኳን ከተለያየ አቅጣጫ በሚመጣ ውስጣዊና ውጫዊ ግፊትና እፍግታ የ”ክልሉ”ን ሁኔታ እንደ በሬ ቆዳ ከቀኝም ከግራም የተወጠረው ቢሆንም የሕዝቡ መረጋጋት፣ ሠላምና አንድነት ወዳድነት፣ ሆደሰፊነት እና አርቆ አሳቢነት ጠንካራ ማኅበረሰባዊ መሠረት ያለው በመሆኑ ችግሩ እንዳይባባስ አርግቦ ይዞታል። በተመሳሳይ ሰዓት ፈንድተው አካባቢውን ሶሪያና የመን ሊያደርጉ የሚችሉ በተለያዩ የውጭና የውስጥ ኃይሎች የተጠመዱ ቦንቦችን አንድ በአንድ እያመከነ ይገኛል። በእውነቱ ይህ የሚደነቅ ነው። ነገር ግን መፍትሔ ካልተበጀለት ምን ያህል ጊዜ ሳይሸረሸር ይቆያል የሚለው አሳሳቢ ነው።

ሐ) በ”ደቡብ ክልል” የወያኔ ርዕዮተ-ዓለም/የፖለቲካ ፍኖት ክሽፈት የፈጠረው ድርብርብ ቀውስ እና በአማሮች ላይ የሚፈጥረው ተፅዕኖ

[ … ይቀጥላል]