July 26, 2019

የሐዋሳ ከተማን ሕዝብ መብትና ጥቅም ሊያስከብር የሚችል ገለልተኛ አካል ከከተማው ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በምርጫ ቦርድ አማካኝነት እንዲደራጅ የጠየቁ አካላት አቤቱታቸውን ለምርጫ ቦርድ እንዳቀረቡ ጠየቁ።

ቢቢሲ ከኢትየጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንዳረጋጋጠው የሐዋሳ ከተማ ነዋሪዎችን ጥያቄ ለሚመለከተው አካል ለማቅረብ የተሰባሰበው ኮሚቴ አባላት ጥያቄታቸውን የያዘ ደብዳቤ ለቦርዱ መዝገብ ቤት አስገብቷል።

ከሐዋሳ ተነስቶ በሌሎች አካባቢዎች ጉዳት ያደረሰው ሁከት

ኮሚቴው ስድስት አመራር አባላት ያሉት ሲሆን የሐዋሳ ከተማን ጉዳይ በተመለከተ ለሲዳማ አመራሮች ብቻ ሳይተው ራሱ ምርጫ ቦርድ ጉዳዩን እንዲያስፈጽም ለመጠየቅ የተቋቋመ መሆንን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ኮሚቴው ዛሬ በጽሑፍ ባቀረበው አቤቱታ ላይ አማራጭ ያላቸውን አምስት ነጥቦችን ያስቀመጠ ሲሆን “በሐዋሳ ከተማ ውስጥ አንድ ሚሊዮን ያህል ነዋሪ ስለሚኖር የእነርሱ ድምፅ በሚገባ መደመጥ አለበት” ሲል ገልጿል።

በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት ምክር ቤት የሲዳማ ዞን የክልልነት ጥያቄን ለመወሰን በአምስት ወራት ውስጥ ሕዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ መወሰኑ ይታወቃል።

ስጋት ያጠላበት የሲዳማ የክልልነት ጥያቄና የሀዋሳ ክራሞት

ምርጫ ቦርድ ከባለድርሻ አካላት ይጠበቃል ብሎ ካስቀመጣቸው ተግባራት መካከል የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት ከክልሉ መንግሥትና ከዞኑ መስተዳደር ጋር በመመካከር በአሁኑ ወቅት የክልሉና የዞኑ አስተዳደር ዋና ከተማ ሆና የምታገለግለው የሐዋሳ ከተማን ይመለከታል።

በዚህም የሕዝበ ውሳኔው ውጤት የሲዳማን ክልል መሆን የሚያረጋግጥ ቢሆን በከተማዋ ላይ ሁለቱ አካላት የሚኖራቸውን መብትና ከዚህ ጋር በተያያዘ የሚነሱ የሃብት ክፍፍል ጥያቄዎችን የሚያስተናግዱበትን አሰራር አዘጋጅተው ለቦርዱ እንዲያሳውቁ ጠይቋል።

“ደኢህዴን የከተማውን ህዝብ ጥቅምና መብት ለማስከብር አቅም የለውም” ያሉት የኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ታገሰ ማዴቦ “የክልሉ አመራርም ሆኑ የከተማው አስተዳደር አካላት በተወሰኑ ሰዎች የተያዙ ናቸው” ይላሉ።

ክልልነት ለጠየቀው ሁሉ ቢሰጥ ችግሩ ምንድነው?

የኮሚቴው ሰብሳቢ እንደሚሉት ከሆነ “የደቡብ ክልል ፕሬዝዳንት፣ የፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት ኃላፊ፣ የካቢኔ ጉዳዮች ኃላፊ፣ የፕሬዝዳንቱ ልዩ አማካሪን የመሳሰሉ የክልሉ ቁልፍ የአመራር ቦታዎች በአንድ ወገን የተያዙ ሲሆን በሐዋሳ ከተማ አስተዳደርም ተመሳሳይ ሁኔታ በመኖሩ የምርጫ ቦርድ የከተማዋን እጣ ፈንታ በተመለከተ የዞኑ አስተዳደር ብቻ አጥንቶ እንዲያቀርብ እንዳያደርግ” ሲሉ ጥያቄ አቅርበዋል።

የኮሚቴው አባላት በደብዳቤያቸው ላይ እንዳስቀመጡት “የዞኑ አመራር ሕገ መንግሥቱን መሰረት አድርጎ ክልል የመሆን ጥያቄውን ሲያቀርብ የሌሎችን ሰዎች በሕገ መንግሥቱ የተሰጠ የመኖር መብት የሚገድቡ የወጣቶች እንቅስቃሴ ታይቷል” ሲሉ ስጋታቸውን ያስቀምጣሉ።

ለዚህም ከሐምሌ 11/2011 ጀምሮ በተለያዩ የሲዳማ ዞን ከተሞች የታየውን የንብረት ውድመት እና ሞት በመጥቀስ ስጋት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

ስለዚህ የምርጫ ቦርድ የከተማዋን እጣ ፈንታ በሚወስነው ውሳኔ ውስጥ ከተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች የተውጣጡ የከተማዋን ነዋሪዎች በገለልተኝነት አደራጅቶ ራሱ እንዲመራው፤ የሀብት ክፍፍልና ሊኖር የሚችል የመብት ጥያቄ ላይም የእነርሱን ተሳትፎ ባካተተ መልኩ እንዲወሰን ጠይቀዋል።

‘ከሕግ ውጪ’ የተዋሃዱት አምስቱ ክልሎች

ኮሚቴው አክሎም የሐዋሳ ከተማ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ሕገ መንግሥት፣ አንቀጽ 6 የተለያዩ ማህበረሰብ አባላት ተሰባጥረው የሚኖሩባት ከተማ መሆኗ በግልፅ የተቀመጠ በመሆኑ የከተማዋን ተጠሪነት ለፌደራል መንግሥቱ እንዲሆን ጠይቀዋል።

ኮሚቴው አክሎም የክልሉ ምክር ቤትና ምርጫ ቦርድ ከሚያቋቁመው አካል ጋር የሀብት ክፈልሉንም ሆነ የሚኖሩ መብቶችን እንዲያስከብር ጠይቀዋል።

አቤቱታቸውን ከምርጫ ቦርድ ውጪ ለሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት፣ ለፌዴሬሽን ምክርቤትና ለተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ማስገባታቸውን የገለፁት የኮሚቴው ሰብሳቢ ጥያቄያቸው በጎ ምላሽ እንደሚያገኝ ያላቸውን ተስፋ ገልፀዋል።


ምንጭ፦ BBC|አማርኛ