ብ/ጄ ተፈራ ማሞና ኮሎ. አለበል አማረ
አጭር የምስል መግለጫ ብ/ጄ ተፈራ ማሞና ኮሎ. አለበል አማረ

ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም በአማራ ክልል ተሞከረ ከተባለው ‘መፈንቅለ መንግሥት’ ጋር በተያያዘ የፀጥታ ዘርፍ ኃላፊዎችን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተካሄደ እንደሆነ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አስታወቁ።

የብ/ጄነራል አሳምነው ፅጌ ሚስት መታሰራቸውን ልጃቸው ገለጸች

“የኢህአፓና መኢሶን ነገር አማራ ክልል ላይ ሊከሰት ይችላል ብዬ ነበር”

ከእነዚህ ተጠርጣሪዎች መካከል የክልሉ የፀጥታ ዘርፍ ኃላፊዎች የነበሩትን ብርጋዲየር ጀኔራል ተፈራ ማሞ፣ ኮሎኔል አለበል አማረ፣ ኮሎኔል ባምላኩ፣ ኮሎኔል አለባቸውና እና ሻለቃ እሸቱ ይገኙበታል።

ሰኔ 16 ቀን 2011 ዓ.ም አንስቶ በእስር ላይ የሚገኙት ተጠርጣሪዎቹ ከሦስት ቀናት ፊት ጀምሮ ‘ፍትህ እንሻለን’ በማለት የርሃብ አድማ ላይ መቆታቸውን ቤተሰቦቻቸው ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

በእስር ላይ ከዋሉ ጀምሮ በየቀኑ የምትጠይቃቸውና ጉዳያቸውን በቅርበት የምትከታተለው የብርጋዲየር ጀኔራል ተፈራ ማሞ ቤተሰብ መነን ኃይለ ማሪያም ‘ፍትህ የለም፤ ምንም ባላደረግነው ነገር ነው የታሰርነው፤ እኛም ታግተን እንደነበር እየታወቀ ያለምንም ምክንያት እንንገላታለን’ በሚል የርሃብ አድማውን እንዳደረጉ ትናገራለች።

ለሦስት ቀናት የርሃብ አድማ ላይ የነበሩት ተጠርጣሪዎቹ በትናንትናው እለት የኃይማኖት አባቶች ሄደው ስለገዘቷቸው ትናንት ከቀኑ ስድስት ሰዓት ጀምሮ ምግብ መቅመስ መጀመራቸውን መነን ገልጻለች።

ከዚህ ቀደም ተቀራርቦ መነጋገር እንደማይቻል የምታስታውሰው መነን የምንግባባው በርቀት በእጅ ምልክት ብቻ ስለነበር ፍላጎታቸውን ቀርበው ለመረዳት አለመቻላቸውን ታስረዳለች።

አብን ከ100 በላይ አባላቶቼ ታስረዋል አለ

ክስተቱ ከተፈጠረ በኋላ ተጠርጣሪ ግለሰቦቹ ወደ ፌደራል ሊወሰዱ የነበረ ሲሆን ክልሉ እንዳስቀራቸውና ጉዳዩ በክልሉ እንዲታይ ማድረጉን እንደምታውቅም አክላለች።

በተጨማሪም “ከዚህ በፊት በነበረው የፍርድ ቤት ቀጠሮ ክሳቸው ምን እንደሆነ አይነገራቸውም፤ ዝም ብለን ገብተን ነበር የምንወጣው፤ ገና ትናንት ነው ጠበቃ ማናገር ትችላላችሁ ተብለው ጠበቃ ወስደን ያነጋገርናቸው” ትላለች።

እርሷ እንደምትለው ብርጋዴር ጀኔራል ተፈራ ማሞ በኢትዮ – ኤርትራ ጦርነት ወቅት በጥይት ተመትተው እግራቸው ላይ ያልወጣ ስምንት ጥይት በመኖሩ አሁን ያሉበት ሁኔታ ሕመማቸውን አባብሶታል።

“ከዚህ ቀደምም ጥይቶቹን አስወጣለሁ እያለ ባለበት ሰዓት ነበር ዘጠኝ ዓመታት የታሰረው፤ አሁንም ይሄው በዚህ ሁኔታ ነው የሚገኘው” በማለት ሌሎቹም እንዲሁ የተለያየ የጤና እክል እንዳጋጠማቸው ተናግራለች።

ለሕይወታቸው ዋስትና ወስዶ የሚያክማቸው አካል ማነው? የሚለውም ስጋት እንደሆነባቸው አልደበቀችም።

መነን አክላም በማህበራዊ ሚዲያ ከነ ጀኔራል ተፈራ ማሞ የተላለፈ መልዕክት ተብሎ የሚሰራጨው ሀሰት መሆኑንና ይህን መልዕክት ለመለዋወጥ ምንም ዓይነት እድል እንዳልነበር ገልጻለች።

የኮሎኔል አለበል ልጅ ናትናኤል በበኩሉ እስከዛሬ ድረስ ቀርቦ መነጋገር ባይቻልም ከትናንት ጀምሮ ከቤተሰብም ሆነ ከሕግ ባለሙያዎች ጋር ተቀራርበው መነጋገር እንደቻሉ ገልፆልናል።

“ላለፉት ሦስት ቀናት ምግብም ስናቀርብላቸው አይቀበሉንም ነበር” የሚለው ናትናኤል ከሰኔ 15ቱ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የክልሉን ሰላም ለመጠበቅ በሚጣደፉበት ጊዜ በወንድሞቻቸው ተጠርጥረው ለእስር መዳረጋችው ሕሊናቸውን ሳይፈታተነው እንዳልቀረ ተናግሯል።

