
የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ብሔር ብሔረሰብና ሕዝቦች የሚለውን ጨፍልቆም ቢሆን ይበይነዋል፤ የተናጥል ትርጉም ግን ፈልጎ ማግኘት አይቻልም። በመካከላቸው ስላለው ልዩነትም የተብራራ ነገርም የለም።
ለብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝብ የሰጠው የወል ትርጉም በአንቀጽ 39፤ 5 ተቀምጧል።
“…ሰፋ ያለ የጋራ ጠባይ የሚያንጸባርቅ ባሕል ወይም ተመሳሳይ ልምዶች ያላቸው፣ ሊግባቡት የሚችልሉበት የጋራ ቋንቋ ያላቸው፣ የጋራ ወይም የተዛመደ ሕልውና አለን ብለው የሚያምኑ….” እያለ ባሕርያቸውን ይተነትናል።
ተባባሪ ፕሮፌሰር ዮናታን ተስፋዬ ፍሰሀ በዩኒቨርስቲ ኦፍ ዌስተርን ኬፕ የሕግ መምህር ሲሆኑ፤ በፌደራሊዝም ጉዳዮች ላይ በተለያዩ የምርምር ሥራዎች ይሳተፋሉ።
እንደ እሳቸው አባባል በሕገ መንግሥቱ ዙሪያ የተደረጉ ውይይቶችም ቢሆኑ ማነው ሕዝብ?፣ ማነው ብሔረሰብ?፣ ማነው ብሔር? ለሚለው እቅጩን መልስ አያስቀምጡም። በሕገ መንግሥቱም ቢሆን ይህ የተናጥል ትርጉም አልተቀመጠም፤ ቢሆንም ግን… ይላሉ ዮናታን (ዶ/ር) “ቢሆንም ግን ይህ አለመሆኑ ከሕገ መንግሥቱ አንፃር ብዙም ለውጥ አያመጣም።”
ይህንን ሐሳብ ሲያፍታቱት፤ ብሔር ስለሆንክ ይህን ታገኛለህ፤ ብሔረሰብ ስለሆንክ ያንን ታጣለህ ብሎ የሚያስቀምጠው ነገር የለም ይላሉ።
ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሰላምና ደህንነት ጥናት ተቋም መምህር ናቸው። ብሔር ማነው? ብሔረሰብስ? ሕዝብስ? ለሚለው መልሳቸው “የመጣው ከጆሴፍ ስታሊን ነው፤ ሶሻሊስታዊ አስተሳሰብ ነው ነው” ይላሉ። ለሳቸው ይህ አብዛኛውን ጊዜ አምባገነኖች ሕዝቡን ከፋፍሎ ለማስተዳደር የሚጠቀምበት መሣሪያ ነው።
• “ነገ ክልል መሆናችንን እናውጃለን” የኤጀቶ አስተባባሪ
ለዶ/ር ዮናስ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንጂ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ብሎ ነገር ራሱ እምብዛም ስሜት የሚሰጥ ነገር አይመስልም።
“ብሔርን ከፍ አድርገው፣ ብሔረሰብን መካከለኛ አድርገው ሕዝብን ዝቅተኛ አድርገው፤ አንዳንዴም አስደንጋጭ ቅጥያዎችን ሁሉ ጨማምረው ሕዳጣን፤ አናሳ ብሔረሰብ የሚሉ ስሞችም ይሰጣሉ፤ ሁሉም ግን ሕዝብን ለመከፋፈል የተደረጉ ናቸው” ይላሉ።
በሕገ መንግሥቱም ላይ አንድ ብሔር፣ ብሔር ስለሆነ ይህ ይገባዋል፣ ብሔረሰብ ደግሞ ስለሆነ ያ ይገባዋል የሚል የተቀመጠ ነገር የለም የሚሉት ተባባሪ ፕሮፌሰር ዮናታን፤ ሕገ መንግሥቱ መብትና ጥቅም ሲሰጥ በእነዚህ መካከል ምንም ልዩነት እንዳላስቀመጠ ያትታሉ።
ታዲያ ልዩነት ከሌለ የክልልነት ጥያቄ ገፍቶ የሚመጣው ለምንድን ነው?
