July 30, 2019
የፍራንክፈርቱ የባልደራስ ስብሰባ ሂደት በተለያዩ የዜና አውታሮች ተዘግቧል። በአካል በቦታው የነበርነው ሰዎች የዜና አውታሮቹ የዘገቡትን ብቻ ሳይሆን፣ በዓይናችን ያየነውን እንመሰክራለን።

ያልነበራችሁት ደግሞ የሰማችሁትን አንድም አምናችሁ ትቀበላላችሁ፣ አሊያም በመጠራጠር ታልፉታላችሁ።
የስብሰባው አጀንዳ አንድ ነበር። እሱም –
“ሕገ- መንግሥታዊ ለውጥ እስካልመጣ ወይም ሕገ መንግሥቱ እስካልተቀየረ ድረስ የአዲስ አበባ ጥያቄ መልስ አያገኝም”
የሚል ነበር። ይህን የአጀንዳ ዓውደ ርዕስ መነሻ በማድረግ ብዙ በጣም ብዙ ተያያዥ ጉዳዮች ተነስተዋል። ወደዚያ ዝርዝር በመግባት አንባቢን ማሰልቸት አልፈልግም። የመልክቴ ዓላማም ያ አይደለም። ይህን ከላይ የተጠቀሰውን አንድ አጀንዳ ለመከታተል የመጣው የተሳታፊዎች ዓይነት ግን በሦስት ይከፈል እንደ ነበር መግለጹ አስፈላጊ ይመስለኛል።
ሀ/ የአዲስ አበባ ባለ-አደራ ምክርት (ባጭሩ ባልደራስ) ዓላማ ደጋፊዎች፣ አባላትም ሊኖሩበት ይችላሉ።
ለ/ የአዲስ አበባን የእኔነት የባለቤትነት ጥያቄ አስመልክቶ የሚፈልጉትን ብቻ ለመስማት የመጡና ለእነሱ የማይስማማ ጉዳይ ከተነሳ ለመጥበጥ ተሰባስበው የመጡ፣
ሐ/ የባለ-አደራው ምክር ቤት ምክትል ሰብሳቢ የሆነው ኤርምያስ ለገሰ ባለፉት ዓመታት ኢሳትን እንደ መድረክ ተጠቅሞ ባደረገው ንቁ ተሳትፎ እንዲሁም በጻፋቸው መጻሕፍትም፣ የኢትዮጵያን ፓለቲካ ስስ ብልቱን ስለሚያውቀው እና ለኢትዮጵያ ሕዝብም እጅግ በጣም ጠቃሚ መረጃ እየሰጠ ወያኔን እርቃኑን ያስቀረ ሰው በመሆኑ ይህን ሰው ለማዳመጥ የመጣ።
በዚህ የስብሰባ ይዘት ስብጥር መሠረት ስብሰባው ተካሂዶ፣ እንግዳውም ተገቢ የሆነ ገለጻ አድርጎ፣ የጥያቄና ውይይት ፕሮግራም በበቂ ሁኔታ ጊዜ ተሰጥቶ፣ የአቋም መግለጫ በማውጣት ስብሰባው ተጠናቋል።
ችግሮች፣ ከላይ የስብሰባውን ተካፋዮች ዓይነት (ስብጥር) ለመግለጽ እንደሞከርኩት እነሱ የሚፈልጉትን መስማት ብቻ እንጅ የሌላውን ሀሳብ ማዳመጥ በማይሹ ኃይሎች ስብሰባው ተበጥብጧል። ይህም ድርጊት ገና ወደ ስብሰሰባው በር መግቢያ ላይ ጀምሮ ስብሰባው ከተጀመረ በኋላም፣ ሰበብ እየፈለጉ ውይይቱን በተደጋጋሚ ለማቋረጥ በመሞከር የከሸፈ ሕልም አልመዋል።
ልክ አዲስ አበባ እስክንድር ነጋም ሆነ የባልደራስ ምክር ቤት ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጥ የመንጋ ቡድን እንደሚረብሸው በፍራንክፈርቱ ስብሰባም ከዚያ ያልተለየ ሁኔታ ታይቷል። የፁጉራቸው መንጨፍረርም ከሀገር ቤቶቹ ጋር ልዩነት አይታይበትም። እንዲያውም የፀጉር መዋቅር ያላቸውም ይመስላል ማለቱ ሳይቀል አይቀርም።