“በቁጥጥር ሥር ሲውሉ ወደ ፌደራል ሊወሰዱ እንደነበርና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፤ ጉዳዩን እዚህ ማየት ይችላል በሚል ታግለው እንዳስቀሯቸው አባቴ አጫውቶኛል” ብሏል።

በርሃብ አድማው ላይ የተወሰነ የጤና እክል እንዳጋጠማቸው የሚናገረው ናትናኤል የታሰሩት እነርሱ ብቻ ሳይሆኑ የውትድርና እውቀት ያላቸው ጠንካራ ግለሰቦችም እንደሚገኙ አክሏል።

“ክስ አልተመሰረተባቸውም፤ ማን እንደከሰሳቸው የተገለፀ ነገር የለም፤ በምን እንደተጠረጠሩም በግልፅ የሚያውቁት ነገር የለም” የሚለው ናትናኤል ከትናንት ጀምሮ ከጠበቆች ጋር እንዲገናኙና እንዲጠየቁ ሁኔታዎች መመቻቸታቸውን ነግሮናል።

ቀጣይ ቀጠሯቸውም ሐምሌ 19 ቀን 2011 ዓ.ም እንደሆነም ታውቋል።

“በዚህ መንገድ መገደላቸው ከፍተኛ የፀጥታ ችግር መኖሩን ያሳያል” ጄነራል ፃድቃን

የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አበረ አዳሙ በክልሉ አመራሮች ላይ ከተፈፀመ ግድያ ጋር ተያይዞ ከጉዳዩ ጋር ቅርበት አላቸው የሚባሉ የጸጥታ አካላትና ሌሎችም ተጠርጣሪዎች መኖራቸውን ይጠቅሳሉ።

በመሆኑም እነዚህ ግለሰቦች በተጠረጠሩበት ጉዳይ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውንና ምርመራ እየተካሄደ እንደሆነ ኮሚሽነሩ አስረድተዋል። “የማጣራቱ ሥራ ጊዜ ይፈልጋል” የሚሉት ኮሚሽነሩ ሥራው ሲጠናቀቅ ፖሊስ ጉዳዩን ለአቃቤ ሕግ እንደሚመራ ይናገራሉ።

ፖሊስ ግለሰቦቹን ጠርጥሮ የያዛቸው በምን ምክንያት ነው ስንል የጠየቅናቸው ኮሚሽነር አበረ “እሱ ምርመራ ላይ ያለ ጉዳይ ስለሆነ ለሚዲያ ማብቃት ለእነርሱም ለአድማጭም አይጠቅምም” ሲሉ በአጭሩ መልሰዋል።

ሰኔ 15 በተፈፀመው ጉዳይ ነው የተጠረጠሩት ከሚል መልስ በስተቀር ዝርዝር ሃሳብ ከመስጠትም ተቆጥበዋል።

ምርመራውን በዋናነት የሚመራው የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን መሆኑን የገለፁት ኮሚሽነሩ “የፌደራል መንግሥት አስተዋፅኦ ምንም ነው ማለት ግን ስህተት ነው” ብለዋል- በትብብር እየሰሩ እንዳሉ በመግለፅ።

‘የአደራ እስረኞች’ ናቸው የተባለው የአገላለፅ ችግር መሆኑን በመጥቀስ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የራሱ ማቆያ ጣቢያ ስለሌለው በ6ኛ ፖሊስ ጣቢያ የሚገኙት ተጠርጣሪዎቹ የጣቢያው እስረኞች አይደሉም ለማለት እንደሆነ ኮሚሽነሩ አብራርተዋል።

“አደራ ለዕቃ ነው፤ ለሰው አይደለም፤ የአደራ እስረኛ የሚባል የለም፤ ምርመራውን የሚያጣራው ጣቢያው አለመሆኑን ለመግለፅ ነው” ብለዋል።

“እነዚህ ሰዎች ከማንም በላይ ጓደኞቼ ነበሩ ፤ አሁንም ጓደኞቼ ናቸው። ነገርግን ተጠርጥረው ምርመራ እየተካሄደባቸው ነው” የሚሉት ኮሚሽነሩ በቅርበት ሄደው እንዳነጋገሯቸው ገልፀዋል።

ኮሚሽነሩ አክለውም “በእነሱ ስም ሌላ ኃይል የማይሆን ነገር እያለ ህዝቡን እንዳይረብሽ፤ እነርሱም ኃላፊነት እንዳለባቸው ተነጋግረናል። ጠበቃ እንዲቆምላቸው፣ ቤተሰብ እንዲጠይቃቸው፣ ምግብ እንዲመገቡ ተነጋግረን ተስማምተን ነው የተለያየነው” ብለዋል።

ከሰኔ 15ቱ ግድያ ጋር በተያያዘ የተጠርጣሪዎች ቁጥር በየጊዜው የሚለዋወጥ ቢሆንም በሁለት መቶዎች የሚቆጠሩ ተይዘው ከመቶ በላይ የሚሆኑት ተፈተዋል ብለዋል- ኮሚሽነሩ።

“አሁንም እያጣራን ማሰሩም፤ መፍታቱም ይቀጥላል” ሲሉ ተናግረዋል።

በመጨረሻም በአሁኑ ሰዓት ክልሉ መረጋጋቱን ኮሚሽነር አበረ ለቢቢሲ ገልፀዋል።