
Sean Gallup
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምርጫን ማካሄድ የሚያስችል ሁኔታ ባለመኖሩ የከተማ አስተዳደሩ የምርጫ ጊዜ እንዲራዘም መወሰኑ ይታወሳል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ቻርተርን ባሻሸለበት አዋጅ የከተማው ምክር ቤትን ምርጫ ከማራዘሙ በተጨማሪ፤ ምርጫ ተደርጐ አዲስ አስተዳደር እስኪደራጅ ድረስ በሥራ ላይ ያለው ምክር ቤትና አጠቃላይ የከተማው የአስተዳደር በነበረበት ሁኔታ ይቀጥላል ብሏል።
የምክር ቤቱ ውሳኔዎች ሕጋዊ አግባብነት የላቸውም የሚሉ ጥያቄዎችና ቅሬታዎች ተነስተዋል። ምክር ቤቱም ሆነ አጠቃላይ የከተማ አስተዳደሩ ሕጋዊ እውቅና ኖሮት ከተማዋን ሊያስተዳድር አይችልም የሚሉ አካላትም አሉ።
• ”አዲስ አበባ የሁላችንም ከተማ ናት” ከንቲባ ታከለ ኡማ
ከእነዚህም መካከል በአዲስ አበባ ከተማ የባላደራ ምክር ቤት የሥራ አስፈጻሚ አባል እና በሙያቸው ጠበቃ የሆኑት አቶ ሄኖክ አክሊሉ ይገኙበታል። አቶ ሄኖክ በቅድሚያ ባላደራ ምክር ቤትን ማቋቋም ካስፈለገባቸው ምክንያቶች መካከል አንዱ ”ገፊ የሆኑ ወቅታዊ ሁኔታዎች ይገኙበታል” ይላሉ።
አቶ ሄኖክ ለባላደራ ምክር ቤት መቋቋም ወቅታዊ ጉዳዮች ናቸው የሚሏቸው ”አሁን ያለው አስተዳደር ወደ ሰልጣን ከመጣ ወዲህ የከተማውን ነዋሪ ባገለለ ሁኔታ የጥቂት ሰዎች ፍላጎት ለማሳካት እንቀስቃሴዎችን ያደርጋል፣ እስከታችኛው የስልጣን እርከን ድረስ የእራሱን አመለካከት የሚያራምዱ ሰዎችን ብቻ ወደ ስልጣን ያመጣል . . . ” የሚሉ ምክንያቶች እና ”ከተማዋን እያስተዳደረ ያለው አካል ሕጋዊ እውቅና የለውም” የሚሉ ምክንያቶች ለባልደራስ ምክር ቤት መፈጠር ምክንያት እንደሆነ ያስረዳሉ።
የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት እና አስተዳደር ”ሕጋዊ እውቅና የለውም”
የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 49 ንዑስ አንቀጽ 2 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሙሉ ሥልጣን ይኖረዋል የሚለውን አንቀጽና የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር ቻርተር አዋጅ ቁጥር 365/1995 በማስታወስ አሁን ላይ ያለው አስተዳደር የተቀመጠለትን የሕግ ማዕቀፍ መሰረት ያላደረገ ነው በማለት አቶ ሄኖክ ይከራከራሉ።
”አዲስ አበባ ላይ የሚመረጥ መንግሥት አምስት ዓመት የሥራ ዘመን እንዳለው በግልጽ ተቀምጧል። የከተማው ሥራ አስፈጻሚ አካል፤ የከንቲባ ጽ/ቤትን ጨምሮ የሥራ ዘመኑ አምስት ዓመት ነው። አምስት ዓመት ደግሞ አልፎታል። የሥራ ዘመኑ ካለፈ መፍትሄ የሚሆነው ምርጫ ማካሄድ ነው። ምርጫ ማካሄድ የማይቻል ከሆነ ህብረተሰቡ የእኔ ናቸው የሚላቸውንና የሚያከብራቸውን ወደ ስልጣን ማምጣት ነው” በማለት አቶ ሄኖክ ይናገራሉ።
የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ወ/ሮ አበበች ነጋሽ በበኩላቸው ”የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤትና የከተማው አስተዳደር የሥልጣን ዘመን አብቅቷል የሚባለው በአንዳንድ በሰዎች ፍላጎት እንዲስፋፋ የሚደረግ የተሳሳተ መረጃ ነው” ይላሉ።
• «አዲስ አበባ የሁሉም ናት» አርበኞች ግንቦት 7
ወ/ሮ አበበች የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ቻርተር አዋጅ ቁጥር 365/1995ን ማሻሻል በማስፈለጉ ከአንድ ዓመት በፊት በአዋጅ ቁጥር 1094/2010 እንደተሻሻለ ያስታውሳሉ።
”በአዲስ አበባ ከተማ ምርጫ እንዲራዘም መወሰኑን ተከትሎ፤ ምርጫ ተደርጐ በምርጫው መሠረት አዲስ አስተዳደር እስኪደራጅ ድረስ በሥራ ላይ ያለው ምክር ቤት እና አጠቃላይ የከተማው የአስተዳደር በነበረበት ሁኔታ ይቀጥላል ሲል አውጇል” በማለት በአዋጅ ቁጥር 1094/2010ን በመጥቀስ ወ/ሮ አበበች ያስረዳሉ።
የተሻሻለው የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ቻርተር አዋጅ ቁጥር 1094/2010 የከተማ አስተዳደሩና ምክር ቤት በሥራ ላይ የሚቆይበትን ቀነ ገደብ እንዳለስቀመጠ የሚናገሩት ወ/ሮ አበበች፤ የማሻሻያ አዋጁ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ከምክር ቤት አባል ውጭ እንዲሾም የሚፈቅድ ስለመሆኑም ይናገራሉ።

