የትነበርሽ ንጉሤ
አጭር የምስል መግለጫ የትነበርሽ ንጉሤ

ድሬዳዋ ተካሂዶ በነበረው የአዲስ ወግ ምክክር መድረክ ላይ የትነበርሽ ንጉሤ ያደረገችው ንግግር በማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ዘንድ መነጋገሪያ ሆኗል። የትነበርሽ ከቢቢሲ ጋር አጭር ቆይታ አድርጋለች።

ቢቢሲ፡ ሰውን እንዲህ እንዲነጋገር ያደረገው ምን ነበር? እዛ መድረክ ላይ ማለት የፈለግሽውስ ምን ነበር?

የትነበርሽ፡ ብሔር የሚለው ቃል አገር ማለት ነው የሚለውን ፅንሰ ሐሳብ ለማስረዳት የተጠቀምኳት አንዲት አማራ፣ ኦሮሞ እንዲሁም ትግሬ የትም ይኖራል፣ ኦሮሞ የትም ይኖራል። ኦሮሞ ቋንቋ ነው እንጂ ብሔር አይደለም፣ ትግርኛም እንዲሁ።

ስለ ብሔር ስናወራ ስለ አገር ነው የምናወራው። ኦሮሞ የትም ይኖራል ብየ አንድ ምሳሌ ሰጥቻለሁ፤ ያ ምሳሌ ማዳጋስካር የምትባል አገር ናት። እኔ ለማለት የፈለግኩት ደሴት ውስጥ እንኳን ሰው ይገኛል እንኳን አገር ውስጥ የሚል ነው። እውነት ለመናገር እስከ ትናንት ጥዋት ድረስ ኦሮሞና ማዳጋስካርን የሚያገናኝ ፖለቲካ እንዳለ እኔ አላውቅም፤ ባውቅ ኖሮ እንደዚህ አይነት ምሳሌ አልጠቀምም፤ ሌላም አገር መጥራት እችል ነበር። ማሳየት የፈለግኩት እንኳን ትልልቅ አገራት ውስጥ ማዳጋስካር ደሴት ውስጥ ኦሮሞ አግኝቼ አውቃለሁ ነው ያልኩት።

“አካል ጉዳተኛ መሆኔ ጥሩ ደረጃ እንድደርስ አድርጎኛል”

ይህቺን ቃል የመዘዙ ሰዎች በአጠቃላይ ስለተነሳው ስለኔ ሀሳብ ሳያወሩ፤ ኦሮሞ ማዳጋስካር አግኝቻለሁ የሚለው አይቻለሁ ወደሚል ተቀየረ። እሷ እንዴት ነው ያየችው ወደሚል የአይነ ስውር ክርክር ውስጥ ገቡ። ከዛ በኋላም የራሳቸውን ሐሳብ ማራመድ የሚፈልጉ ሰዎች ማራመድ ጀመሩ። ከዚህ የምንረዳው አንደኛ ቦታው ላይ የነበሩ ሰዎች ብዙ ፅፈዋል። ሙሉ ንግግሩንም አንድ አፍታ የሚባል የማኅበራዊ ሚዲያ ድረ ገፅ ይዞት ወጥቷል። ድረ ገፁ በደንብ አብራርቶ ፅፎታል። ይሄ ሃሳብ እንደሌለኝና በዚህ መልክ ለምንድንነው የተረዳነው የሚለውን ይዟል።

ዋናው ነገር የኔን ሐሳብ ተጠቅመው ሰዎች የራሳቸውን መልእክት አስተላልፈዋል። ማዳጋስካር አግኝቻለሁ ብሎ ማለት ከማዳጋስካር ተሰደው ነው የመጡት ብለው መከራከሪያ የሚያቀርቡትን መደገፍ ነው ብሎ ማሰብ እንግዲህ በጣም የተራራቀ ነው። ሙሉ ንግግሩ በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ ተላልፏል። ኦንላይንም አለ። እነሱ የሚሉት ሐሳብ የተገለፀበት ቦታ የለም። ከንግግሩ ውስጥ ሦስት ቃላት መዘው አውጥተው ኦሮሞ ማዳጋስካር አግቻለሁ ማለት ክፋት ባይኖረውም፤ ያሳደሩት ቡኮ ስለነበራቸው ያንን ቡኮ ለመጋገር የሞከሩ ሰዎች አሉ።

