
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ከጅማሮው በዋና ሥራ አስፈጻሚነት ሲመሩት የነበሩት ኢንጅነር ስመኘው በቀለ ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩ አንድ ዓመት አስቆጠሩ።
ኢንጂነር ስመኘው በቀለ በመስቀል አደባባይ መኪናቸው ውስጥ ህይወታቸው በድንገት አልፎ ከተገኘ በኋላ፤ በወቅቱ የፌደራል ፖሊስ በሰጠው መግለጫ ኢንጅነሩ ራሳቸውን እንዳጠፉ በምርመራው እንደደረሰበት ማሳወቁ ይታወሳል።
መኪናቸው ውስጥ የተገኘውም ሽጉጥ የኢንጂነሩ እንደነበር በምርመራው አረጋግጫለሁ ብሏል።
•ለህዳሴ ግድብ ግንባታ መዘግየት ምን አይነት መፍትሔዎች እየተሰጡ ነው?
•ስለአዲሱ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሥራ አስኪያጅ ጥቂት እንንገርዎ
የግድቡ ምልክት ተደርገው የሚወሰዱት ኢንጅነር ስመኘው ሞት፣ በርካቶችን ያስደነገጠ እና ኃገሪቱ በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ የፈሰሰበት የህዳሴ ግድብ ከየት ይደርሳል? የሚል ስጋትን የፈጠረም ነበር።
በኢንጅነር ስመኘው ቦታ የተተኩት የህዳሴ ግድብ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር ክፍሌ ሆሮ፤ ”አንድ ሰው በግሉ የሚቻለውን ያክል ነው አስተዋጽኦ ማበርከት የሚችለው እንጂ የጀመረውን ሁሉ ይጨርሳል ማለት አይደለም” በማለት የቀድሞውን የፕሮጀክቱን መሪ ያስታውሳሉ።
አክለውም ”ህዳሴ ግድብ የህዝብ ነው። እኔም አሻራዬን ትቼ ላልፍ እችላለሁ የኢንጅነር ስመኘውን አስተዋጽኦንም እንዲሁ ነው የምመለከተው” ይላሉ።
የቀድሞው የሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት መሪ ከሞቱ በኋላ ባለፉት አስራ ሁለት ወራት የህዳሴ ግድብ አፈጻጸም እንዴት ነው? ምን ተለወጠ? ምን ችግር አጋጠመው? ከኢንጅነር ክፍሌ ጋር ቆይታ አድርገናል።
• ”የሚፈርስ የግድቡ አካል የለም” የግድቡ ዋና ሥራ አስኪያጅ
ፕሮጀክቱ ለምን ዘገየ?
ኢንጅነር ክፍሌ ፕሮጀክቱ በታቀደለት የጊዜ ገደብ ባይሄድም በአሁኑም ወቅት ህዝብ እና መንግሥት ለአባይ ግድብ የሚያደርጉትን ድጋፍ እንዳላቋረጡ ይናገራሉ።
በዋናነት ከፕሮጀክቱ ጋር በተያያዘ ያጋጠሙ ሁለት ፈተናዎች አሉ የሚሉት ኢንጅነር ክፍሌ የመጀመሪያው ከስነ-ምድር (Geology) ጋር የተያያዘ እንደሆነ ይገልጻሉ።
የአባይ ወንዝ የሚሄድበት መሬት ሥሩ ጠንካራ ነው ተብሎ ወደ ስራ መገባቱን ገልፀው፤ ወደ ስራ ከተገባ በኋላ ግን መሬቱ እንደተጠበቀው ሳይሆን እንደቀረና መሬቱን ቆፍሮ በኮንክሪት የመሙላቱ ሥራ ብዙ ጊዜ መውሰዱን ኢንጅነር ክፍሌ ያስረዳሉ።
ለህዳሴ ግድብ መዘግየት እንደ ሁለተኛ ምክንያትነት የሚጠቅሱት ደግሞ ከብረታብረት እና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ጋር የተያያዘ ነው።