የሕግ ምሁሩ ዮናታን (ዶ/ር) መልስ አላቸው፤ ክልል እንሁን የሚሉ ወገኖች ራሳቸውን ብሔር ነን ብለው ያስባሉ። ነገር ግን ሕገ መንግሥቱ ክልልነት የምታገኘው ብሔር ስለሆንክ ነው፣ ወይንም ደግሞ ብሔረሰብ ስለሆንክ ክልልነት አይገባህም የሚል ነገር የለውም።
የትኛውስ ነው አቃፊ? ብሔር ውስጥ ነው ብሔረሰቦች ያሉት? ሕዝቦችስ ብሔር ውስጥ ናቸው? ወይስ ብሔረሰቦች ውስጥ ናቸው? ለሚለው ጥያቄም ሕገ መንግሥቱ ልዩነት እንደሌለው ዮናታን (ዶ/ር) ይናገሩና “የሕገ መንግሥቱ ትልቁ ግርታ ያለው እዚያ ላይ ነው” ይላሉ።
በርግጥ ይላሉ፣ አንዳንዶቹ የመብት ጥያቄ ሲያቀርቡ ራሳቸውን ብሔር አድርገው ይወስዳሉ፤ አንዳንዶቹ ደግሞ ብሔረሰብ አድርገው ይወስዳሉ። በማለት እንደ ሲዳማ ያሉ ትላልቅ ማህበረሰቦች ራሳቸውን እንደ ብሔር አድርገው ነው የሚወስዱት፤ እንደ ስልጤ ያሉት ደግሞ ባለፈው መብታቸውን ሲጠይቁ እንዳስቀመጡት ራሳቸውን እንደ ብሔረሰብ አድርገው ነው የቆጠሩት ይላሉ።
ታዲያ በምን መስፈርት ነው እነዚህ ወገኖች አንደኛው ራሱን ብሔር ሌላኛው ብሔረሰብ ያለው? ቢባል ግልፅ ያለ ነገር የለም ባይ ናቸው የሕግ ምሁሩ።
• በሲዳማ ክልልነት ጉዳይ ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ የምርጫ ቦርድ ወሰነ
የብሔረሰቡ ሊቃውንትም ራሳቸውን በአንደኛው ሥር ያካተቱበት መስፈርት የማህበረሱ ቁጥር ይሁን ሌላ ምንም የሚታወቅ ነገር የለም። ሕገ መንግሥቱ ግን ክልል የመሆን መብትን የሚሰጠው ለሁሉም ነው ይላሉ ዶ/ር ዮናታን። ለብሔርም፣ ለብሔረሰብም፣ ለሕዝብም።
ስለዚህ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ክልል ለመሆን ቁጥር መስፈርት አይደለም።
ታዲያ ሕገመንግሥቱ ለማንኛውም አካል ክልል የመሆን ጥያቄን በዚህ መልክ አቅልሎ ከነበር እንዴት እስከዛሬ ድረስ ጥያቄዎች ሳይቀርቡ ቀሩ?
ለዶ/ር ዩናታን እስከዛሬ አልቀረቡም ብሎ በሙሉ አፍ መናገር ከባድ ነው። ምክንያቱም የሲዳማ የክልልነት ጥያቄ ከበፊት ጀምሮ የነበረ ነው ይላሉ።
እንደውም በማለት፤ የሲዳማ ዞን ምክር ቤት ተገንጥዬ የራሴን ክልል እመሰርታለሁ ብሎ ወስኖ ጥያቄ ለፌደራል መንግሥቱም አቅርቦ ነበር። ነገር ግን የፌደራል መንግሥቱ ያስገቡትን ጥያቄ እንዲተዉት እንዳደረጋቸው ያስታውሳሉ።
“ራሳቸው ያስገቡትን ጥያቄ ድጋሚ ደብዳቤ በመጻፍ ጥያቄያችንን አንስተናል። ጥያቄው በዚህ ጊዜ መቅረብ የነበረበት አልነበረም በማለት ደብዳቤ አስገብተዋል።”
ስለዚህ ከዚህ በፊት ጥያቄዎቹ ይነሱ የነበረ ቢሆንም፣ ጥያቄዎቹን ለማስተናገድና ለመመለስ ግን ፍቃደኝነት አልነበረም ሲሉ የድሮና ዘንድሮን ፖለቲካዊ ድባብ ልዩነት ያብራራሉ።
አሁን ለምን?
ለዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) በአሁኑ ሰዓት የክልልነት ጥያቄ ከተለያዩ አቅጣጫ እየተሰማ ያለው በኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ሰዓት የብሔር አክራሪነት ስለገነነ ነው።
የኢትዮጵያ አገረ መንግሥትም ይላሉ ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር)፤ መሰረቱን በብሔር ማንነት ላይ ማድረጉ የመጨረሻው ውጤት ይህ እንዲሆን አድርጎታል።
“በማንነት ላይ የተመሰረተው ፌደራሊዝም መጨረሻው ይኸው ነው። በምሥራቅ አውሮጳ የታየውም ይኸው ነው።”
ነገሩን ከፖለቲካው ምኅዳር መስፋትና መጥበብ ጋ የሚያያይዙት ተባባሪ ፕሮፌሰር ዮናታን፤ ቀደም ሲል ቡድኖቹ ጥያቄውን ለመግፋት የሚችሉበት የፖለቲካ ሁኔታ አልነበረም ይላሉ።
“ፖለቲካው ከፈትፈት ብሏል። ጠንካራ የነበረው የፓርቲው ዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት አሁን ብዙም የለም፤ ስለዚህ እነዚህ ቡድኖች ጥያቄያቸውን ማንሳት እንደሚችሉ፣ ገፍተው ቢሄዱ የሚያስፈራራቸው፣ የሚጫናቸው ኃይል ብዙም እንደሌለ ስለሚሰማቸው በአሁኑ ሰዓት ክልል እንሁን የሚል ጥያቄ ሊበራከት ችሏል” ይላሉ።

ክልል በመሆን የሚገኘው ትርፍ ምንድነው? የሚታጣውስ?
“ክልልነት ለማህበረሰቡ የተሻለ ሥልጣን ይሰጣል” ይላሉ ዶ/ር ዮናታን።
አብዛኛው ክልል የበጀት ድጎማ የሚያገኘው ከፌደራል መንግሥቱ ነው። ክልሎች ከፌደራል መንግሥቱ ያገኙትን ገንዘብ እነርሱ ደግሞ ለዞኖች ያከፋፍላሉ።
አሁን ባለው ሁኔታ ሲዳማ ክልል ስላልሆነ በቀጥታ የገንዘብ ድጋፍ አያገኝም። ክልል ሲሆን ግን ዞን ሲሆን ከሚያገኘው የተሻለና ከፌደራል መንግሥቱም በቀጥታ የገንዘብ ድጋፍ ያገኛል።
ከበጀት ባሻገርም ራስን የማስተዳደሩን ሥልጣን የመጠቀም መብቱ ከፍ ያለ ይሆናል።
የዞን ስልጣን የነበረው ወደ ክልልነት ከፍ ሲል ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣኑም አብሮ ያድጋል።
ሕገ መንግሥቱ የሚሰጣቸውን ሥልጣኖች በቀጥታ የመጠቀም፣ ፍርድ ቤቶች፣ የጸጥታና የፖሊስ ተቋማትን ማቋቋም ይቻላል።
ክልልነት ለጠየቀው ሁሉ ቢታደል ምንድነው ችግሩ?
ዶ/ር ዮናታን ነገር ግን ክልልነት ማደል ከጀመርን ጥያቄው መቆሚያ አይኖረውም ሲሉ ፍርሀታቸውን ይገልፃሉ።
ኢትዮጵያ ከሰማኒያ በላይ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ያሉባት ሀገር ናት የሚሉት ምሁራኑ፤ የክልልነት ጥያቄ ላነሳው ሁሉ የፌደራል መንግሥት እያነሳ ቢሰጥ ክልል ለመሆን ኢኮኖሚያዊ ብቃት የሌላቸው ቦታዎች ክልል እንዲሆኑ ማድረግ ይሆናል ይላሉ።
ይህ ደግሞ ክልል ቢሆኑ እንኳ ሙሉ በሙሉ በፌደራል መንግሥት ድጋፍ ላይ የሚንጠለጠሉ አካባቢዎችን ይፈጥራል።
ስለዚህ ካሉን ከ80 በላይ ብሔረሰቦች፣ ብሔሮችና ሕዝቦች መካከል በፖለቲካ፣ በምጣኔ ሀብት፣ በሰው ኃይልም ለክልልነት ብቁ የማይሆኑ እንዳሉ ግልፅ ነው።
• ኢህአዴግ ከአባል ፓርቲዎቹ መግለጫ በኋላ ወዴት ያመራል?
ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ሕገ መንግሥታዊ ነው ያሉት ዶ/ር ዮናታን፤ ያ መብት ግን በተለያየ መልኩ ወደ ሥራ ሊገባ ይችላል ሲሉ ያስረዳሉ።
ክልል በመሆን ራስን በራስ የማስተዳደር ሕገ መንግሥታዊ መብት ማረጋገጥ ይቻላል። ነገር ግን ያ ብቸኛ መንገድ አይደለም። ከክልል በታች ዝቅ ያሉ ዞንም ሆኑ ወረዳዎች ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ተደርጎ ሊተረጎም ይችላል ሲሉ ይናገራሉ።
“ስለዚህ ሰማኒያ ብሔር ባለበት አገር ሁሉም ክልል ይሆናል ብሎ ማለት አስቸጋሪ ነው። ያ እንዳይሆን ግን የሚያግድ ሕጋዊ መሰረት የለም።”
አሁን ባለውም ሕገ መንግሥት ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የመሆን መብት አላቸው ሲሉ ይደመድማሉ ዶ/ር ዮናታን። ሌላ የተቀመጠ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ፣ የጂኦግራፊ መስፈርት ወይንም ቅድመ ሁኔታ የለም።
መብት አለ፤ ግዴታ የለም
ሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 47 የክልልነት ጥያቄ ለሚያነሱ መብት ይሰጣል። ይህንንም ይዘረዝራል፤ ነገር ግን የፌደራል መንግሥቱም ሆኑ፣ ክልሉ ይህንን ጥያቄ መቀበል አለባቸው ብሎ አያስቀምጥም። ስለዚህ እዚህኛው አንቀጽ ላይ መብት አለ፤ መብቱ ግን የተቀመጠው ሌሎቹ መቀበል አለባቸው ከሚል ግዴታ ጋር እንዳልሆነ ያስረዳሉ።
ሁለተኛ ነጥብ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ባደረጉት ንግግር ላይ የጠቀሱት የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ሐሳብ ነው።
በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 47፣3 መሠረት ክልሎች የክልልነት ጥያቄ አቅርበው ተቀባይነት እንዳገኙና ሕዝበ ውሳኔው በአብላጫ ድምፅ ከተጠናቀቀ ወዲያውኑ የፌደሬሽኑ አካል ይሆናሉ።
ነገር ግን እዛው አንቀፅ ላይ 47፣1 በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን ክልሎች በአጠቃላይ ይዘረዝራል። እነዚህ ክልሎች ዘጠኝ ሲሆኑ አዲስ የሚመጣ ክልል እዚህ ዝርዝር ውስጥ የግድ መግባት አለበት። እዚያ ውስጥ ለመግባት ደግሞ አንቀፁ መሻሻል ወይንም መቀየር አለበት ይላሉ የሕግ ምሁሩ።
• “የመከላከያው በአደባባይ ሚዲዎችን እከሳለሁ ማለት አስፈሪ ነው” ዶ/ር አብዲሳ ዘርዓይ
ዶ/ር ዮናስ አዳዬ በበኩላቸውም ሕገ መንግሥቱን ሳያሻሽሉ አዳዲስ ክልል መመስረት ያለውን ጦስ ያስረዳሉ። በቅድሚያ ሕገ መንግሥቱ ላይ የተቀመጡት ዘጠኝ ክልሎች ጉዳይ መሻሻል አለበት ሲሉም ይመክራል።
አዲስ የሚመጡ ክልሎች ከሌሎቹ እኩል ሆነው የፌደራል መንግሥቱን ሥልጣን እንዲካፈሉ ራሳቸውን እንዲያስተዳድሩ ደግሞ የሕገ መንግሥት እውቅና እንዲኖራቸው ይገባል የሚሉት ዮናታን (ዶ/ር) ያ እንዲሆን ደግሞ አንቀፅ 47፣1 መሻሻል አለበት።
የሕገ መንግስት ማሻሻያ ለማድረግ ደግሞ የራሱ ሂደት አለው። ሕገ መንግሥት እንዲቀየር የክልሎቹን ሁለት ሦስተኛ ድጋፍ ማግኘት፣ የፌደሬሽን ምክር ቤትና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ድምፅ መስጠትና መደገፍ አለባቸው።
ስለዚህ ይህ ክልል ሙሉ በሙሉ ክልል ተብሎ ሕገ መንግሥታዊ እውቅና እንዲሰጠው ሕገ መንግሥቱ መቀየር አለበት ማለት ነው። ሕገ መንግሥቱ እንዲቀየር ደግሞ የሌሎቹ ድጋፍ ያስፈልጋል።
በሁለቱ ምሁራን አመለካከት ይህ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ሂደት ግምት ውስጥ ሲገባ አሁን ባለው ሁኔታ ጥያቄ ስለቀረበና ድጋፍ ስለተገኘ ብቻ ክልል መሆን ይቻላል ብሎ መደምደም አስቸጋሪ ይሆናል።
የሲዳማ ክልልነት ጥያቄ ሲፀድቅ የሌሎቹስ?