የኦሳ 33ኛ ጉባኤ አዲስ አበባ ውስጥ ተጀመረ

መጀመሪያ ላይ አበሳጨኝ፤ ያላልኩት ነገር አለች ሲባል የኔ እምነት ያልሆነ ነገር በኔ ጭንቅላት ሊያስቀምጡ ሲሞክሩ ያበሳጫል። እያደር ሳስበው ግን ያው የምንታገለው ለሐሳብ ነፃነት አይደል? እነሱ የኔ ሐሳብ ነው ብለው ሐሳባቸውን ቢገልፁ ሐሳባቸው ይከበራል። እነዚህ ሰዎች ኦፖርቹኒስቲክ ናቸው፤ አጋጣሚ እየጠበቁ ታዋቂ፣ ተሰሚ መሆን የሚፈልጉ ሰዎች ናቸው። ማኅበራዊ ሚዲያም ላይ ከኔ በላይ ሰው ነው ትክክል እንዳልሆነ እየገለፀ ያለው፤ ብሔራዊ ሎተሪ ወይም ብሔራዊ ትምባሆ እንላለን ብሔር የሚለው ቃል ለቋንቋ በተለዋጭ እየተጠቀምንበት ነው። እሱ ስህተት ነው የሚል ሐሳብ ነው ያስቀመጥኩት።

ቢቢሲ፡ ሰዎች ሙሉውን ያንቺን ንግግር የያዘ ቪድዮ ቢያዩ የተሻለ ግንዛቤ ያገኛሉ ብለሽ ታስቢያለሽ?

የትነበርሽ፡ ሙሉ ቪዲዮውን ራሴ ፌስቡክም ላይ አስቀምጫለሁ፤ ነገር ግን ኤዲት አድርጋው ነው የሚል ሐሳብም አመጡ። አንድ አፍታዎች ናቸው በመጀመሪያ ያወጡት፤ ኤዲትም እንዳላደረግኩት አስቀምጠዋል። ሰዎች መረጃ ሲያገኙ ሙሉውን ቢያነቡ ጥሩ ነው። አልተደነቅኩም ምክንያቱም ይሄ የቆየ ተግባር ነው። እንደዚህ ሕዝብ የሚወዳቸው ሰዎች ሀሳብ እንዳይሰጡ ለማድረግ የሚደረጉ ጥረቶች ናቸው። የሚያሳዝነው ግን የሀሳብ ነፃነትን ለማስከበር የሚታገሉ ሰዎች የሌሎችን የሃሳብ ነፃነት እንዲህ ባለ ኢፍትሐዊ በሆነ መልኩ ለመርገጥ መሞከራቸው ተገቢ አይደለም።

ሌላው አንድ ነገር ሲነገር የተነገረበት ኮንቴክስት (አውድ) ምንድን ነው? የሚለውን ማየት ተገቢ ይሆናል። አለበለዚያ እንዳንነጋገር በር ይዘጋሉ። በአሁኑ ሰዓት ደግሞ ኢትዮጵያን ከችግር ሊያወጣት የሚችለው ነገር መነጋገር፣ መደማመጥ፣ መከባበርና መፈላለግ ነው። ከዚህ ነጥለው ሊያወጡን የሚሞክሩ ኃይሎችን እምቢ ማለት በሐሳባችንም በድርጊታችንም የኛ ድርሻ ነው ብየ አስባለሁ። እኔ ማኅበራዊ መሪ ነኝ ብየ ነው የማስበው፤ ፖለቲከኛም አይደለሁም። ፖለቲከኛም መሆን አልፈልግም። ለፖለቲካ አጀንዳ መጠቀም ስህተት ነው ምክንያቱም መጨረሻ ላይ ፊት አላደርግም፤ አልሆንም።