አከራካሪው አዋጅ ቁጥር 1094/2010
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአዲስ አበባ ከተማ ምርጫን ላልተወሰነ ጊዜ ያራዘመውና የአዲስ አበባ ምክር ቤትም ባለበት እንዲቀጥል የወሰነው የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ቻርተር አዋጅ ቁጥር 365/1995ን በአዋጅ ቁጥር 1094/2010 በማሻሻል ነው።
አቶ ሄኖክ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአዲስ አበባን ምክር ቤት የሥራ ዘመን የማራዘም መብት የለውም በማለት ይከራከራሉ። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ አስተዳደሩን የሥራ ዘመን የማራዘም መብት ሳይኖረው በዚህ አዋጅ አማካኝነት የከተማ አስተዳደሩን የሥራ ዘመን እንዲራዘም መደረጉ አሁን ያለው የከተማው አስተዳደርና ምክር ቤት የሕግ አግባብነት እንደሌለው ይናገራሉ።
ሕገ መንግሥቱ ላይ አንቀጽ 49.2 ከተማ አስተዳደሩ ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሙሉ ሥልጣን ይኖረዋል ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል ይላል እንጂ፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአዲሰ አበባ ምክር ቤት የሥራ ዘመንን ያራዝማል በሚል የተጠቀሰ ቦታ የለም ይላሉ አቶ ሄኖክ።
”ከፖለቲካ አንጻር ብንመለከተው እንኳን ያለንበት ነባራዊ ሁኔታ ምርጫ እንዲካሄድ የማይፈቅድ ከሆነና ለአንድ ዓመት እንኳ አሸጋጋሪ መንግሥቱን እንቀበለው ብንል፤ ወደ ስልጣን የሚመጣው መንግሥት የከተማው ህዝብ ካለው ራሱን የማስተዳደር መብትና ከሕገ መንግሥቱ ጋር በተጣጣመ መንገድ መሆን ይኖርበታል። ይሁን እንጂ ይህን ከግምት ውስጥ ያላስገባ በመንግሥት የተሰየመበት ሁኔታ የበለጠ ቀውስና ችግር የሚፈጥር ሆኖ አግኝተነዋል” ይላሉ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤትን የሥራ ዘመን ማራዘም አይችልም፤ አዋጅ ቁጥር 1094/2010 ሕጋዊ አግባብነት የለውም በሚለው ላይ ምላሻቸውን እንዲሰጡ የተጠየቁት የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወ/ሮ አበበች ነጋሽ ”የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዋጅ ቁጥር 1094/2010 ማጽደቅ አይችልም ከተባለ፤ እሱ ላይ አስተያየት መስጠት አልችልም። እኛ ግን አዋጁን በሕጋዊ መንገድ ተግባራዊ እያደረግን ነው” ብለዋል።
አቶ ኤፍሬም ታምራት የሕግ ባለሙያ ሲሆኑ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ ምክር ቤቱን የሥራ ዘመን ማራዘም እንደሚችል አስረግጠው ይናገራሉ።
አቶ ኤፍሬም ሃሳባቸውን ሲያስረዱ ”በሕገ መንግሥቱ ላይ አንቀጽ 49 ስር የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተጠሪነቱ ለፌደራሉ መንግሥት መሆኑና የከተማ አስተዳደሩ ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ይህን ለመደንገግ ዝርዝር ሕግ ይወጣል ይላል። ዝርዝር ሕግ ተብሎ ከተጠቀሰው መካከል አንዱ ቻርተሩ ነው። በቻርተሩ ላይ ደግሞ በግልጽ የፌደራሉ መንግሥት በራሱ አነሳሽነት ቻርተሩን ሊያሻሽለው እንደሚችል ተገልጿል።”
የከተማ መስተዳደር ቻርተር አዋጅ ቁጥር 365/1995 ያወጣው የፌደራል መንግሥቱ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኩል ነው። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፌደራል መንግሥቱ አንደኛ አካል ነው ይላሉ አቶ ኤፍሬም።
አክለውም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተጠሪነቱ ለፌደራል መንግሥቱ ነው ሲባል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን ይመለከታል። የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ስልጣን የተቀዳለት ከፌደራል መንግሥቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው። ምክር ቤቱ የከተማ አስተዳደሩን የሥራ ዘመን ሊያራዝም እንደሚችልም ይጠቅሳሉ።

የአዲስ አበባ ከተማ ምርጫ መቼ ይካሄዳል?