በሕጉ መሰረት ካየን፤ የሲዳማ ዞን ማሟላት ያለበትን አሟልቶ ሕዝበ ውሳኔ (ሪፈረንደም) ተካሂዶ የሚያስፈልገው ድምፅ ቢገኝም እንኳ ሕገ መንግሥቱ እስካልተሻሻለ እና ሲዳማ አንዱ ክልል መሆኑ ሕገ መንግሥቱ ላይ እስካልሰፈረ ድረስ ክልል ነው ማለት ያስቸግራል ይላሉ ዮናታን (ዶ/ር)።
ከዚያ በፊት ያለውን ሂደት ማቆም አይቻልም የሚሉት ዶ/ሩ፤ ለዚህ ነው የራሳቸውን ክልል እንዲኖራቸው በሚጠይቁት የሲዳማ ማህበረሰብ ተወካዮች መካከል፣ በፌደራል መንግስቱና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል መካከል ውይይት የሚያስፈልገው ይላሉ።
• “ኢትዮጵያዊነቴን ያገኘሁት ሙዚቃ ውስጥ ነው” አቨቫ ደሴ
ውይይቱ አሁን የክልልነት ጥያቄ ተነስቶ ሙሉ ድጋፍ ካገኘ በዲሞክራሲያዊ፣ መንገድ የቀረበውን እና የተገለጠውን ሀሳብ ማክበር ያስፈልጋል። ነገር ግን ሌሎች ከሲዳማ ክልል መሆን ጋር የሚያያዙ ጥያቄዎች ካሉ እነርሱን በተመለከተ፣ በተለይ ደግሞ የሌሎቹን ሁኔታ ግምት ውስጥ ያስገባ ፣ የአገሪቱን ሁኔታ ጥቅምና ጉዳት ግምት ውስጥ ያስገባ ውይይት ተደርጎ፣ ማመቻመች እና ስምምነት ላይ መድረስ አለበት ሲሉ ይመክራሉ።
የሲዳማ ማህበረሰብ ተወካዮችም ከክልሉ እና ከፌደራል መንግሥቱ የሚመጡ ስጋቶችን መጋራትና ለድርድር ዝግጁና ክፍት መሆን አለባቸው ሲሉም ይመክራሉ።
ከአንድ ክልል ጋር አብሮ በሚኖርበት ጊዜ የሚያገገናኝ ብዙ ነገር እንዳለ ሁሉ ሲለያዩም የሚያነጋግር ነገር ይኖራሉ በማለት ሲዳማ ውስጥ ስላሉ የሀብት ክፍፍሎች፣ ሲዳማ ውስጥ ስለሚኖሩ ሌሎች ማህበረሰቦች፣ ስለ ሲዳማ ክልል ድንበር፣ ውይይት ብቻ ሳይሆን ስምምነትም ላይ ሊደረስባቸው ይገባል ሲሉ ያስቀምጣሉ።
ቀጣይ ፈተናዎች ምንድናው?
የሕግ ምሁሩ ዮናታን (ዶ/ር) ክልል የመሆን ጥያቄ እና የሚሰጡ መልሶች ሌሎች ተመሳሳይ ጥያቄዎች እንዲነሱ በሩን ወለል አድርጎ እንዳይከፍተው ስጋት አላቸው።
የሚነሱ ቀጣይ ጥያቄዎች ቀጣይ የመሆን እድላቸው ሰፊ ነው የሚሉት ዶ/ር ዮናታን፤ እነዛን ጥያቄዎች እንዴት መፍታት ይቻላል? የሚለው መታየት አለበት ሲሉ ይመክራሉ።
“የሲዳማን ጉዳይ የምንመልስበበት መንገድ የሌሎችን ጥያቄዎችን የምናስተናግድበትን መንገድ ይበይናል” በማለትም የሌሎቸንም አገራት ልምድ ማየት መልካም መሆኑን ይመክራሉ።
• “ኢስላማዊ ባንክ ለኢትዮጵያ ምን ይፈይዳል?”
“ሕንድ እንዲህ ዓይነት በርካታ ጥያቄዎች አስተናግዳ ታውቃለች። ነገር ግን ሕንድ ማዕከላዊ መንግሥቱ ነው ለጥያቄው መብት መስጠትየሚችለው” በማለት በሕንድ በዚህ መንገድ ከአንድ ክልል ብቻ ስድስት አዳዲስ ክልሎች መፈጠራቸውን በመጥቀስ ከሌሎች አገራት ልምድ መቅሰም አስፈላጊነቱን ያሰምሩበታል።