የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

የአዲስ አበባና እና የድሬዳዋ ምክር ቤቶች እንዲሁም የአካባቢ ምርጫ ከቀጣዩ ሃገር አቀፍ ምርጫ ጋር እንዲካሄድ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባደረገው 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ አስቸኳይ ስብሰባው ወስኗል።

ወደ 2011 ዓ.ም እንዲራዘም የተደረገውን የሁለቱን ምክር ቤቶች ምርጫ በተያዘለት ጊዜ ሰሌዳ መሰረት ማካሄድ እንደማይችል ምርጫ ቦርድ ጠቅሶ ከሃገር አቀፉ ምርጫ ጋር እንዲካሄዱ በደብዳቤ መጠየቁን ተከትሎ ነው ይህ ውሳኔ የፀደቀው።

“አዲስ አበባ የምንወዛገብባት ሳትሆን በጋራ የምንኖርባት ከተማ ናት” ም/ከንቲባ ታከለ ኡማ

የአዲስ አበባ መስተዳደርና የባላደራው ምክር ቤት

ምርጫ ቦርድ ሐምሌ 4/2011ዓ.ም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በፃፈው ደብዳቤ የሁለቱን ምክር ቤት ምርጫ ዘንድሮ ማካሄድ እንደማይቻል ጠቅሷል።

ለዚህም እንደ ምክንያትነት ያቀረበው ምርጫ አስፈፃሚዎችን ለመመልመል፣ ለማደራጀት እና ለስልጠና የቀረው የዓመቱ ጊዜ አጭር በመሆኑ ነው። በውሳኔውም መሰረት በሥራ ላይ ያሉት ምክር ቤቶች ምርጫ እስኪካሄድ ድረስ ሥራቸውን እያከናወኑ ይቀጥላሉ።

በ2010 መካሄድ የነበረበት የሁለቱ ምክር ቤቶች ምርጫ ሃገሪቱ ውስጥ በነበረው አለመረጋጋትን ተከትሎ በዚህ ዓመት እንዲካሄድ መራዘሙ የሚታወስ ነው።