- 28 ጁላይ 2019

አቶ ዘካሪያስ አስፋው ሸንቁጥ የአቶ ሙሉጌታ አስፋው ሸንቁጥ ወንድም ናቸው። መጋቢት 1 ማለዳ ወደ ናይሮቢ 157 መንገደኞች ጭኖ ይበር የነበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ውስጥ ከነበሩት መካከል አንዱ ነበሩ።
አቶ ዘካሪያስ እንደሚሉት አውሮፕላኑ እሁድ ማለዳ ሊከሰከስ እርሳቸውና ወንድማቸው ማታ ቤተሰቦቻቸው ቤት አብረው እራት በልተው ሲጫወቱ አምሽተዋል።
ቤታቸው አቅራቢያም እየተንሸራሸሩ ስለሁለቱም የግል ሕይወት የሆድ የሆዳቸውን አውግተዋል። አቶ ሙሉጌታ ባለትዳርና የሦስት ልጆች አባት እንደነበሩ ይናገራሉ።
አቶ ሙሉጌታ ወደ ናይሮቢ ለመጓዝ የተነሱት ከሥራቸው ጋር በተያያዘ ለስብሰባና ለስልጠና እንደነበር ይናገራሉ።
አቶ ዘካሪያስ በወንድማቸው ሞት እርሳቸው፣ የአቶ ሙሉጌታ ባለቤትና ልጆቻቸው እንዲሁም ወላጆቻቸው በሀዘን ስሜታቸው መጎዳቱን ይገልጣሉ።
• ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖችን ማምረት ላቆም እችላለሁ ሲል አስጠነቀቀ
• “ኦሮሞ እና ማዳጋስካርን የሚያገናኝ ፖለቲካ እንዳለ አላውቅም” የትነበርሽ ንጉሤ
እርሳቸውና የሟች የአቶ ሙሉጌታ ባለቤት ወንድም በአሜሪካ ስለሚኖሩ ከዚህ አደጋ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ማናቸውንም ሕጋዊ ጉዳዮች ለማስጨረስ ከወንድማቸው ባለቤት ሕጋዊ ውክልና መውሰዳቸውን ይናገራሉ። ለዚህም የአየር መንገድ ጉዳዮችን በመያዝና ጥብቅና በመቆም የሚታወቁ ጠበቆችን በማፈላለግ አውሮፕላን አምራቹን ቦይንግን ከሰዋል።
አቶ ሼክስፒር ፈይሳ በአሜሪካ ሲያትል ነዋሪ ሲሆኑ በጥብቅና ላይ ከ18 ዓመታት በላይ ልምድ እንዳላቸው ይናገራሉ። የአቶ ዘካሪያስ ወንድምንና ሌሎች በዚህ አደጋ ቤተሰቦቻቸውን ያጡ ኬኒያውያንን ጉዳይ ይዘው ቦይንግ ላይ ክስ መመስረታቸውን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
የእርሳቸው የጥብቅና ድርጅት፣ ከፍሪድመን ሩበን እንዲሁም ፓወር ሮጀርስ የሕግ ቢሮዎች ጋር አብረው እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
አቶ ሼክስፒር እንደሚሉት ሲያትልና ቺካጎ ውስጥ ከአየር ትራንስፖርት ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ልምድ ያላቸውን ጠበቆች በማሰባሰብ፤ በኢትዮጵያና በኬኒያ ከሚኖሩ የአደጋው ሰለባዎች ቤተሰቦች ጋር በመነጋገር ቦይንግንና በዚህ አውሮፕላን ማምረት ሂደት ውስጥ የተሳተፉትን መክሰሳቸውን ይናገራሉ።
ቦይንግ ላይ የመሰረቱት ክስ እንደደረሰው የተናገሩት አቶ ሼክስፒር መልሳቸውን እየተጠባበቁ መሆኑን ገልጠዋል።
ቦይንግ ላይ የ37ገፅ ያለው ክስ መመስረቱን ተናግረው የክሱ ጭብጥን ሲያስረዱ ቦይንግ በርካታ ማስጠንቀቂያ እየተሰጠው ስህተቱን ባለማረም፣ በተለይ የኢንዶኔዢያው ላየን ኤር ጥቅምት ላይ ተከስክሶ፤ አውሮፕላኑን እስካ ለበት ጉድለት ለኢትዮጵ ሕዳር 2018 ላይ ማስረከባቸው አንደ አንድ ምክንያት ይጠቅሳሉ።