የአረባበሻቸው ዓይነትም ከአዲስ አበባው ጋር ይመሳሳል። አካላዊ ጉዳት ለማድረስም ያዙኝ ልቀቁኝ ይሉ ነበር።
ተሰብሳቢውም የስብሰባው አዘጋጆችም ጨዋነት በተመላበት መንገድ እንደ በጥባጮቹ ባለመሆን ስብሰባው በትዕግሥት ሊጠናቀቅ ችሏል። በተለይ በተለይ የኦሮሞ ልጆች ተለይተው እየተለቀሙ ስብሰባውን እንዳይሳተፉ ተብሎ በሶሻል ሚዲያ የተለቀቀው ዜና እጅግ እጅግ ያሳዝናል። የስብሰባውን ሕግ አክብረው እስከ መጨረሻው ስብሰባውን የተከታተሉ፣ በጥያቄና አስተያየት በመስጠትም የተሳተፉ የኦሮሞ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ይህን ዓይነቱን በሬ-ወለደ ዜና ሲሰሙ ምን እንደሚሰማቸው አላውቅም?
ሕግ ያለበት አገር የምንኖር በመሆናችን ስብሰባው በሕግ ተመርቶ በጥባጮችም በጉልበት ሳይሆን አቅማቸውን በሕግ እንዲያውቁ ተደርጎ እስከ መጨረሻው ለመቆየት ተችሏል። ጥያቄው ግን ሰው ሕግ ባለበት አገር እየኖረ ከብት ልሁን ሲል መፍትሔው ምንድነው ነው? በዚህ አካሄድስ እንዴት ነው አብሮ መጓዝ የሚቻለው ነው?
በማናቸውም ብሔሮች የሚገኙ ፅንፍ-ረገጥ አክቲቪስቶችን እየሰማንና የእነሱን ተልዕኮ ለማሳካት የእነሱ ተላላኪዎች እየሆን በየቦታው ብጥብጥ የምንፈጥር ከሆነ፣ የሚታሰበውን የዴሞክራሲ ሥርዓት ሳይሆን የምንፈጥረው፣ ሥርዓት አልባ የመንጋ ፓለቲካ በሀገራችን እየገነባን ስለመሆኑ የትናንትናው ስብሰባ በቂ ምስክር ይመስለኛል።
ለውጡንም አደጋ ላይ እየጣለው ያለው የመንጋ ፓለቲካ አራማጁን ኃይል አደብ እንዲገዛ ከማድረግ ይልቅ እሹሩሩ ማለቱ ስለ በዛ ይመስለኛል።
እኔ እንደ አንድ የስብሰባው ታዛቢ የተመለከትኩትን በእውነት የምመሰክረው ስብሰባውን ሳይረብሽ ከስብሰባው አንድም ሰው የዚህ ብሔር አባል ነህ ተብሎ የወጣ የለም። መጥፎ እየሰሩ፣ ብሔርን መደበቂያ ዋሻ ለማድረግ መዋሸት በዚያ በመጡበት ብሔረሰብ ላይ ወንጀል መፈጸም ነው።
ለወደፊቱም ቢሆን ሕግ ተከብሮ በሚኖርባቸው የአውሮፓ አገሮች በአካል እየኖርን በመጥበጥ ጋይንት፣ ወይም ደንቢዶሎ፣ ወይም ብቸና ወይም አዲስ አባባ ወይም ሻሸመኔ፣ ወይም አዋሳ እንደሚደረገው እናድርግ ካልን ትርፉ ጥቁር ሊስት ውስጥ ገብቶ ሕይወትን ማበላሸት ነው።
እንድንሰማ የምንፈልገውን ሳይሆን ለእኛ ጆሮ የማይጥመንንም አዳምጠን በሰለጠነ መንገድ በመወያየት ወደ ጋራ መፍትሔ ለመድረስ እባካችሁ በኢትዮጵያ ሥም ጥረት እናድርግ።
እንደ ተጨማሪ ማስታወሻ