እንደ ኢንጅነር ክፍሌ ከሆነ መንግሥት የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ተቀርፆ ወደ ግንባታው ሲገባ በተቻለ መጠን በግድቡ ላይ ሃገር በቀል ተቋማት አስተዋጽኦዋቸውን እንዲያበረክቱ ቅድሚያ ተሰጥቷቸው ነበር።
በዚሁ መንፈስ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ሥራውን እንዲያከናውን በንዑስ ተቋራጭነት እንዲሰራ መወሰኑን ያስረዳሉ።
ተቋሙ የኤክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብን የመገንባት አቅምም ሆነ ልምድ ስለሌለው የግንባታ ስራውን ወደፊት ማስኬድ አልቻለም ብለዋል።
“ፕሮጀክቱ ላይ ብዙ ቢሊየን ብር ቢፈስም፤ መልክ አልያዘም” ይላሉ።
በአሁኑ ሰዓት የሲቪል ሥራው ከ80 በመቶ በላይ ቢጠናቀቅም፤ የብረት ቱቦዎች ሥራ፣ ተርባይኖችን ጨምሮ የመካኒካል ሥራዎች 20 በመቶ እንኳን እንዳልተጠናቀቁ ይናገራሉ።
መጋቢት 10፣ 2011ዓ.ም በነበረው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ምክርቤት ጽሕፈት ቤት፣ ከሚዲያ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ጋር በነበረው የውይይት መድረክ የግድቡ የግንባታ ቡድን ተወካይ አቶ ኤርሚያስ ውብሸት የግድቡ የሲቪል ሥራ 85 በመቶ፣ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራ 25በመቶ እና የብረታ ብረት ስራ 13 መድረሱንና በአጠቃላይ ፕሮጀክቱ 66.24 በመቶ ደርሷል ብለዋል።
መንግሥት ለሜቴክ ተሰጥቶ የነበረውን ውል ካቋረጠ በኋላ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና እና ልምድ ላላቸው ለአዳዲስ ተቋራጮች በመስጠት ወደ ስራ እንዲገቡ የማድረግ ተግባርም ተከናውኗል ።
በግንባታ ስራው ተሰማርተው የሚገኙት ስድስትተቋራጮች እንደሆነ የሚናገሩት ኢንጅነር ክፍሌ፤ ከእነዚህም መካከል የፈረንሳይ፣ ጀርመን እና ቻይና ኩባንያዎች ይገኙበታል ይላሉ።
በውይይት መድረኩ ላይም እንደተጠቀሰው ከተቋራጮቹም መካከል ሲጂጂሲ፣ ሳይኖ ሃይድሮ፣ ቮይት፣ ጂኦ ሃይድሮ ፍራንስና ኤክሲዲ ይገኙበታል በማለት በስም ይዘረዝራሉ።
•ስለኢንጂነር ስመኘው አሟሟት እስካሁን ምን እናውቃለን?
እንደ ተርባይን ያሉ ከውሃ ጋር ግንኙነት ያላቸው ግንባታዎች ከፍተኛ ልምድ የሚጠይቁ ሥራዎች መሆናቸውን ኢንጅነር ክፍሌ ገልፀው አዳዲሶቹ ተቋራጮች የግንባታ ሥራውን በተቀላጠፈ ሁኔታ እየሠሩ እንደሚገኙ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የሳሊኒ ቅሬታ እና የፕሮጀክቱ ክንውን
የሲቪል ሥራውን ለማከናወን ኮንትራት ወስዶ ሲሰራ የቆየው የጣሊያኑ ሳሊኒ ከግንባታ ክፍያ መዘግየት ጋር ተያይዞ ቅሬታዎችን ሲያሰማ ነበር።
ኢንጅነር ክፍሌ እንደሚሉት ሳሊኒ ያነሳቸው ቅሬታዎች አግባብነት ከተጠና በኋላ መንግሥት እና ሳሊኒ ከመግባባት ላይ ደርሰዋል ይላሉ።