እንዲሁም ቦይንግ አውሮፕላኑ ችግር እንዳለበት እያወቀ ሆን ብሎ ለኢትዮጵያና ለሌላ ሀገሮች መሸጡ፣ ለአሜሪካን አየር መንገዶች የሚሸጠውና ለሌሎች ኢትዮጵያን ለመሰሉ ሀገራት የሚሸጠው የተለየ መሆኑን በዚህም የሰው ሕይወት በመጥፋቱ ለሰዎቹ ካሳ ከዚህም አልፎ ቦይንግ ራሱ እንዲቀጣ የሚል ክስ ማቅረባቸውን ይናገራሉ።
ቦይንግ ክስ ላይ የገንዘብ ካሳ መጠን እንዳላስቀመጡ ገልፀው ለጠፋው የሰው ሕይወት እና ኩባንያው ዳግመኛ እንዲህ አይነት ጥፋትን እንዳይደግም ማስተማሪያ የሚሆን የመቀጣጫ ቅጣት በሰው እስከ አንድ መቶ ሚሊየን ዶላር ድረስ ይቀጣል የሚል ግምት እንዳላቸው ገልፀዋል።
ቦይንግ በ2018 በዓመት 110 ቢሊየን ዶላር ያተረፈ ኩባንያ ነው።

ጥያቄ ለፌደራል አቬይሽንአስተዳደር
አቶ ሼክስፒር እንደሚሉት ET 302 ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን ውስጥ 157 ሰዎች ተሳፍረው የነበረ ቢሆንም እስካሁን ቦይንግ ላይ ክስ የመሰረቱት ገሚሶቹ መሆናቸውን ጠቅሰው ከእነርሱ ውጪ እስካሁን ድረስ ማንም ይህንን ተቋም አለመክሰሱን ይናገራሉ።
ተቋሙ የቦይንግ አውሮፕላኖች መብረር ይችላሉ የሚል ፈቃድ የሚሰጥ መንግሥታዊ ተቆጣጣሪ ተቋም ሲሆን ክሳቸው እንደሚያስረዳው ተቋሙ ሥራውን ትቶ ከአምራቹና ነጋዴው ኩባንያ ጋር “ሴራ” ውስጥ መግባታቸውን በመጥቀስ እንደከሰሱ ተናግረዋል።
የፌደራል አቬይሽን ባለስልጣን አንድ አውሮፕላን ተሰርቶ ሲያልቅ ወደ ገበያ ከመቅረቡ በፊት መፈተሽ፣ መመርመርና ለበረራ ብቁ ሆኖ ካገኘው ሰርተፊኬት የሚሰጥ ተቋም ነው።
ነገርግን በቂ የሰው ኃይልና ገንዘብ የለንም በሚል የመፈተሽና የመመርመሩን ኃላፊነት ለራሱ ለቦይንግ ሰጥቶት ነበር።
• “እናቴ ካልመጣች አልመረቅም” ኢዛና ሐዲስ ከማንችስተር ዩኒቨርስቲ
የፌደራል አቬይሽን አስተዳደር የአውሮፕላኖች ደህንነት ላይ ቁጥጥር የሚደርግ ከመሆኑ በተጨማሪ የተለያዩ ቅሬታዎች ሲቀርቡለት አውሮፕላኖቹ እንዳይሸጥና እንዳይበሩ የማድረግ ስልጣን ቢኖረውም ይህንን ሳያደርግ በመቅረቱ የቦይን 737 ማክስ አሰቃቂ አደጋዎች ደርሰዋል።
ለዚህ ደግሞ ቦይንግ ከፈረንሳዩ የአውሮፕላን አምራች ኤር ባስ ጋር ባለበት ፉክክር ምክንያት አስፈላጊውን ቁጥጥርን ቸል በማለቱ በዚህ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን ሳቢያ የኢንዶኔዢያውን አደጋ ጨምሮ ከ300 በላይ ሰዎች ሊሞቱ ችለዋል ይላሉ።
በክሳቸው ላይ ለደንበኞቻቸው በሰው የ800 ሚሊየን ዶላር ካሳ መጠየቃቸውን የተናገሩት አቶ ሼክስፒር የአሜሪካ መንግሥት ለክሳቸው መልስ ለመስጠት እስከ አምስት ወር ድረስ የጊዜ ገደብ እንዳለው ገልፀዋል።
የማይመልሱ ከሆነ ወደ ፍርድ ቤት በመሄድ አስገድደን ለደንበኞቻችን ፍትሕ ለማግኘት እንሞክራለን ብለዋል።