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባለው ነባራዊ ሁኔታ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ምርጫን ማካሄድ አይቻልም በማለት ምርጫው በ2011 ዓ.ም ላይ እንዲካሄድ ማራዘሙ ይታወቃል። በውሳኔው መሰረትም ዓመቱ ሳይጠናቀቅ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫውን ሊያከናውን እንደሚችል ሲጠበቅ ነበር። ይሁን እንጂ ምርጫ ቦርድ በተቀመጠው ቀነ ገደብ ምርጫ ማካሄድ እንደማይችል አስታውቋል።
የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሕዝብ ግነኙነት ኃላፊ ወ/ሪ ሶሊያና ሽመልስ፤ ምርጫ ቦርድ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደታሰበው ምርጫውን ማካሄድ እንደማይችል ጠቅሶ ምክር ቤቱ ውሳኔ እንዲሰጥበት በደብዳቤ አሳውቋል ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ምርጫ ቦርድ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጻፈው ደብዳቤ፤ ”የአዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተማ ምክር ቤቶች ምርጫን ጨምሮ የአካባቢ ምርጫን ለማከናወን የሚያስፈልጉ የምርጫ አስፈጻሚዎች ምልመላና ስልጠና ለመስጠት፣ ተቋማዊ የለውጥ ሥራዎችን በየክልሉ በተዋረድ አጠናቆ ለማስፈጸም ጊዜ አለመኖሩንና ዓመቱ እየተጠናቀቀ በመምጣቱ ምክር ቤቱ ውሳኔ እንዲሰጥበት ደብዳቤ ተልኳል” ሲሉ ተናግረዋል።
የባላደራ ሚና እስከ ምን ድረስ ነው?
የአዲስ አበባ ሕዝብ የመረጠው መንግሥት ወደ ስልጣን ቢመጣ የባልደራሱ ሚና ምን ሊሆን እንደሚችል የባልደራስ የሥራ አስፈጻሚ አባል የሆኑት አቶ ሄኖክ አክሊሉ ሲናገሩ ”ከሕዝብ የተሰጠ ሁለት አደራ አለ” የሚሉት አቶ ሄኖክ “የመጀመሪያው ዜጎችን በእኩል ዓይን የማይመለከት አስተዳደርን መታገል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ‘የአዲስ አበባና ኦሮሚያ ድንበር በተመለከተ ሁለቱ አካላት የሚደራደሩበትን ሁኔታ እንድንመለከ ህዝብ የሰጠን አደራ አለ” ይላሉ።
የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ወሰን አለመግባባት የተፈጠረበት ነው የሚሉት አቶ ሄኖክ ”በጠቅላይ ሚንስትሩ በተቋቋመው ኮሚሽን የድንሩን ለማካለል በአዲስ አበባ በኩል በምክትል ከንቲባው በኦሮሚያ በኩል ደግሞ በፕሬዝደንቱ የሚመራ ቡድን እንደተሰየመ ይታወሳል። ሁለቱም ተደራዳሪዎች ተመሳሳይ ፍላጎት ስላላቸው እና የአዲስ አበባን ጥቅም የሚወክል ስለሌለ የከተማዋን ጥቅም እናስከብራለን” ይላሉ።
ይህም የከተማው ሕዝብ የሚመርጣቸው ተወካዮቹ የነዋሪውን መብትና ጥቅም በሚያስከብሩበት ሁኔታ እስከሚመረጡ ድረስ ጥኣቄዎቹን በማንሳት ተቀበልናቸው የሚሉትን አደራዎች ለማስፈጸም እንደሚሰሩ ይናገራሉ።
በአሁኑ ወቅት ያለው የከተማዋ መስተዳደር የስልጣን ዘመኑ ማብቃትና “ከሕግ ውጪ” ተሾሙ የተባሉት ከንቲባ ጉዳይ እስካሁን እያነጋገረ ቢሆንም፤ አሁንም ምርጫ ለማካሄድና የተመረጠ አስተዳደር ለማቋቋም አመቺ ሁኔታዎች እንደሌሉ እየተገለጸ ነው።
ለዚህ ደግሞ በቀጣይ ዓመት ይደረጋል ተብሎ የሚታሰበውን አጠቃላይ ሃገራዊ ምርጫ መጠበቅ የግድ ሳይሆን አይቀርም። ይህ ደግሞ የ1997ቱን ምርጫ ተከትሎ ከቀሪው የሃገሪቱ ክፍሎች ምርጫ ተነጥሎ ለብቻው ሲካሄድ የነበረውን የአዲስ አበባ ምርጫ ወደነበረበት እንዲመለስ ያደርገዋል ተብሎ ይጠበቃል።