July 25, 2019

በምርጫ ህግ ላይ የቀረበው ረቂቅ የማሻሻያ አዋጅ የመድብለ ፓርቲ ስርዓቱን እንዳያዳክም ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለፁ።
ማሻሻያ ረቂቅ አዋጁን በተመለከተ ከፓርቲዎቹ ከህብረተሰቡ እና ከሲቪክ ማህበራት የተውጣጡ አካላት በተገኙበት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውይይት በመደረግ ላይ ነው።
በአገር አቀፍ እና በክልል ደረጃ የሚመሰረቱ ፓርቲዎች የመስራች አባላት ቁጥር 10 ሺ እና 4 ሺ እንዲሆን በረቂቅ አዋጁ መጠየቁ ከውድድር ያርቃል የሚል ስጋት እንዳሳደረባቸው ፓርቲዎቹ ገልፀዋል።
የቁጥሩ ከፍ መደረግ ጠንካራና ተፎካካሪ ፓርቲዎችን ለመፍጠር ቢያስችልም ፖለቲካዊ ተሳትፎን እና ሃሳብን ሊገድብ የሚችል በመሆኑም እንዲሻሻል ፓርቲዎቹ ጠይቀዋል።
በምርጫ የሚወዳደሩ የመንግስት ሰራተኞች በምርጫ ወቅት ያለ ጥቅማጥቅምና ደሞዝ ስራ መልቀቅ አለባቸው የሚል አንቀፅ በረቂቅ አዋጁ መካተቱም ተገቢ አይደለም ያሉት ፓርቲዎቹ፣ እንደተማረ የሚታሰበውን ኃይል ተሳትፎ የሚገድብ ነው ብለዋል።
የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ በበኩላቸው የፓርቲዎች መስራች አባላት ቁጥር ከፍ ማለት የተጠናከሩ ፓርቲዎች እንዲፈጠሩ በሚል እንደሆነ እንጂ የመድበለ ፓርቲ ስርዓቱን የማቀጨጭ ዓላማ እንደሌለው ተናግረዋል።
በአጠቃላይ አነስተኛ የህዝብ ቁጥር መሰረት ያላቸው ፓርቲዎች የፖለቲካ ተሳትፎ እንዳይገደብ በልዩ ሁኔታ የሚታይበት አካሄድ ሊኖር እንደሚችልም ሊቀመንበሯ ገልፀዋል።
በአልዓዛር ተረፈ