ቦይንግ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በወንጀል እየተመረመረ እንደሆነ የጠቀሱት ጠበቃ ሼክስፒር የአሜሪካ የፍትህ መሥሪያ ቤትና የወንጀል መርማሪው አካል ኤፍ ቢ አይ በወንጀል እየመረመራቸው መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ይህ በቦይንግ ታሪክ ውስጥ ተደርጎ አያውቅም ያሉት ጠበቃው የሚያሳየን ወንጀሉ ከፍ ያለና ከፍትሀ ብሔር፣ ከገንዘብና ቸልተኝነት አልፎ ወንጀል መሆኑን ነው ይላሉ።
“እኛ መረጃ እያላቸው፣ እያወቁ የደበቁ ሰዎች አሉ ብለን ነው የምናምነው” የሚሉት አቶ ሼክስፒር በአሜሪካም፣ በአውሮፕላን ማምረት ታሪክም፣ ምናልባት በፋብሪካዎች ታሪክም ትልቁ ክስ ነው የሚሆነው ይላሉ።
የቦይንግ ይቅርታ
ቦይንግ በተፈጠረው አደጋ የተሰማውን ሐዘን በመግለጽ ይቅርታ መጠየቁ ይታወሳል። ይህ ግን ለአቶ ዘካሪያስ የሚዋጥ አይደለም። ይቅርታ የሚጠየቀው የተጎዳውን ሰው ነው የሚሉት አቶ ዘካሪያስ ቦይንግ ግን በመገናኛ ብዙኀን ላይ ወጥቶ ይቅርታ የጠየቀው አጠቃላይ ማህበረሰቡን መሆኑን በማንሳት በአደጋው ቤተሰቦቻቸውን ላጡ ወገኖች ቦይንግን ከሚያክል ኩባንያ የሀዘን መግለጫ ፓስት ካርድ እንኳን እንዳልደረሳቸው ያነሳሉ።
“የእኔ እናትና አባት እኮ ኢንተርኔት የላቸውም፤ የእኔ እናትና አባት እኮ ቦይንግ ያለውን ነገር በቴሌቪዥን ሊያዩ አይችሉም ” በማለት የኢትዮጵያ አየር መንገድ አደጋው ከተፈጠረበት ዕለት አንስቶ እስከ አንድ ሳምንት ድረስ ቤተሰቦቻቸው ቤት በመመላለስ፣ አበባና ካርድ በመላክ፣ ላላቸው ጥያቄዎች ሁሉ አቅማቸው በፈቀደ መልስ በመስጠት ሐዘናቸውን መጋራቱን ይገልጣሉ።
• በእነብርጋዴር ጀነራል ተፈራ ማሞ የክስ መዝገብ ፍርድ ቤት የቀረቡት ተጠርጣሪዎች ለሀምሌ 29 ተቀጠሩ
በተጨማሪም ቦይንግ በመግለጫው ላይ አውሮፕላኑ ከመሬት ለቅቆ አየር ላይ በቆየባት ስድስት ደቂቃ ውስጥ ያለውን ጉዳይ ብቻ በማንሳት ለአውሮፕላኑ መከስከስ አብራሪዎቹን ጥፋተኛ ለማድረግ መሞከሩን በመጥቀስ፤ ነገር ግን ትልቁ ስህተት የተሰራው አውሮፕላኑን ከ737 ወደ 737 ማክስ የተደረገውን የዲዛይን ለውጥ፣ ዋጋ ለመቀነስ የሚረዱ ነገሮች ማንም እንዲያውቅና እንዲናገር አይፈልጉም በማለት ቦይንግ ወጥቶ በተናገረ ቁጥር በአደጋው ወንድሙን እንዳጣ ቤተሰብ ይጎዳኛል ይላሉ።
“ቦይንግ አዝነናል ቢል፣ የምንችለውን እናደርጋለን ሊል ይችላል ግን እየዋሸን ነው።”
ፍትህ የሚናፍቁት ቤተሰቦች
አቶ ዘካሪያስ እንደቤተሰብ ሐዘን ላይ ብቻ ሳንሆን ፍትህም እንዲከናወን እንፈልጋለን በማለት ያለባቸውን ተደራራቢ ጫና ይናገራሉ። ያጣነው ለቤተሰቡ ኩራት የነበረ ሰው ነው በማለት ባለቤቱና ልጆቹም እንዲሁም እናትና አባቱ የደረሰባቸውን ሐዘን ያስረዳሉ።
እናታችን የስኳር ሕመምተኛ ስለነበረች የሐዘኑ ሰሞን ለእርሷም ለቤተሰቡም ከባድ ወቅት ነበር የሚሉት አቶ ዘካሪያስ በተደጋጋሚ የስኳር መጠናቸው ከፍ ብሎ እንደነበር ሐዘናቸው ብርቱ እንደሆነ ይናገራሉ።
ለዚህም ይህንን ጉዳይ ወደ ፍትህ አደባባይ ለመውሰድ እኔና የባለቤቴ ወንድም ለመጋፈጥ የወሰንነው ይላሉ።
