መቀሌ ከፈረሱት ቤቶች መካከል አንዳንዶቹ

በመቀሌ ዙርያ የእንደርታ ወረዳ አስተዳደር ከ400 በላይ “ሕገ-ወጥ ናቸው” ያላቸውን ቤቶች ‘በዶዘር በመታገዝ’ ማፍረሱን የአካባቢው ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገለጹ።

በተያያዘ ዜና በምሥራቅ ሸዋ፤ አዳማና ሞጆ አካባቢዎች ‘በሕገ-ወጥ መሬት ወረራ የተገነቡ’ የተባሉ ከ2000 በላይ ቤቶች መፍረሳቸውን የአካበቢው ነዋሪዎች ለቢቢሲ ኦሮምኛ ክፍል ተናግረዋል።

በትግራይ ክልል በእንደርታ ወረዳ አስተዳደር ሥር የሚገኘው ‘ማሕበረ ገነት’ ቀበሌ አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ ጥዑማይ ፍጹም ጉዳዩን አስመልክተው ሲናገሩ “ከ4-10 የቤተሰብ አባሎች የሚኖሩባቸውና ከ1990 ዓ.ም ጀምረው ያስተዳደሩዋቸው ቤቶች ጨምሮ ህጋዊና ሕገ-ወጥ ቤት ሳይለይ ከ420 በላይ ቤቶች እንዲፈርሱ ተደርጓል” ይላሉ።

የጦር መሳሪያዎቹ ምንጫቸው የት ነው?

እሳቸው እንዳሉት ስለቤቶቹ መፍረስ የተሰጠ ቅድመ ማስጠንቀቂያ አልነበረም። ከክስተቱ በኋላ በድርጊቱ የተቆጡ ነዋሪዎች ወደ ርዕሰ-መስተዳድሩ ቢሮ በመሄድ ተቃውሟቸውን እንደገለጹ አቶ ጥዑማይ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

የእንደርታ አካባቢ ነዋሪዎች እንዳሉት ከሆነ የወረዳው አስተዳደር በልዩ ኃይል እና በፖሊስ ታጅቦ ነው እርምጃውን የወሰደው። ክለውም “ሁኔታውን የተቃወሙ እና ፎቶ ያነሱ” ሰዎች መታሰራቸውም ነዋሪዎቹ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ ቤታቸው የፈረሰባቸው የእንደርታ ከተማ አንድ ነዋሪ “ከሃያ ዓመት በፊትም ሆነ በቅርቡ የተሰሩ ቤቶች በአንድ ላይ ፈርሰዋል” ሲሉ ተናግረዋል።

“ስለጉዳዩ መረጃ እስክናቀርብ እንኳ ግዜ አልተሰጠንም። ይፈርሳል አይፈርስም ስለሚለውም አናውቅም ነበር። ማታ ‘ዶዘር’ ይዘው መጥተው እቃዎቻችንን አውጡ አሉን” ይላሉ።

ቤታቸው ከፈረሰባቸው አንዳንዶቹ ‘አውላላ ሜዳ ላይ’ ድንኳን ሰርተው ተጠልለው እንደሚገኙም ነዋሪዎች ተናግረዋል።

ሕገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር መበራከት ምንን ያመለክታል?

“ከአማራ ክልል ተፈናቅለው የመጡ አንዳንድ ሰዎች እዚህ መሬት ገዝተው ነበረ። አሁን ተመልሰው ለችግር ተዳርገዋል” ሲሉም ለቢቢሲ ገልጸዋል። ሌሎች ነዋሪዎችም “ከነ ሙሉ ንብረታቸው ቤታቸው የፈረሰባቸው አሉ” ይላሉ።

የትግራይ ክልልም ሆነ የወረዳው አስተዳደር ጉዳዩን በተመለከተ የሰጠው መግለጫ የለም።

በምሥራቅ ሸዋ ዞን የመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ክፍል ምክትል ኃላፊ የሆኑት አቶ ሙባረክ ዑስማን፤ በዞኑ ውስጥ ሕገ-ወጥ የመሬት ወረራ የተስፋፋ ሲሆን ሕገ-ወጥ ቤቶችን በተመለከተ የወጣውን ደንብ ቁጥር 182 ተከትሎ ከ2005 ዓ.ም ወዲህ የተሰሩ 5000 ያህል ቤቶች አንደሚፈርሱ ለቢቢሲ አስታውቀዋል።

የትግራይ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል [ዶ/ር] መንግሥታቸው የሕገወጥ ቤቶች ግንባታ ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ እንደሚወስድ ቀደም ሲል ገልጸው ነበር።

በመሬት ወረራ እና ሕገ-ወጥ የቤቶች ግንባታ ላይ የተሰማሩ ሰዎችም ከተግባራችው እንዲታቀቡ አስጠንቅቀው ነበር።

መፈናቀል፡ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የአንድ ዓመት ፈተናዎች አንዱ