
በሲዳማ ዞን በተለያዩ ሥፍራዎች በተፈጸሙ ጥቃቶችና ዘረፋዎች ከባድ ጉዳት ደረሰ
21 July 2019
- ብሔር ተኮር ጥቃቶችና ዝርፊያዎች ተስተውለዋል
- በርካታ ሰዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል
በደቡብ ክልል ከሲዳማ ዞን የክልልነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአምስት ወራት ውስጥ ሕዝበ ውሳኔና ተዛማጅ ሥራዎች ለማከናወን ዝግጅት መጀመሩን ካስታወቀ በኋላ፣ በሲዳማ ዞን ውስጥ በተለያዩ ሥፍራዎች በተፈጸሙ ጥቃቶችና ዘረፋዎች ከባድ ጉዳት ደርሷል፡፡
በሐዋሳ ከተማና በአካባቢው የተለያዩ ሥፍራዎች በተነሳው ሁከት በግለሰቦች ቤቶች፣ በንግድ ተቋማትና በመንግሥታዊ ተቋማት ላይ ውድመት መከሰቱን የደቡብ ክልል አመራሮች ከማረጋገጣቸው በላይ፣ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎችም ተናግረዋል፡፡
የተደራጁ የሲዳማ ወጣቶች ቀደም ብለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የክልልነት ጥያቄውን አስመልክቶ አፋጣኝ ምላሽ ካልሰጣቸው፣ ሐምሌ 11 ቀን 2011 ዓ.ም. በራሳቸው የክልልነት ጥያቄውን እንደሚያውጁ እስከ ማስፈራራት ደርሰው ነበር፡፡
ምርጫ ቦርድም ከዚሁ ከሲዳማ የክልልነት ጥያቄ ጋር በተገናኘ ሐምሌ 9 ቀን 2011 ዓ.ም. የደረሰበትን አቋም በይፋ በማስታወቅ፣ ለሕዝበ ውሳኔው ዝግጅት ማድረጉን ገልጾ ነበር፡፡ ነገር ግን ከሐሙስ ሐምሌ 11 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ በሐዋሳና በአካባቢው ከተሞች በተፈጸሙ ጥቃቶች ጉዳት አጋጥሟል፡፡
በሲዳማ ዞን ኤጀቶ በመባል የሚታወቁት የተደራጁ ወጣቶች የምርጫ ቦርዱን መግለጫ ባለመቀበል፣ ከሐምሌ 11 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ በራሳቸው ክልልነትን ለማወጅ በሐዋሳ ከተማ መንገዶችን በመዝጋት ከፀጥታ ኃይሎች ጋር ተጋጭተዋል፡፡
ምንም እንኳ በሐዋሳ ከተማ ሦስት ሰዎች ሞተው ሦስት ቆስለው የከፋ ጉዳት ሳይደርስ የፀጥታ ኃይሎች ተቆጣጥረውታል ቢባልም፣ በሌሎች ሥፍራዎች ግን የከፋ ጉዳት መድረሱን ምንጮች ገልጸዋል፡፡
በተለይ በአለታ ወንዶ፣ በሁላ ወረዳ (አገረ ሰላም) እንዲሁም በይርጋለምና በአፖስቶ ከፍተኛ የንብረት ውድመት፣ ከሐሙስ ጀምሮ ዓርብ ዕለት እስከ ምሽት ድረስ እንደነበር የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል፡፡
የደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ሐዋሳ ከተማ ዓርብ ዕለት ከሐሙስ በተሻለ መረጋጋቱን ገልጿል፡፡ ነገር ግን በሌሎቹ ሥፍራዎች ተጨማሪ ግጭቶችና ውድመቶች እንደነበሩ ለማወቅ ተችሏል፡፡
ዓርብ ዕለት ለሐዋሳ የተሻለ መረጋጋት የነበረ ቢመስልም፣ በሕዝቡ ውስጥ ግን ከፍተኛ ፍርኃትና ሥጋት ነበር፡፡ የፀጥታ ኃይሎች ነዋሪዎች ከቤታቸው እንዳይወጡ በማሳሰባቸው ከተማው ጭር ብሎ ነበር፡፡
