
ባለፈው ሰኞ ሐምሌ 22/2011 ዓ.ም በጎንደር ከተማ 3217 የሚሆኑ የመትረየስ (አብራራው) ጥይቶች መያዛቸውን የጎንደር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ሰጤ ዘርጋው ለቢቢሲ ገልፀዋል።
ኮማንደሩ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ተጠርጣሪው ግለሰብ ጥይቶቹን በባጃጅ ጭኖ ሲሄድ በቁጥጥር ስር ውሏል።
በወቅቱ ወደ ከተማ የመጡ እንግዶችን ለመቀበል መንገድ ተዘጋግቶ እንደነበር የገለፁት ኮማንደሩ ባጃጁ መንገዱን ጥሶ ለማለፍ ሲሞክር እንዲቆም መታዘዙን ይናገራሉ።
•ሕገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር መበራከት ምንን ያመለክታል?
ይሁን እንጂ ባጃጁን ሲያሽከረክር የነበረው ግለሰብ ከመቆም ይልቅ ለማምለጥ ሲሞክር የጸጥታ ኃይል ተከታትሎ በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ኮማንደሩ ተናግረዋል።
ግለሰቡ ከአራተኛ ጣቢያ አካባቢ ልዩ ስሙ ፋጭት ከሚባል ቦታ ወደ ‘ወጥቶ ባርቶ’ የተባለ ሥፍራ እያመራ ነበር ብለዋል።
በወቅቱ በባጃጁ ውስጥ አሽከርካሪው ብቻ የነበረ ሲሆን ከሱ ጀርባ ያሉትንም ለማግኘት ምርመራ ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል።
ጥይቱ እንዴት ተገኘ? ከየት መጣ? የሚለው በምርመራ ላይ መሆኑን ኮማንደር ሰጤ ነግረውናል።
ፌደራል ፖሊስ ከጥቂት ወራት በፊት ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳስታወቀው ከሃምሌ 1፣ 2010 ዓ. ም. እስከ ጥቅምት 20፣ 2011 ዓ. ም. 2,516 የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች በሕገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወሩ መያዛቸውንና 7,832 የጦር መሳሪያ ጥይቶችም ወደ ሀገር ውስጥ ለመግባት ሲሉ መያዛቸውን አስታውቋል።
ይህም ብዙዎችን ምን እየተካሄደ ነው? የሚል ስጋት ውስጥ ከትቷል። መንግሥት ምን እያደረገ ነው ? የሚል ጥያቄም በስፋት እያስነሳ ነው።
•በአስር ወራት አማርኛ ማንበብና መፃፍ የቻለው ጀርመናዊ
ሕገ ወጥ የመሳሪያ ዝውውሩ በጉልህ ከታየባቸው ክልሎች የአማራ ክልል በዋነኛነት ይጠቀሳል።
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል እንደሻው ጣሰው ቢቢሲ ከጥቂት ወራት በፊት ባናገራቸው ወቅት ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውሩ አሁን ያለበትን ደረጃ ሲያስረዱ ”በአንዳንድ የሃገሪቱ ስፍራዎች የጦር መሳሪያ ዝውውሩ እንደጨመረ እና በሌሎች አካባቢዎች ደግሞ በተደረገው ቁጥጥር የዝውውር መጠኑ ቀንሷል” ይላሉ።
በተደጋጋሚ እየተከሰተ ያለው ሕገ-ወጥ መሳሪያ ዝውውር ምንጩ አንድ ብቻ ሳይሆን በርከት ያለ እንደሆነ ይታመናል። በመንግሥት እጅ የነበሩ ጦር መሳሪያዎችም በዚህ ውስጥ እንደሚገኙ ኮሚሽነሩ ያመለክታሉ ”ሕገ-ወጥ መሳሪያዎች ከውጪ ብቻ አይደለም የሚመጡት። ሃገሪቱ ውስጥ ካሉ የመሳሪያ ግምጃ ቤቶች ውስጥ በተለያዩ ኃይሎች ተዘርፈው የተወሰዱም ይገኙበታል።”
እንደ ኮሚሽነሩ ከሆነ፤ ከሃገር ውስጥ ከተዘረፉ መሳሪያዎች ውጪ ከደቡብ ሱዳን፣ ከጅቡቲ እና ከሶማሊያ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ሕገ-ወጥ መሳሪያዎችም መጠናቸው ቀላል የሚባል አይደለም።