25 ጁላይ 2019

የደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ገዢ ፓርቲ የሆነው የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን) የሲዳማ ዞን አመራሮችን ጨምሮ በርካታ ከፍተኛ ባለስልጣናትን ከሃላፊነታቸው አገደ።
ከክልሉ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ቢቢሲ ማረጋገጥ እንደቻለው የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር፣ የሲዳማ ዞንና የሐድያ ዞን ከፍተኛ ባለስልጣናት ከነበሩበት የኃላፊነት ቦታ ታግደዋል።
• ክልልነት ለጠየቀው ሁሉ ቢሰጥ ችግሩ ምንድነው?
ድርጅቱ ለከፍተኛ አመራሮቹ መታገድ እንደ ምክንያት የጠቀሰው በክልሉ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች በተለይ ደግሞ በሐዋሳ ከተማና በሌሎች የሲዳማ አካባቢዎች ሰሞኑን ያጋጠሙትን ቀውሶች ሲሆን፤ የሐድያ ዞን ከፍተኛ አመራሮችም በዞኑ ውስጥ ታይተዋል በተባሉ የጸጥታ ችግሮች ውስጥ ሚና አላቸው ተብለው በመጠርጠራቸው ነው ተብሏል።
ከሐምሌ 11 2011 ጀምሮ በሐዋሳ፣ በአላታ ወንዶ፣ በሀገረ ሰላም፣ በወንዶ ገነትና ሌሎች የሲዳማ ዞን ወረዳዎች በተፈጠረ ግጭት እስካሁን ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎች ሲሞቱ በግለሰቦች መኖሪያ ቤቶች፣ በንግድ ተቋማትና በአብያተ ክርስትያናት ላይ በተፈጸመ ጥቃት ውድመት አጋጥሟል።
• ከሐዋሳ ተነስቶ በሌሎች አካባቢዎች ጉዳት ያደረሰው ሁከት
ደኢሕዴን ከተጠቀሱት አካባቢ ከፍተኛ ባለስልጣናት በተጨማሪ በተመሳሳይ ድርጊቶች ውስጥ ተሳትፈው ተገኝተዋል የተባሉ በክልሉ ሌሎች አካባቢዎች የሚገኙ ባለስልጣናት ላይም እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቋል።
በተያያዘ ዜና በሐዋሳ ከተማና በዙሪያዋ አጋጥሞ ከነበረው ሁከት ጋር በተያያዘ ለጸጥታ ሲባል በከተማዋ ውስጥ ሞተር ሳይክሎች እንዳይቀሳቀሱ እገዳ መጣሉን ቢቢሲ ያናገራቸው የሞተር ሳይክል አሽከርካሪዎችና የከተማዋ ነዋሪዎች ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
እርማጃው የተወሰደው ከጸጥታ ጋር በተያያዘ ምክንያት ነው ብለው የሚያምኑት የከተማዋ ነዋሪዎች እገዳ መጣሉ በክልሉ መገናኛ ብዙሃን በኩል እንደተገለጸ ጠቅሰዋል። አሽከርካሪዎች ግን ስለዚህ ጉዳይ ምንም የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
• በወንዶ ገነት ከተማ በነበረ ተቃውሞ 3 ሰዎች መሞታቸው ተገለጸ
በዚህም ምክንያት በሐዋሳ ከተማ በብዛት ይተዩ የነበሩት ሞተር ሳይክሎች ከዛሬ ጠዋት ጀምሮ እንደሌሉ የገለጹት አንድ ነዋሪ ትራፊክ ፖሊሶችም መንገድ ላይ ያገኟቸውን ሲያስቆሙ መመልከታቸውንና መኪኖችና ባጃጆች ግን በከተማዋ ጎዳናዎች ላይ እንደሚታዩ ገልፀዋል።
የሲዳማ ዞን ክልል እንዲሆን ጠይቆ የምርጫ ቦርድ በጉዳዩ ላይ ሕዝበ ውሳኔ ለማካሄድ የአምስት ወራት ቀጠሮ መስጠቱ ይታወሳል።