“ሳሊኒ ሲያነሳው የነበረው ቅሬታ ‘ፕሮጀክቱ የዘገየው እኔ በፈጠርኩት ችግር አይደለም። ሜቴክ የሚጠበቅበትን የተርባይን እና ሌሎች ለፕሮጀክቱ የሚያስፈልጉ ብረቶችን በወቅቱ ማቅረብ ቢችል ኖሮ ሥራውን በሰዓቱ ማጠናቀቅ እችል ነበር። ፕሮጀክቱ በመዘግየቱ ለኪሳራ ተጋልጫለሁ’ የሚል ነበር” በማለት ኢንጅነር ክፍሌ ያስረዳሉ።
ሳሊኒ በዚህ ምክንያት ለደረሰበት ኪሳራ መንግሥት ካሳ እንዲከፍለው ጥያቄ አቅርቦ ነበር።
•ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ሕይወታቸው ያለፈው በጥይት ተመተው ነው፡ ፌደራል ፖሊስ
“ሳሊኒ የጠየቀውን ሁሉ አግኝቷል ማለት ሳይሆን በባለሙያዎች ከተጣራ በኋላ ውሳኔ ላይ ደርሰናል፤ ጉዳዩን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ለመቋጨት ተቃርበናል፤ ሳሊኒ በተደጋጋሚ ቅሬታውን ያቅርብ እንጂ አንድም ቀን ስራውን አላቋረጠም” ይላሉ ኢንጅነር ክፍሌ።
ፕሮጀክቱ በመዘግየቱ ሳሊኒ ብቻ ሳይሆን ጉዳቱ የኢትዮጵያ ህዝብ ጭምር ነው የሚሉት ኢንጅነር ክፍሌ፤ “እውነት ለመናገር ህዝቡ በግንባታው ሞራሉ ተነክቷል። ግንባታው የደረሰበትን ደረጃ በማስመልከት ለህዝብ የሚሰጠው መረጃ የተሳሳተ ነበር። እውነቱ ተደብቆ ቆይቶ በአንዴ እውነቱ ሲገለጥ ህዝቡ ማዘኑ አልቀረም” ይላሉ።
መቼ ይጠናቀቃል?
ፕሮጀክቱ በተጀመረበት ወቅት በአራት ዓመት ውስጥ በሁለት ተርባይኖች አማካኝነት ኃይል ማመንጨት ይጀምራል መባሉን እና በሰባት ዓመታት ውስጥ ደግሞ ሙሉ በሙሉ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደነበረ ኢንጅነር ክፍሌ ያስታውሳሉ።
ይህን መሰል ግዙፍ ፕሮጀክት በሰባት ዓመታት ውሰጥ መጨረስ ይቻላል ተብሎ መጀመሩ በራሱ ስህተት ነው የሚሉት ኢንጅነር ክፍሌ፤ ሜቴክ “የሚጠበቅበትን በወቅቱ ማድረግ ቢችል ኖሮ ቢያንስ በ2009 ላይ ኃይል ማመንጨት መጀመር ይቻል ነበር” ይላሉ።
ከሁለት አመታት በኋላ ኃይል የማመንጨት ጅማሮ እቅድ እንዳለ የሚናገሩት ኢንጅነር ክፍሌ በአራት ዓመታት ውስጥ ደግሞ ግንባታው ሙሉ በሙሉ የማጠናቀቅ እቅድም እንደተያዘ ይናገራሉ።
በተጠቀሱት ዓመታት ውስጥ ሁሉም ተርባይኖች ኃይል ማመንጨት ይጀምራሉ ማለት ሳይሆን በመጀመሪያ ግድቡ ውሃ የሚሞላበት ሁኔታ ላይ የታችኛው የተፋሰስ ሃገራትን ማወያየት ዋናው ስራ እንደሆነ ይናገራሉ።
“ተርባይኖቹ በሙሉ አቅም ኃይል የሚያመነጩት በግድቡ ውሃ መሙላት ላይ ተሞርኩዞ ነው። የተርባይኖቹ ስራ ግን ሙሉ በሙሉ ለመጨረስ ታቅዷል” ይላሉ።
የፕሮጀክቱ ተጨማሪ ወጪ ሃሳብ ሆኗል?
የዚህ ፕሮጀክት ወጪ ከህዝብ ከሚሰበሰበው እና መንግሥት ከሚመድበው በጀት ሲሆን፤ መንግሥት ተጨማሪ በጀት እየመደበ የግንባታ ሥራው እንዲቀጥል እያደረገ መሆኑንም ይናገራሉ።
ህዝቡም ከ12 ቢሊዮን ብር በላይ በማዋጣት ለፕሮጀክቱ ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱንም ጠቅሰዋል።
የውጪ ምንዛሬ እጥረት እና ከግንባታው መጓተት ጋር በተያያዘ ተጨማሪ ወጪ ፕሮጀክቱን እንደጎዳው የሚናገሩት ኢንጅነር ክፍሌ “ህዝብ እና መንግሥት አሁንም ፕሮጀክቱን ከግብ ማድረስ ያለስለሰ ጥረት እያደረጉ እንደሆነ” ተናግረዋል።