July 21, 2019

የህዝብ ለህዝብ መድረኩ የተጀመረው በቅርቡ ለተሰውት የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች የህሊና ፀሎት በማድረግ ነው፡፡

በመድረኩ ከአማራ ክልል የተውጣጡ የኅብረተሰብ ክፍሎችና የሀይማት አባቶች በሱማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጦፋ ሙሐመድ ዑመር ከተመራውና 100 አባላት ከሉት የክልሉ ልዑክ ጋር ተወያይተዋል፡፡

በዚህ ወቅት የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ላቀ አያሌው የካራማራን ታሪክ በማንሳት ሁለቱ ህዝቦች ለአገራዊ ሉዓላዊነትና ለፍትህ የከፈሉትን መስዋትነት ዘክረዋል፡፡

“የዛሬው ግንኙነት በአገሪቱ ለዘመናት የተሻገሩ የአንድነት እንቅፋቶችን በጋራ ታግሎ ለመጣል የተደረገ በመሆኑ ትርጉሙ ላቅ ያለ ነው” ብለዋል አቶ ላቀ፡፡

የአማራ ህዝብ በተሳሳተ የጨቋኝነት ትርክት አግላይ ፖሊሲዎች ሲጫኑበትና በርካታ ችግሮች ሲገጥሙት መቆየቱን አንስተዋል፡፡

ይህንን በመታገል ሂደትም የሱማሌ ህዝብና መንግስት ለአማራ ህዝብና መንግስት ያደረጉት አስተዋጽዖ ጉልህ መሆኑን አቶ ላቀ አውስተዋል፡፡

በጅግጅጋ በርካታ የአማራ ክልል ተወላጆች የሚገኙ እንደመሆኑ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብታቸው ተጠብቆ እየሰሩ እንዲኖሩ የክልሉ መንግስት እያሳየ ያለውን ቁርጠኝነትም አድንቀዋል፡፡

በ2010 ዓ.ም በጅግጅጋ ከተማና አካባቢው በተፈጠረው ግጭት 7 ቤተክርስቲያኖች ተቃጥለው የነበረ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ አምስቱን ክልሉ መልሶ በማስገንባት ወደ ስራ ማስገባቱ ተገልጿል፡፡

የሱማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጦፋ ሙሐመድ ዑመር ስለአብሮነትና አንድነት ያላቸው አቋም በአማራ ክልል ህዝብ ዘንድ ትልቅ ተቀባይነት ማግኘቱ ተጠቅሷል፡፡

በውይይቱ የሁለቱን ህዝቦች ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ትስስሮች የሚዳስሱ ሁለት ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበዋል፡፡

ጥናታዊ ጽሑፎቹ በዋናነት ሁለቱ ህዝቦች ለአገር ሉዓላዊነትና ነፃነት የከፈሉትን ዋጋ እንዲሁም የሚጋሯቸውን የአብሮነት እሴቶች የሚያጎሉ ናቸው ተብሏል፡፡

ሪፖርተር፦ ራሔል ፍሬው Sponsored by Revcontent