የተሰራው ስህተት እንዳይሸፋፈን እና ግልፅ እንዲወጣ ቦይንግን መብረር ትችላለህ ብሎ የምስክር ወረቀት የሚሰጠውን አካል ፌደራል አቬይሽን አስተዳደር መክሰሱ ጥቅም አለው ይላሉ።
• ኢትዮጵያ ወደ አውሮፓና እስያ ሠራተኞችን ልትልክ ነው
“የኢትዮጵያ አየር መንገድም ቢሆን የአሜሪካ ፌደራል አቬይሸን የሰጠውን ምስክርነት ነው አምኖ አውሮፕላኑን ሊገዛ የሚችለው” የሚሉት አቶ ዘካሪያስ እነዚህን ቦይንግ ሰራሽ አውሮፕላኖች እራሱ አረጋግጦ መብረር ይችላሉ ሲል እንደሚሸጡና ወደ ሥራ እንደሚገቡ ይናገራሉ።
ስለዚህ ይህ መስሪያ ቤት መከሰሱ የተፈጠረውን ችግር ከማወቅ አንጻር ቦይንግ 737 ማክስ ላይ ያልተመለከተንው ምን ነበር የሚለውን በጥልቀት ማወቅ እንዲቻል ይጠቅማል ይላሉ።
ሁለተኛው ደግሞ ይላሉ አቶ ዘካሪያስ “ከአሁን በኋላ ተመሳሳይ ችግር እንዳይከሰት ይህ መስሪያ ቤት ለገዛ ስማቸው ሲሉና በቦይንግ የሚበረውን ማህበረሰብ እምነት መልሰው ለማግኘት ሲሉ መጠንቀቅ ይጀምራል” ይላሉ።
በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩ አሜሪካውያኑን ጨምሮ ከ30 በላይ ዜጎች መሆናቸውን አስታውሰው ለሌሎች ዜጎች ብቻ ሳይሆን ለአሜሪካውያንም ተጠያቂ በመሆናቸው ጥንቃቄያቸውን ይጨምራል ሲሉ ያስረዳሉ።
ከምንም በላይ ይህ ሕጋዊ አካሄድ ምንም አይነት ውሳኔ አመጣ ምንም፤ መጠየቅ ያለባቸው አካላት ሁሉ መጠየቅ አለባቸው ብለው እንደሚያምኑ ገልጠው ቀላል ጉዳይ እንዳልሆነ ይናገራሉ።
ጥያቄው ለፌደራል አቬይሽን አስተዳደር መቅረቡ የአውሮፕላን አምራቾችን የመቆጣጠርና ፈቃድ የመስጠት ሥራውን በአግባቡ እንዲያከናውን የሚያስገድድ እንደሆነ የሚናገሩት የሕግ ባለሙያው አቶ ሼክስፒር ፈይሳ፤ በዚህም የአውሮፕላኖች ደህንነትን አስተማማኝ በማድረግ የተጓዦች ደህንነት እንዲጠበቅ ያደርጋል ይላሉ።
በተጨማሪም በአደጋው ቤተሰቦቻቸውን ያጡ ሰዎች የፌደራል አቬይሽን አስተዳደርን ተጠያቂ በማድረግ የተሟላ ፍትህን እንዲያገኙ ለማድረግ እንደሚያስችል ይጠቁማሉ።
በአደጋው ብቁ ያልሆነ አውሮፕላን በማቅረብ ቦይንግ ቀዳሚ ተጠያቂ ቢሆንም የፌደራል አቬይሽን አስተዳደር ግንን ከኢንዶኔዢያው አደጋ በኋላ በኢትዮጵያው አየር መንገድ ላይ ችግሩ እንዳይከሰት ማድረግ ይችል ነበር ይላሉ አቶ ሼክስፒር።
ቦይንግን በማንኛውም ሰዓት መክሰስ ይቻላል?
በአደጋው ቤተሰባቸውን ያጡ ኢትዮጵያውያን እስካሁን ድረስ ቦይንግን ያልከሰሱ ኢትዮጵያውያን ይወክለናል የሚሉትን ጠበቃ በሚገባ መርጠው ክሳቸውን ቢያቀርቡ የተሻለ እንደሚሆን ይመክራሉ።
ቦይንግን መክሰስ የሚቻለው አደጋው ከደረሰበት ጊዜ አንስቶ እስከ ሁለት ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ መሆኑን ጠቅሰው፤ ክሱ በቆየ ቁጥር ታሪኩ እየተረሳ እንደሚሄድ፣ የጉዳዩ አስፈላጊነትም እየቀዘቀዘ እንደሚሄድ ይናገራሉ።
በቆዩ ቁጥር ማስረጃዎቹ እየደከሙ ሊሄዱ ስለሚችሉ ሀሳባቸውን ሰብሰብ አድርገው ተገቢውን የህግ አካሄድ ቢጀምሩ መልካም መሆኑን ይናገራሉ።