19 ጁላይ 2019

የሲዳማ ኔትወርክ አርማ

በትናንትናው ዕለት አመሻሽ ላይ የሲዳማ ሚድያ ኔትወርክ ዋና ሥራ አስኪያጅና ምክትል ሥራ አስኪያጅ ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር ስብሰባ ተቀምጠው በነበረበት ሰዓት የፀጥታ ኃይሎች ደርሰው በቁጥጥር ሥር እንዳዋሏቸው የኔትወርኩ የዜናና ፕሮግራሞች አስተባባሪ አቶ ሙሉቀን ብርሀኑ ለቢቢሲ ተናገሩ።

ዋና ሥራ አስኪያጁ አቶ ጌታሁን ደጉዬ እና ምክትላቸው አቶ ታሪኩ ለማ የሚባሉ ሲሆን ሌሎች የመገናኛ ብዙሀኑ ባልደረቦች ግን ወደ ቢሯቸው እንዳይገቡ መከልከላቸውን ገልፀዋል።

ትናንት ጠዋት ወደ 6 ሰዓት አካባቢ ወደ ቢሯቸው የፀጥታ አካላት መምጣታቸውን እና ጥበቃ ሰራተኞቹ የቢሮውን ቁልፍ እንዲሰጧቸው መጠየቃቸውን ያስታወሱት አስተባባሪው፤ ነገር ግን የጥበቃ ሰራተኞቹ ቁልፍ እንደሌላቸው በመግለፅ እንዳሰናበቷቸው ተናግረዋል።

ከሐዋሳ ተነስቶ በሌሎች አካባቢዎች ጉዳት ያደረሰው ሁከት

“አሁንም እያጣራን ማሰሩም፤ መፍታቱም ይቀጥላል” ኮሚሽነር አበረ

ማታ ወደ 4 ሰዓት የሲዳማ ዞን ከፍተኛ አመራሮች፣ ሽማግሌዎችና፣ ኤጀቶዎች በታቦር መካነ ኢየሱስ ቤተክርስቲያን ውስጥ የምርጫ ቦርድን ሃሳብ ለመቀበል በንግግር ላይ ባሉበት ወቅት የፀጥታ ኃይሎች ደርሰው በቁጥጥር ስር እንዳዋሏቸው ተናግረዋል።

እነዚህ ኃላፊዎች ከወጣቶቹ ጋር የተሰበሰቡት ኤጀቶ ውስጥ በነበሯቸው ተሳትፎ ምክንያት እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።

የአዲስ አበባ መስተዳደርና የባላደራው ምክር ቤት

ሲዳማ ሚዲያ ኔትወርክ ሕጋዊ እውቅና አግኝቶ ሥራ የጀመረው ባለፈው ሰኔ ወር ላይ ሲሆን እስካሁን የሚገኘው የሙከራ ስርጭት ላይ ነው።

የሚዲያ ተቋሙ ፕሮግራሞቹን የሚያስተላልፈው ሐዋሳ ከሚገኘው ቢሮውና ደቡብ አፍሪካ ጆሀንስበርግ ውስጥ ከሚገኘው ማሰራጫው እንደሆነ አስተባባሪው ተናግረዋል።

በአሁን ሰዓትም ምንም ዓይነት ስርጭት ከሐዋሳ የማይተላለፍ ሲሆን ነገር ግን ከጆሀንስበርግ የሚተላለፉ ዝግጅቶች ብቻ በቴሌቪዥን ፕሮግራሙ ላይ እንደሚታዩ ተናግረዋል።

በቁጥጥር ስር ውለዋል ስለተባሉት ግለሰቦች የእስር ምክንያትና ስላሉበት ሁኔታ ለመጠየቅ ይመለከታቸዋል የተባሉ የደቡብ ክልልና የሐዋሳ ከተማ ባለስልጣናትን ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

ሲዳማ ሚዲያ ኔትወርክ በሲዳማ ተወላጅ ዳያስፖራዎችና ባለሀብቶች የተቋቋመ ቴሌቪዥን ሲሆን ድርጅቱ ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች ጨምሮ አርባ አንድ ሰራተኞች እንዳሉት ተገልጿል።