19 ጁላይ 2019

አቡነ አንጦኒዮ

ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የኤርትራ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶስ የቤተ ክርስቲያኗ ሦስተኛ ፓትሪያርክ የነበሩትን አቡነ አንጦኒዮን አውግዛ ከቤተክርስቲያኗ አገደች።

በስድስት የኤርትራ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጳጳሳት የተፈረመ ደብዳቤው እንደሚያሳያው፤ አቡነ አንጦኒዮስ “ምንፍቅና” ፈፅመዋል በሚል ከቤተ ክርስትያኒቱ መታገዳቸውን ተገልጿል።

ኤርትራ በቤተ ክርስቲያን ስር ያሉ የጤና ተቋማትን ወሰደች

ቅዱስ ሲኖዶሱ በመግለጫው ላይ፤ ሦስተኛው ፓትሪያርክ ከእንግዲህ በኋላ ከቤተ ክርስቲያኒቱ የተገለሉ መሆናቸውን አስፍሮ “መንፈሳዊ ስልጣን ባይኖራቸውም እንኳን ስለቀደመው አገልግሎታቸው ሲባል ቤተ ክርስቲያኒቷ በርህራሄ ዓይን አይታ አሁን ባሉበት የቤተ ክርስቲያኒቷ መኖሪያ ውስጥ እንዲቆዩና ሰብአዊ መብታቸው እንዲጠበቅላቸው” መወሰኑን አመልክቷል።

አቡነ አንጦኒዮስ የኤርትራን መንግሥት እንደሚተቹ የሚነገር ሲሆን፤ በ1998 ዓ. ም ላይ መንፈሳዊና አስተዳደራዊ ስልጣናቸውን ተገፈው ላለፉት 13 ዓመታት በቤታቸው ውስጥ በቁም እስር ይገኛሉ።

ከዚህ ቀደም አቡነ አንጦኒዮስ ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ከፓትርያርክነታቸው ተነስተው የመንግሥት ተወካይ ሥልጣኑን እንዲያዝ መደረጉን ሲገልጹ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል በማኅበራዊ ሚዲያ ተሰራጭቶ እንደነበር ይታወሳል። ተንቀሳቃሽ ምስሉ ከ13 ዓመታት በኋላ የአቡነ አንጦኒዮስ ድምፅ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰማበትም ነበር።

“አሁን ያገኘነው ሰላም ከሰው ሳይሆን ከአምላክ ነው”- ዘማሪ ሳሙኤል ተስፋሚካኤል

ከመንበራቸው ተወግዘው እንዲነሱ የተደረጉትን ፓትሪያርክ አቡነ አንጦኒዮስን የሚደግፉ ጳጳሳት የሲኖዶሱን ውሳኔ ተቃውመው ውሳኔው እንዲቀለበስና አቡኑ ወደስልጣናቸው እንዲመለሱ ጠይቀዋል።

የአቡኑ ተከታዮች የኤርትራ መንግሥትን በቤተ ክርስቲያኒቷ ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ ይገባል በማለት በተደጋጋሚ ክስ ያቀርባሉ።

የኤርትራ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን አራተኛ ፓትሪያርክ የነበሩት ዲዮስቆሮስ በ2007 ዓ. ም በሞት ከተለዩ በኋላ ቤተ ክርስቲያኗ ያለ ፓትሪያርክ ትገኛለች።