July 27, 2019
Posted by: Girma Kassa
Source: https://www.zehabesha.com/amharic/archives/96187

ይድነቃቸው ከበደ፣ የቀድሞ የሰማያዊ ፓርቲ ከፍተኛ አመራር ፣ በወህኒ የባላደራው አመራር አባላትን አለማግኘት ሞክሮ የሚከተለውን ዘገባ አስፍሯል።
—————
ዛሬ ጠዋት ወንድሞቼን የእውነት አምላክ ያስፈታችሁ ለማለት ፤ በግፍ ወደ-ታጎሩበት እስር ቤት ለመጠየቅ ሄጄ ነበር ። የእስር ቤቱን የአሰራር ደንብ ተከትዬ ለ1 ሰዓት ያህል ወረፋዬን ጠብቄ ፤ ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ ፣ አቶ መርከቡ ሀይሌ እና አቶ ስንታየሁ ቸኮል አግኝቻቸዋለሁ ። ሦስቱም ለጤናቸው ደህና ናቸው ፤ በፊታቸው ላይ የሚታየው የወትሮው የእነሱ መገለጫ የሆነ ፈገግታቸው እና ቅን የሆነዉ ንግግራቸው አሁንም እንዳለ ነው።
የጤናቸው ሁኔታ እና የወዳጅነት ሰላምታ ከተለዋዋጥን በኋላ ፤ ሦስቱም ስለ-ተጠረጠሩበትና ታስረው ስለሚገኙበት የሽብር ክስ ሃሳባቸውን አጋርተውኛል ፤ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ሊያውቁልን ይገባል የሚሉትን መልዕክት አስተላልፈዋል ።
ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ ፦ ” በስመአብ” በማለት የአግራሞት ሳቅ በመሳቅ ፤ ” ከእኔ ጋር ተከሳች የሆኑት 13ቱ ተከሳሾች አንዳቸውንም ከዚህ ቀደም አይቼቸው አላቅም ፣አያውቁኝም አላውቃቸውም ፤ ነገር ግን ከእነሱ ጋር በመሆን ፣ ከፍተኛ ባለስልጣናት ግድያና መፈንቅለ መንግስት ሙከራ አድርገሃል ተብዬ በሽብር ወንጀል ተጠርጥሬ መታሰሬ አስገርሞኛል። በዶ/ር ዐቢይ የሚመራው መንግስት እንዲህ አይነቱ የሐሰት ውንጀላ ውስጥ በዚህ ፍጥነት ይገባል ብዬ አልገመትኩም ነበር ፤ በእኔ ላይ የተፈጸመው መንግስታዊ በቀል ነው ፤ ሃሳቡን በነፃነት የመግለጽ መብቴን ተጠቅሚ ለአገር እና ለወገን ይጠቅማል ብዬ የማስበውን ሁሉ፣ የሌላውን መብት ሳልጋፋ በአገኘሁት አጋጣሚ ከመግለጽ ወደኋላ አላልኩም ። በተለይ በአዲስ አበባ ጉዳይ ሃሳብና ትችት ከመስጠት ባለፈ ፣ የእኔን ሃሳብ ከሚጋሩ ጋር በመሆን የበኩሌን በጎ አስተዋጽኦ፣በህጋዊ መንገድ ለማድረግ ጥረት አደርግ ነበር። እነኚህ እንቅስቃሴዎቼ በሙሉ አሁን ላይ በስልጣን ላይ የሚገኘው መንግስት ደስ አላሰኘውም ፤ ለዚህም ነው በማላውቀው ወንጀል የተወነጀልኩት” በማለት የደረሰበትን በደል በመግለጽ ፤ “የእውነት አምላክ ፍርዱን ይሰጣል ! ” የሚል መልዕክቱን አስተላልፏል።
አቶ መርከቡ ሀይሌ እና አቶ ስንታየሁ ቸኮል፤ ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ ከነገረኛ ብዙም የተለያየ ነገር አልነገሩኝም ። የእነሱም ክስ ተመሳሳይ ነው። አቶ ስንታየሁ ፦ ” እኔ በአዲስ አበባ ጉዳይ ላይ ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ እንደሚያውቀው፤ ከሰብዓዊ መብት ተሟጋች እና ጋዜጠኛ ከሆነው ከእስክንድር ነጋ ጋር በመሆን፤ ማንንም ያላገለለች ፣ የሁሉም የሆነች እንዲሁም ማንንም ከማንም የተለየ ጥቅም የማያገኝባት፤ የሁላችን የሆነችው አዲስ አበባ ከተጋረጠባት አደገኛ ችግር ለመታደግ ፤ የምናደርገው እንቅስቃሴ ለማዳከም እና እኛንም ለመበቀል የተመሰረተብን የሐሰት ወንጀል ነው ” ሲል ሃሳቡን የገለጸልኝ ሲሆን ። አቶ መርከቡ ፦ ” እንኳን ላደርገው ይቅርና አስቤውም ባማላውቀው ወንጀል፣ ለዛውም ሰውን በመግደል እና በማስገደል በሽብርተኝነት ክስ መከሰሴ አሁን ድረስ እውነት አልመስል እያለኝ ነው “በማለት “በእኔ እና በጓደኞቼ ላይ በቀጥታ የተፈጸመብን መንግስታዊ በቀል ነው” ብሎኛል ።
ሦስቱ’ም እንደነገሩኙ ከሆነ ፤ እስከዛሬ ድረስ በምርመራ ወቅት የሚጠየቁት ” ከአዲስ አበባ ባላደራ ምክር ቤት ባልደራስ ” እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ ጉዳይ እንጂ፤ አንድም ቀን ተሞከረ ስለተባለው “የመፈንቅለ መንግሥት እና በተገደሉ ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ” ጉዳይ ጋር በተያያዘ በምርመራ ወቅት ተጠይቀው እንደማያውቁ ገልጸውልኛል ።