የሐዋሳ ከተማ ነዋሪዎች ለምርጫ ቦርድ አቤቱታ አቀረቡ

ያግባቡናል፤ ማህበረሰቡን እንደ ማህበረሰብ ወደፊት ይወስዳሉ ብየ የማስባቸውን የራሴን ሐሳቦች እናገራለሁ፤ ሌሎችም እንዲናገሩ እድሉን እሰጣለሁ። ሰዎች ሐሳባቸውን በነፃነት እንዳይናገሩ እንቅፋት በመሆን የሐሳብ ነፃነትን ማረጋገጥ አይቻልም ስህተት ነው። የምናደርገውና የምንናገረው አንድ መሆን እንኳን ባይሆን፤ ባይቃረን ጥሩ ነው ብየ አስባለሁ። እኔ የማምንበት ነገር ትክክል ነው ሰዎች ይቀበሉኝ የሚል እምነት የለኝም፤ አለማመን መብታቸው ነው። ምክንያቱም ወደፊት ለመሄድ አንድ አይነት መሆን አይጠበቅብንም፤ ነገር ግን የኔን ክብር የሚነካ ነገር በማድረግ፤ ሐሳቤን በሐሳብ ማሸነፍ ይቻላል አሁን የተያዘው ግን የካራክተር አሳሲኔሽን ጉዳይ ነው።

ይሄ እንግዲህ እኔን በግልፅ ለማጥቃት እንደሆነ የምታውቀው የስልክ ቁጥሬ ድረ ገፁ ላይ ተቀምጧል። እግዚአብሔር ይስጣቸው እስካሁን የደወሉልኝ ሰዎች በጣም አስተዋይ፣ አክባሪ ለማድመጥ የሚፈልጉና መጨረሻ ላይ ተግባብተን የተለያየንና እነሱም በራሳቸው ገፅም አስተያየታቸውን የሰጡ ሰዎች ናቸው። እነሱ እንደሚያስቡት ለሚፈልጉት አላማ የስልክ ቁጥሬ የዋለ አልመሰለኝም። ስልክ ቁጥር መስጠትም ስህተት ነው። በወንጀል ከሰህ ቅጣት ማስቀጣት ይቻላል። ያንን ያህል ርቀት መሄድ አስፈላጊ ነው ወይ? ለነሱስ እንዲህ አይነት ጉልበት (ኢነርጂ) ማባከን ይጠቅማል ወይ? ያው የሥራ ዘርፋችን ይለያያል፤ አንዳንዶቹ በወሬ ይተጋሉ ሌሎቻችን በሥራ መትጋት አለብን ስለዚህ ወደ ሥራየ አተኩሬያለሁ።

እኔ የማግዛቸው የበጎ አድራጎት ተቋማት አሉ። እኔ ከሕዝብ ጋር ያገናኘኝ ፌስቡክ አይደለም፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያውቀኝ በፌስቡክ ፀሐፊነት አይደለም፤ ወይም በፖለቲካ ሐሳብ አራማጅነቴ አይደለም። የተፈጠርኩትም፣ የመጣሁበትም መንገድ ለዛ አይደለም ስለዚህ ወደሥራየ ተመልሻለሁ። ያው እንዲህ ሲሆን ከመደበኛ ሥራ ይረብሻል።

ቢቢሲአሁን ያለው የፖለቲካ ሁኔታ፣ የብዙዎች ስሜተ ስሱ መሆን ነገሩ እንዲካረር አድርጓል ብለሽ ታስቢያለሽ?

የትነበርሽ፡ እኔ ንግግሬን ብዙ ሰው ወስዶታል ብየ አላስብም። ብዙ ሰው አልተረጎመውም ያስደሰተኝም ይሄው ነው። እነዚህ ሰዎች ቢያንስ እንደማይሳካላቸው ያውቃሉ። ተስፋ ይቆርጣሉ ብየ አስባለሁ፤ የጥቂት ሰዎች ሙከራ ነው እንጂ በርካታ የኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪ ወጣቶች ደውለውልኛል፤ ከአዳማ፣ ከኤሊባቡርና ከሌሎችም አካባቢዎች፤ በጣም ተደስቻለሁ። እግዚአብሔር ያክብራቸው። እንዲህ አይነት ልጆች አሉን። ሙሉውን እንዳልሰሙትና ይህንን ቃል እንዴት ተናገርሽ? የሚል በርካታ ጥያቄዎች ጠይቀውኛል። ግብታዊ ሆነው አንድ ሰው ክፉ ቃል የተናገረኝ የለም። ተሰምቶኛል፣ አንቺ እንዴት? ያለኝ ሰው አለ እናም ሳስረዳው ጊዜው እኮ መጥፎ ነው እና ምንም ባትይ ብለውኛል። እኔም እነሱ በመደቡኝ አልንቀሳቀስም።