በተለይ በከተማው አላሙራ በሚባለው አካባቢ እስከ ዓርብ ምሽት ውጥረቱ ከፍተኛ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡
ሪፖርተር ከነዋሪዎቹ ማረጋገጥ እንደቻለው ቅዳሜ ዕለት በሐዋሳ ከተማ የሚታይ ግጭት ባይኖርም፣ የመንግሥት ተቋማት፣ ባንኮችና የተለያዩ የንግድ ቤቶች ዝግ ነበሩ፡፡
የመከላከያ ኃይልና የፌዴራል ፖሊስን ጨምሮ በከተማዋ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የፀጥታ ኃይል ተሰማርቷል፡፡
ነገር ግን ከሐዋሳ ውጪ ባሉ ከተሞች ችግሩ የከፋ መሆኑንና በርካታ የንግድ መደብሮችና የመንግሥት ተቋማት በተሰነዘሩ ጥቃቶች ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ ዓርብ ዕለት በይርጋለምና በአፖስቶ ከተሞች ብቻ ከ100 በላይ የመኖርያ ቤቶችና የንግድ ቤቶች ጉዳት እንደ ደረሰባቸው የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም በይርጋለም ከተማ በከንቲባው ቢሮ፣ መኖሪያ ቤትና ተሽከርካሪ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል ተብሏል፡፡ የዓርቡን ግጭት ለመከላከል የፌዴራል ፖሊስ ከቀኑ ሰባት ሰዓት ገደማ ደርሶ ሙሉ ለሙሉ ፀጥታውን መቆጣጠሩ ታውቋል፡፡
በይርጋ ዓለም፣ በአለታ ወንዶ፣ በአገረ ሰላምና አጎራባች ከተሞችም ተመሳሳይ ችግር ተከስቶ ነበር፡፡ የተለያዩ ምንጮች ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ጥቃቱ ሲዳማ ባልሆኑ የዞኑ ነዋሪዎች ላይ ያነጣጠረ ነው ተብሏል፡፡ ጥቃቱ ከዝርፊያና ከቃጠሎ በተጨማሪ በሰው ሕይወት ላይ ጭምር ተቃጥቶ፣ የተወሰኑ ሰዎች መሞታቸው ተሰምቷል፡፡ በዚህም ምክንያት የሲዳማ ተወላጅ ያልሆኑ ነዋሪዎች የመከላከያ ሠራዊት እንዲታደጋቸው ሲጠይቁ እንደነበር ታውቋል፡፡
ነገር ግን የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሚሊዮን ማቴዎስ ግጭቱ በታየባቸው ሥፍራዎች በተለይም በአለታ ወንዶና አካባቢው ብሔር ተኮር ጥቃቶች ታይተዋል ስለመባሉ ተጠይቀው በሰጡት ማብራሪያ፣ “በምልክት ደረጃ” ችግሩ መከሰቱንና ዝርፊያ መስተዋሉን አረጋግጠዋል፡፡ በሐዋሳ ሰላም እየሰፈነ መሆኑን፣ የተፈጠረው ችግር በመርገብ ላይ እንደሆነና የፀጥታ ኃይሎች በተገቢው መንገድ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የሲዳማ ተወላጅ ባልሆኑ ነዋሪዎች ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት ወደ ከፋ ደረጃ እንዳይደርስ በይርጋዓለም፣ በአለታ ወንዶና በሌሎች ሥፍራዎች የሲዳማ ተወላጅ የሆኑ የአገር ሽማግሌዎችና የንግድ ማኅበረሰቡ፣ በማረጋጋትና ጥቃት ለደረሰባቸው ከለላ በመስጠት ድጋፍ ማድረጋቸውን አቶ ሚሊዮን ጨምረው ገልጸዋል፡፡
ቅዳሜ ዕለት የወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ ከንግድና ከመሥሪያ ቤቶች በተጨማሪ በእምነት ተቋማት ላይ ጥቃት መፈጸሙን አመልክተዋል፡፡ በተለይ በአገረ ሰላም ከገለልተኛ ወገኖች ባይረጋገጥም በሦስት አብያተ ክርስቲያናት ላይ ቃጠሎ መድረሱ ተሰምቷል፡፡
