July 26, 2019

ጃዋር የኦሮሞ ብሄረተኛ አክቲቪስት ነው። ኢትዮጵያዊ ነኝ ስለማለቱ የማውቀው ነገር የለም። ኢትዮጵያዊ አይደለሁም ያለን ሰው በግድ ኢትዮጵያዊ ነህ ልለው አልችልም። ኢትዮጵያዊ አይደለሁም የማለት መብቱ ነውና። ኦሮሞ ነኝ ስለሚል ግን ኦሮሞ ነው።
እኔ ግን የኦሮሞ አያቶች ቢኖሩኝም ራሴን ኦሮሞ ነኝ ብዬ አልጠራም። በጎጃሜና መንዜ አያቶቼ ምክንያት አማራ ነኝ እንደማልለው። እንኳን “ኦሮሞ፣ አማራ” ልል ቀርቶ ሌላውም ኦሮሞ፣ አማራ ሲል አይመቸኝም።
ጃዋር መሐመድ በኢትዮጵያ ውስጥ በክፉም ሆነ በበጎ ብዙ የሚጠራ ሰው ነው። ታዋቂ ነው። በተለያዩ ጊዜያትም ይህ ሰው በሚያራምደው ፖለቲካ ዙሪያ ጠንካራ ትችቶችን አቅርቤ አውቃለሁ። በግሌ በአሁኑ ወቅት በአገራችን ትልቅ ችግር እየፈጠሩ ያሉትም እነ ጃዋር ያሉበት የኦሮሞ ጽንፈኛ ፖለቲከኞችና አክቲቮስቶች እንደመሆናቸው፣ የነርሱ እንቅስቃሴ ላይ ብእሮቼ የተሳሉ ናቸው።
ታዲያ አንድ አብርሃም ለማ የሚባል የኦሮሞ ብሄረተኛ፣ በነጃዋር ዙሪያ የምጽፈውን ተመልከቶ፣ ‹አታስበዉ ጀዋር እነዳንተ ቃዥቶ አይደለም እዚህ የደረሰዉ። ቀን ሌሊት እየስራ ነዉ፡፡ ወደድክም ጠላህም ጀዋር የተግባርና የመርህ ሰዉ ነዉ፡፡ስለማታዉቀዉ ስለሱ አዉርቶ ታዋቂ መሆን አይቻልም፡፡ከቻልክ ከሱ የተሻለ ስራ» ፣ የሚል አስተያየት ሰጠኝ።
እኔም የመለስኩለትን እንደሚከተለው ላጋራችሁ ወደድኩ።
«ወዳጄ ማፍርስ ቀላል ነው፣ መገንባት ከባድ ነው። ማለያየት ቀላል ነው። አንድ ማድረግ ከባድ ነው። መረበሽ ቀላል ነው። ሰላም ማምጣት ከባድ ነው። ዘርን ሰብኮ ደጋፊ ማሰባሰብ ቀላል ነው። ፍቅርን ሰብኮ ሰውን ማዛመድ ከባድ ነው። መጥላት ቀላል ነው። መውደድ ከባድ ነው። የጎሳ ፖለቲካን ማራመድ ቀላል ነው። የአንድነት ፖለቲካን ማካሄድ ከባድ ነው። ብሶት ማውራት ቀላል ነው። መፍትሄ ማምጣት ከባድ ነው። ሰዉን ዘቅዝቆ መስቀል ቀላል ነው፣ የወረደ ነገር ነው። እንደ እንሳሳ መሆን ነው። ሰውን ማንሳት ግን ከባድ ነው። ትልቅነት ነው» አልክት።
ሳክልም
” ጃዋርና እኔ አንወዳደርም።
አንደኛ – እኔ ፖለቲካ ሞያዬ አይደለም። የምጦምረው፣ የምጽፈው ደሞዝ እንዲከፈለኝ አይደለም። የምጦምረው ስለሚያገባኝ ነው። በሞያዬ ፊዚሲስት ነኝ፤ ኢንጂነር ነኝ።፡በአንድ ትልቅ የአሜሪካ ኩባንያ የምሰራ።
ሁለተኛ – እኔ “ኦሮሞ ትልቅ ነው፣ ኦሮሞ ግንድ ነው። ኦሮሞ አቃፊ ነው። ኦሮሞ የሚጠቀመው ከሌላው ኢትዮጵያዊ ወንድሙ ጋር ሲተሳሰር ነው፤ ኦሮሞው መነጠል የለበትም፤ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት ማደግ አለበት” ባይ ነኝ። ጃዋር ኦሮሞዉ ከሌላው እንዲነጠል፣ በሌላው እንዲፈራ፣ የሚያደርግ፣ በኦሮሞዉና በሌላው መካከል አጥር የሚያበጅ ነው። እነርሱና እኛ የሚል ነው።
ሶስተኛ – እኔ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በማንኛውም የአገሪቷ ክፍል መጤ፣ ወራሪ ሳይባል በነጻነት እንደ አገሩ መኖር አለበት ባይ ነኝ። ጃዋር “ኦሮሞ የኦሮሞ ብቻ ነው።ሌላው እንደ ዉጭ አገር ዜጋ፣ ኬኒያ እንዲሚኖር በኦሮሞ ፍቃድ መኖር ይችላል” የሚል በአንድ አካባቢ እኩልነትን ሳይሆን የአንድን ጎሳ የበላየነት የሚሰብክ ዘረኛ ነው።
አራተኛ – እኔ ወያኔና ኦነግ በሕዝቡ ላይ የጫኑት የጎሳ አወቃቀር መፍረስ አለበት ባይ ነኝ። ጃዋር የኦነግና የሕወሃት ስርዓት እንዲቀጥል ነው የሚፈልገው። ምክንያቱም ኦሮሞ፣ ትግሬ፣ አማራ መባባል ከቀረ፣ ስራ አይኖረውም»
“ታዋቂ ለመሆን ከፈለክ” ላለው ወንድሜ ታዋቂ ለመሆን የሚፈልጉ የበታችነት ስሜት ያለባቸው፣ በራሳቸው የማይተማመኑ ሰዎች ናቸው። ግርማ ካሳ ያደረገውን ፣ የሰራዉን፣ ምን እንደሚመስል ፎቶዎች ሲለጥፍ አይታይም። እነ ዶ/ር አብይ ሲመጡ፣ እነ አቶ ገዱ አሁንም መጥተው መድረክ ፍለጋ ግርማ ካሳ ሲሯራጥና ሲሽቀዳደም አልታየም።አለሁ፣ አለሁ አላለም።
እኔ የምጽፈው ለመታወቅ፣ ለመወደድ፣ ፣ ሰውን ለማስደስት አይደለም። ያ ቢሆን ኖሮ ቄሮ፣ ቄሮ በሚባለበት ወቅት ደፍሬ የቄሮ አክራሪነትን ቀድሜ ባልተቃወምኩ ነበር። ሳር ቀጠሉ ግንቦት ሰባት ግንቦት ሰባት በሚልበት ወቅት ግንቦት ሰባትን ባልተቸው ነበር።፡ ግርማ ካሳ የራሱ ሰው ነው ። አራት ነጥብ። Sponsored by Revcontent