የጠበካችኋቸው ነጥቦች ብቻ ሳይሆኑ ሌሎችም በዘገባዬ ያላነሳኋቸው ብዙ ጉዳዮች አሉ። ፅሁፉን ማርዘም ባለመፈለግ፣ ሌሎች የሚዲያ ሰዎችም ስለ ስብሰባው እንደሚያቀርቡ ስለምገምት ድግግሞሽ እንዳይሆን በማሰብ ነው።
ዋናው ምክንያቴ ግን በስብሰባው ላይ አንድ ዘር ተለይቶ ከስብሰባው እንደታገደ በሶሻል ሚዲያ “ነጭ ወሬ” ተሰራጭቶ ስላዳመጥኩ ሌላው ሰው ከመወናበዱ በፊት ይህን በቅድሚያ መከላከል ያስፈልግ ስለ ነበር ያንን መንገድ ነው በዘገባዬ ለማሳየት የፈለኩት። (የአግላይነት ፓለቲካ መነገጃ ምክንያት ተደርጎ ስለሚወሰድ)
ጽሁፉን በፌስቡክ ገጼም ለጥፌው ስለነበር መልክቴም ውጤታማ ሆኖ፣ የኦሮሞ ተወላጅ ጓደኝቼም ጭምር በውስጥ መስመር እውነታውን ስለገለጽክልን “ሳናመሰግንህ አናልፍም” በማለት ስሜታቸውን ገልጸውልኛል።
ለማንኛውም በወንድማችን በኤርምያስ ገለፃ መሠረት በሕገ መንግሥቱ “ልዩ ጥቅም” ማለት የባለቤትነት ጥያቄ እንጅ ሌላ ትርጉም እንደሌለው በማያሻማ መንገድ ገልጾታል። እናም የአዲስ አበባ የችግር ቅርቃር የተቸነከረበት በሕገ መንግሥቱ ስለሆነ ይህን ማስቀየር ግድ ስለሚል ትግሉ ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት መሆኑን አበክሮ አሳስቧል።
አሁን ባለው ሕገ መንግሥት መሠረት 9 ክልሎች ሆነው ኢትዮጵያን ሲመሰርቱ ወደ ስድስት ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ የሚኖርባት አዲስ አበባ ግን ኢትዮጵያን በጋራ እንድትመሰርት አልተፈቀደላትም። ባጭሩ የባለ አደራው ምክር ቤት የእንቅስቃሴው መሠረታዊ ዓላማም፣
– አዲስ አበባ የኗሪዎቿ እንጅ ሌላ አካል በባለቤትነት የሚይዛት ከተማ አለመሆኗ፣
-በፌዴሬሽን ምክር ቤት ወደፊት ሕገ መንግሥታዊ ውክልና እንዲኖራት፣
-አዲስ አበባ እራሷን የቻለች እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያን መሠረቱ እንደተባሉት ዘጠኝ ክልሎች መብትና እስታተስ እንዲኖራት
– ከሕገ መንግሥት መቀየር ጀምሮ አዲስ አበባን አስመልክቶ በሚነሱ የባለቤትነት ጥያቄዎች ዙሪያ አቋም የማይወስድ የፓለቲካ ድርጅት የአዲስ አበባ ሕዝብ ድምጹን ባለመስጠት እንዲቀጣው የባለ-አደራው ምክር ቤት ሽንጡን ገትሮ እንደሚታገል ኤርምያስ በመግለጫው ደጋግሞ ገልጿል።
ሌላው ያሰመረበት ነጥብ ደግሞ እነግ ወይም ሌሎች የኦሮሞ ድርጅቶች አሁን “ምርጫ ወይም ሞት” ያሉበት ዋናው ምክንያት ሕገ መንግሥቱ ሳይቀየር በሚካሄድ ምርጫ አዲስ አበባን ይዘው መሄድ እንዲችሉ መሆኑን መረዳት ግድ እንደሚል ነው።
ኆኅተብርሃን ጌጡ