እስካሁን ባለው ሁኔታ በተለያዩ ምንጮች በርካታ ቁጥሮች እየተጠቀሱ ሰዎች መሞታቸው ቢነገርም፣ የሟቾችን ትክክለኛ ቁጥር ለማወቅ አልተቻለም፡፡ የሲዳማ አርነት ንቅናቄ (ሲአን) ዓርብ ባወጣው መግለጫ 17 ሰዎች መሞታቸውን አስታውቋል፡፡ ከሐዋሳ 55 ኪሎ ሜትር በሚርቀው ወተሬሳ በሚባለው አካባቢ ብቻ 12 ሰዎች መገደላቸውን ሲአን ቢያስታውቅም፣ ከክልሉም ሆነ ከገለልተኛ ምንጮች ማረጋገጥ አልተቻለም፡፡ በሐዋሳ የሟቾች ቁጥር ሦስት እንደሆነ ግን ተሰምቷል፡፡
ሰሞኑን በሲዳማ ዞን ውስጥ በነበረው ሁከት ምክንያት በርካታ ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ታውቋል፡፡ የፖሊስ አባላት፣ የሲዳማ ሚዲያ ኔትወርክ ዋና ሥራ አስኪያጅና ምክትላቸው፣ እንዲሁም በጥቃቶችና በዘረፋዎች ተሳትፈዋል የተባሉ የተለያዩ ሰዎችን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ማሰሩን ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡
የሐዋሳ ከተማ ነዋሪ የሆኑ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ አንድ አዛውንት ለሪፖርተር እንደነገሩት፣ በደቡብ ክልል የተለያዩ ሥፍራዎች በመንግሥትና በግል ሥራ ከ40 ዓመታት በላይ ኖረዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሲዳማ ዞን ውስጥ የሚያዩት ድርጊት እንግዳ እንደሆነባቸው ተናግረው፣ ከፍተኛ የሰው ፍቅር ካላቸውና በእንግዳ ተቀባይነት ከሚያውቋቸው ሰዎች ጋር አሁንም በጉርብትና እንደሚኖሩ አስረድተዋል፡፡ ነገር ግን በወጣቶቹ ውስጥ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚያዩት ባህሪ የሲዳማን ሕዝብ እንደማይወክል፣ ነገር ግን ሌሎች የውጭ ኃይሎች ከኋላ እንደሚገፏቸው ምልክቶችን እንደሚያዩ ተናግረዋል፡፡ የክልልነት ጥያቄው በምርጫ ቦርድ ዕቅድ መሠረት ምላሽ አግኝቶ ሕዝበ ውሳኔው መካሄዱን ሽማግሌዎች ጭምር እየደገፉት፣ ወጣቶቹ አላስፈላጊ ድርጊት ውስጥ የሚሰማሩት በሌሎች ኃይል ግፊት ነው ሲሉም ያሰምሩበታል፡፡ ይህም ለማንም የማይጠቅም ነው ሲሉም ያክላሉ፡፡
የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን) ባለፈው ሳምንት ያወጣውን መግለጫ በማስመልከት፣ በክልሉ ውስጥ በተለያዩ ሥፍራዎች ተቃውሞ ተሰምቶበታል፡፡ ከተቃውሞዎቹ መካከል በወላይታ ዞን በአረካና በቦሎ ሶሬ ከተሞች የደኢሕዴንን ውሳኔ በመቃወም የወጡ ነዋሪዎች፣ የድርጅቱን ውሳኔ አድሏዊ በማለት ለሲዳማ ዞን የወገነ መሆኑን ተቃውመዋል፡፡ በካፋ ዞን በቦንጋ ከተማም ነዋሪዎች ደኢሕዴንን በመቃወም ሠልፍ በመውጣት ጥያቄያቸው ምላሽ እንዲያገኝ ጠይቀዋል፡፡ ደኢሕዴን ያወጣው መግለጫ ግልጽነት የጎደለውና ለመረዳት የሚያስቸግር መሆኑ ትችት ሲቀርብበት መሰንበቱ አይዘነጋም፡፡